ክፍል አንድ - ዕባዳዎች በልብ ላይ የሚያሳርፉት አሻራ(መውደድ ፦) 1

ክፍል አንድ - ዕባዳዎች በልብ ላይ የሚያሳርፉት አሻራ(መውደድ ፦) 1

መውደድ

የመውደድ ጽንሰ ሀሳብ ፦

የአላህ ውዴታ፦

አላህንﷻ መውደድና እርሱን ማፍቀር ማለት የልብ በርሱ መጽናናትና ወደርሱ ማዘንበል፣እርሱ ለሚፈልገው ነገር ሁሉ ምላሽ መስጠት፣የርሱ ውዳሴና ዝክር ልብን መቆጣጠር ማለት ነው።

የአላህ ፍቅር እውነታ

አላህን ማፍቀር ዕባዳውን ማፍቀር፣ለርሱ መተናነስና እርሱን ማላቅ ነው። ይህም በአፍቃሪው ልብ ውስጥ ትእዛዛቱን በመፈጸምና ከእገዳዎቹ በመታቀብ የሚገለጽ የተፈቃሪው አላህﷻ አክብሮትና ልቅና መኖር ማለት ነው። ይህ ፍቅር የኢማንና የተውሒድ መሠረት ሲሆን፣የሚያስገኘው የትሩፋት ውጤቶች ከቁጥር በላይ ናቸው። አላህ የሚወዳቸውን ቦታዎች፣ጊዜያትና ግለሰቦች፣አካላዊና አንደበታዊ ተግባራትንና የመሳሰሉትን አላህ የሚወዳቸውን ነገሮች ሁሉ መውደድም አላህንﷻ የመውድና የማፍቀር አካል ነው።

የአላህ ፍቅር ለርሱ ብቻ ፍጹም የተደረገ መሆን ሲኖርበት፣ተፈጥሯዊ የሆነ ወላጆችን ልጆችን መምህርን፣ምግብና መጠጥን፣ትዳራዊ ግንኑነትን፣አልባሳትን ወዳጆችንና የመሳሰሉትን ከመውደድና ከማፍቀር ጋር አይጋጭም።

ሐራም ሆኖ የተከለከለው ፍቅር፣ሙሽሪኮች ጣዖቶቻቸውንና አማልክቶቻቸውን አላህን እንደሚወዱ መውደድ፣ነፍስያ የምትወዳቸውን ነገሮች ፍቅር ከአላህﷻ ፍቅር ማብለጥ ወይም አላህ ﷻ የማይወዳቸውን ጊዜያትና ቦታዎችን፣ግለሰቦችን፣ሥራዎችን፣ንግግሮችን መውደድ ነው። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(وَمِنَ النَّاسِ مَنْ يَتَّخِذُ مِنْ دُونِ اللَّهِ أَنْدَادًا يُحِبُّونَهُمْ كَحُبِّ اللَّهِ وَالَّذِينَ آَمَنُوا أَشَدُّ

حُبًّا لِلَّهِ)

‹ከሰዎችም ከአላህ ሌላ ባላንጣዎችን (ጣዖታትን)፣አላህን እንደሚወዱ የሚወዷቸው ኾነው የሚይዙ አልሉ፤እነዚያ ያመኑትም፣አላህን በመውደድ (ከነርሱ) ይበልጥ የበረቱ ናቸው፤››

[አልበቀራህ፡165]

ከአላህ ፍቅር ትሩፋቶች መካከል ፦

1-

የተውሒድ መሰረትና የተውሒድ መንፈስ መሆኑ፣ፍቅርና ውዴታን ለአላህ ብቻ ፍጹም ማድረግ ነው። ይህ የዕባዳ መሰረታዊ እውነታ ነው። አንድ አማኝ ለአላህ ያለው ፍቅር የተሟላ እስኪሆንና ከሚወዳቸው ነገሮች ሁሉ ቀዳሚ፣የተቀሩት ተፈቃሪዎቹ ለዚህ የተድላውና የመድህኑ መገኛ ለሆነው ዐቢይ ፍቅር ተመሪ በሚሆኑበት ሁኔታ የአላህﷻ ፍቅር የበላይ ተቆጣጣሪና ወሳኝ እስኪሆን ድረስም ተውሒድ ምሉእ አይሆንም።

2-

የአላህ አፍቃሪ በችግርና በመከራ ወቅት መጽናኛ የሚያገኝ መሆኑ። አፍቃሪ ችግሮችን የሚያስረሳና መከራዎችን የሚያዘናጋው የፍቅር ጣዕምና ስሜት ይሰማዋል።

አላህﷻ ከሚመለክባቸው ዕባዳዎች ሁሉ፣ፍቅርን ፍርሃትንና ተስፋ በርሱ ላይ መጣልን ከመሳሰሉት የዕባዳ ዓይነቶች የሚበልጡ የሉም።

አላህን ለመገናኘት መናፈቅና መጓጓት፣የዓለማዊ ሕይወት ጣጣዎችን ከልብ የሚያባርር የሕይወት መንፈስ ነው።

3-

የተሟላ ደስታና ምቾት ፦ ይህ ሊገኝ የሚችለው አላህን ﷻ በማፍቀር ብቻ ነው። ልብ ከብቸኝነቱ የሚወጣው፣የፍቅር ረሃቡንና ጥማቱን የሚያረካው በአላህ ፍቅርና ወደርሱ ብቻ በመመለስ ነው። ሁሉም ቁሳዊ ደስታዎችና መደሰቻዎች ቢሟሉለት እንኳ በአላህ ﷻ ፍቅርና በርሱ ውዴታ ብቻ እንጂ ልብ መጽናናትና መረጋጋት አይችልም። የርሱ ፍቅር የሕሊና ደሰታና የመንፈስ እርካታ ነው። ጤናማ ልቦችና በጎ መንፈስ፣የጠራ ሕሊና እና የጸዳ ልቦና ባላቸው ሰዎች ዘንድ ከርሱ ፍቅር ይበልጥ የሚጣፍጥ፣የሚያዝናና የሚያጽናና፣የርሱን ግንኑነት ከመናፈቅ ይበልጥ የሚያረካ ምንም ነገር የለም። በአንድ ሙእምን ልብ ውስጥ ያለው የኢማን ጣእምና ጥፍጥናው ከምንም በላይ ነው። የሚሰማው ደስታና እርካታም ከየትኛውም ደስታና እርካታ ይበልጥ የተሟላ ነው።

‹‹ሦስት ነገሮች ያሉት ሰው የኢማንን ጥፍጥና ያገኝባቸዋል ፦ አላህና መልክተኛው ከተቀሩት ሁሉ እርሱ ዘንድ ይበልጥ የተወደዱ መሆን፤ለአላህ ብሎ ብቻ አንድን ሰው የሚወድ መሆን፤አላህ አንዴ ከርሱ ካዳነው በኋላ ወደ ኩፍር መመለስን ወደ እሳት መወርወርን የሚጠላውን ያህል የሚጠላ መሆን ናቸው።››

(በቡኻሪ፣በሙስሊምና በነሳኢ የተዘገበ)

በአላህ ﷻ ፍቅር መርካታን፣በርሱ መረጋጋትንና በርሱም መጽናናትን ከተነፈገ ሰው ይበልጥ በምድረ ዓለም ላይ ዕድለቢስ የሆነ መናጢ የለም።

የአላህን ፍቅር የሚያስገኙ ምክንያቶች ፦

ጌታችን ﷻ የሚወዱትን ይወዳቸዋል፣ የሚቀርቡትንም ይቀርባቸዋል። የአላህን ፍቅር የሚያስገኘው የመጀመሪያው ምክንያት ባሪያው፣ከፍጥረታቱ ውስጥ ማንንምና ምንንም በማይወድ ውዴታ ፈጣሪ ጌታውን መውደድ ነው። የአላህን ውዴታ የሚያስገኙ ዝርዝር ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው ፦

1-

ቁርኣንን ትርጉሙንና መልክቱን እያስተነተኑ በአስተውሎና በግንዛቤ ማንበብ። ራሱን በአላህ መጽሐፍ የጠመደና ጥናቱን ሥራዬ ብሎ የያዘ ሰው፣ልቡ በአላህ ፍቅር የታነጸና የተሞላ ይሆናል።

2-

መደበኛ ግዴታዎችን ከፈጸሙ በኋላ ተጨማሪ በሆኑ የሱንና ዕባዳዎች (ነዋፍል) ወደ አላህ መቃረብ።

‹‹ባሪያዬ እኔ እስክወደው ግዴታ ባልሆኑ ተጨማሪ የሱንና ሥራዎች (ነዋፍል) በመፈጸም ወደ እኔ ይቃረባል። በወደድኩት ጊዜ የሚሰማበት ጆሮው፣የሚያይበት ዓይኑ፣የሚይዝበት እጁና የሚጓዝበት እግሩ እሆንለታለሁ። ከለመነኝ በእርግጥ እሰጠዋለሁ። ከክፉ ነገር የኔን ጥበቃ ከለመነኝም በእርግጥ እጠብቀዋለሁ።››

(በቡኻሪ የተዘገበ ሐዲሥ አልቁድሲ)

3-

በሁሉም ሁኔታዎች በአንደበትና በልብ፣ በተግባርና በስነምግባር አላህን ﷻ ማውሳትና የርሱን ዝክር ማዘውተር።

4-

አላህ የሚወዳቸውን ነገሮች፣ነፍስያ ከምትወዳቸው ፍላጎቶችና ቁሳዊ መደሰቻዎች ማስቀደም።

(يُحِبُّهُمۡ وَيُحِبُّونَهُ )

‹‹የሚወዳቸውንና የሚወዱትን።››

[አልማኢዳህ፡54]

5-

ልብን የአላህን ﷻ ስሞችና ባህርያት እንዲያጠና እና እንዲያውቅ ማድረግ።

6-

ውለታዎቹን፣ጸጋዎቹን፣ግልጽና ስውር ችሮታዎቹን ማስተዋል።

7-

የልብ አላህ ﷻ ፊት ሙሉ በሙሉ መተናነስና መሰባበር።

8-

ጌታችን ﷻ ወደ ቅርቢቱ ሰማይ በሚወርድበት የሌሊት የመጨረሻው ሲሦ፣ በዱዓእ፣በዝክርና ቁርኣንን በማንበብ፣በተሟላ አደብ ከፊቱ ቆሞ በመስገድ፣ከዚያም ምህረቱን በመለመን በተውበትና በእስትግፋር በማጠናቀቅ ከአላህ ጋር መሆን።

9-

ከእውነተኛ የአላህ ወዳጆች ጋር መቀመጥ፣ መልካም የአዝመራ ፍሬ እንደሚለቀመው የንግግራቸውን መልካም ፍሬዎች መልቀምና መሰብሰብ። መናገር ለራስና ለሌላውም ተጨማሪ ጠቃሜታ ያለው ሆኖ እስካልተገኘ ድረስ በዝምታ መቆየት።

10-

ልብን ከአላህ ﷻ ከሚለዩ ምክንያቶች ሁሉ መራቅና ምክንያቶቹንም ማራቅ።

የአላህ ፍቅር ለባሪያው ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች መካከል የሚከተሉትን እናገኛለን፦

- አላህ ﷻ የወደደውን ሰው ይመራል፣ ያቀርበዋል። ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹አላህን ﷻ እንዲህ ይላል ፦ እኔ ባሪያዬ ባሰበኝበት እገኛለሁ። እኔን ሲያስበኝ ከርሱ ጋር እገኛለሁ። በውስጡ ሲያስታውሰኝ በውስጤ አስታውሰዋለሁ። በጉባኤ ሲያስታውሰኝ ከርሱ ጉባኤ በላጭ በሆነ ጉባኤ ላይ አስታውሰዋለሁ። አንድ ስንዝር ወደኔ ከቀረበ በአንድ ክንድ ወደርሱ እቀርባለሁ። በአንድ ክንድ ወደኔ ከቀረበ በአንድ ባዕ (ሁለት እጆች ወደ ጎን ሲዘረጉ ከአንዱ መዳፍ እስከ ሌላኛው መዳፍ ለው ርቀት) ወደርሱ እቀርባለሁ። እየተራመደ ወደኔ ከመጣ እየሮጥኩ ወርሱ እመጣለሁ።››

(በቡኻሪ የተዘገበ)

ባሪያው ጌታውን በፈራና በተጠነቀቀ ቁጥር ወደ ሌላ መመሪያ ከፍ ይደረጋል። አላህን በወደደ ቁጥርም መመራት (ህዳያ) ይጨመርለታል። መመራት በተጨመረለት ቁጥርም ፍርሃትና ተቅዋ ይጨመርለታል።

- አላህ የወደደውን ሰው በምድር ላይ ተቀባይነት እንዲያገኝ ያደርጋል ፦

ተቀባይነት ያገኛል ማለት ጌታው የወደደው ይህ ባሪያ፣በሌሎች ዘንድ ውዴታና መልካም ዝና ያገኛል፣የአላህን ﷻ ውዴታ እምቢ ያለ በመሆኑ ካፍር ብቻ ሲቀር ሁሉም ነገር ይወደዋል፣ወደርሱ ያዘነብላል ማለት ነው። ረሱል ﷺ እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹አላህ አንድ አገልጋዩን ሲወደው ጅብሪልን ይጠራና፦ ‹እኔ እገሌን ወድጄዋለሁና አንተም ውደደው› ይላል። ጂብሪልም ይወደዋል፤ከዚያም ለሰማይ ነዋሪዎች፦ ‹አላህ እገሌን ይወደዋልና እናንተም ውደዱት› በማለት ያውጃል፤የሰማይ ነዋሪዎችም ይወዱታል፤በምድር ላይም ተቀባይነት እንዲኖረው ይደረጋል።››

(በሙስሊም የተዘገበ)

አላህ ﷻ አንድ ባሪያውን ሲወደው በዚህ መልኩ በጥበቃውና በእንክብካቤው ውስጥ አድርጎት፣ነገሮች ሁሉ በትእዛዙ ስር እንዲሆኑ ያደርግለታል። አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ገር ያደርግለታል። የራቀውን ሁሉ ያቀርብለታል። የዱንያን ጉዳይ ቀላል ያደርግለታል። ጭንቀትም ሆነ ልፋት አይሰማውም። አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(إِنَّ ٱلَّذِينَ ءَامَنُواْ وَعَمِلُواْ ٱلصَّٰلِحَٰتِ سَيَجۡعَلُ لَهُمُ ٱلرَّحۡمَٰنُ وُدّٗا ٩٦)

‹‹እነዚያ ያመኑና በጎ ሥራዎችን የሠሩ፣ አልረሕማን ለነሱ ውዴታን ይሰጣቸዋል።››

[መርየም:96]

- አላህ የደደውን ሰው በራሱ አብሮነት ውስጥ ያደርገዋል ፦ አላህ ﷻ ባሪያውን ከወደደው በጥበቃውና በእንክብካቤው ከርሱ ጋር ይሆናል። ለሚጎዳውና ለሚያውከው ሰው አሳልፎ አይሰጠውም። ከጌታቸው በሚተላለፍላቸው ሐዲሥ አልቁድሲ ውስጥ ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹አላህ እንዲህ ብሏል ፦ የኔን ወዳጅ ጠላቱ ባደረገ ሰው ላይ ጦርነት አውጄበታለሁ፤ባሪያዬ እኔ እስክወደው ግዴታ ያልሆኑ ተጨማሪ የሱንና ሥራዎችን በመፈጸም ወደኔ ይቃረባል። በወደድኩት ጊዜ የሚሰማበት ጆሮው፣የሚያይበት ዓይኑ፣የሚይዝበት እጁና የሚጓዝበት እግሩ እሆንለታለሁ። ከለመነኝ በእርግጥ እሰጠዋለሁ። ከክፉ ነገር ለመዳን የኔን ጥበቃ ከለመነኝም በእርግጥ እጠብቀዋለሁ። ማድረጌ በማይቀረው ነገር ላይ፣እርሱ ሞትን የሚጠላ ሆኖ እኔ ደግሞ እርሱን ማስከፋት የምጣላ በመሆኔ የአማኝ ሰው ነፍስን ከመውሰድ ይበልጥ የማመነታበት ሌላ ምንም ነገር የለም።››

(በቡኻሪ የተዘገበ)

በአላህ መካድ ከሞት በፊት ሞትና የሐዘን መንስኤ እንደሆነ ሁሉ፣እውነተኛ ኢማን የነፍስ ሕይወት፣የደስተኝነትና የመታደል መገኛ ነው።

- አላህ የደደውን ሰው ጸሎቱን ይሰማለታል፤ የለመነውን ይሞላለታል። አላህ ﷻ ምእመናን ባሮቹን ለመውደዱ አንዱ ማስረጃ ገና እጆቻቸውን ወደ ሰማይ ከፍ አድርገው ‹‹ጌታዬ! ጌታዬ!›› ሲሉ በችሮታውና በቸርነቱ ጸሎታቸውን የሚቀበልላቸው መሆኑ ነው። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(وَإِذَا سَأَلَكَ عِبَادِي عَنِّي فَإِنِّي قَرِيبٌۖ أُجِيبُ دَعۡوَةَ ٱلدَّاعِ إِذَا دَعَانِۖ فَلۡيَسۡتَجِيبُواْ لِي وَلۡيُؤۡمِنُواْ بِي لَعَلَّهُمۡ يَرۡشُدُونَ ١٨٦)

‹‹ባሮቼም ከኔ በጠየቁህ ጊዜ፣(እንዲህ በላቸው)፦ እኔ ቅርብ ነኝ፤የለማኝን ጸሎት በለመነኝ ጊዜ እቀበለዋለሁ፤ስለዚህ ለኔ ይታዘዙ፤በኔም ይመኑ፤እነርሱ ሊመሩ ይከጀላልና።››

[አልበቀራህ፡186]

ከሰልማን አልፋሪሲ በተላለፈው መሰረት የአላህ መልክተኛﷺ እንዲህ ብለዋል፦

‹‹አላህ ባለ ይሉኝታ ቸር ጌታ ነው፤አንድ ባሪያው እጆቹን ወደ ላይ ከፍ አድርጎ ሲለምነው ባዶ መመለስ ያሳፍረዋል።››

(በትርምዚ የተዘገበ)

አላህ አንድን ባሪያ ከደደው መላእኮች ምሕረት እንዲለምኑለትና እስትግፋር እንዲያደርጉለት ያደርጋል። መላእኮች አላህን ለሚወድ ሰው ከአላህ ምሕረትና እዝነቱን ይለምኑለታል።

አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(ٱلَّذِينَ يَحۡمِلُونَ ٱلۡعَرۡشَ وَمَنۡ حَوۡلَهُۥ يُسَبِّحُونَ بِحَمۡدِ رَبِّهِمۡ وَيُؤۡمِنُونَ بِهِۦ وَيَسۡتَغۡفِرُونَ لِلَّذِينَ ءَامَنُواْۖ رَبَّنَا وَسِعۡتَ كُلَّ شَيۡءٖ رَّحۡمَةٗ وَعِلۡمٗا فَٱغۡفِرۡ لِلَّذِينَ تَابُواْ وَٱتَّبَعُواْ سَبِيلَكَ وَقِهِمۡ عَذَابَ ٱلۡجَحِيمِ ٧)

‹‹እነዚያ ዐርሹን የሚሸከሙት፣እነዚያም በዙሪያው ያሉት፣በጌታቸው ምስጋና ያወድሳሉ፤በርሱም ያምናሉ፤ጌታችን ሆይ! ነገሩን ሁሉ በእዝነትና በዕውቀት ከበሃል፤ስለዚህ ለነዚያ ለተጸጸቱት፣መንገድህንም ለተከተሉት ምሕረት አድርግላቸው፤የእሳትንም ቅጣት ጠብቃቸው፣እያሉ ለነዚያ ላመኑት ምሕረትን ይለምናሉ።››

[አልሙእሚን፡7]

በተጨማሪም አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(تَكَادُ ٱلسَّمَٰوَٰتُ يَتَفَطَّرۡنَ مِن فَوۡقِهِنَّۚ وَٱلۡمَلَٰٓئِكَةُ يُسَبِّحُونَ بِحَمۡدِ رَبِّهِمۡ وَيَسۡتَغۡفِرُونَ لِمَن فِي ٱلۡأَرۡضِۗ أَلَآ إِنَّ ٱللَّهَ هُوَ ٱلۡغَفُورُ ٱلرَّحِيمُ ٥

‹‹(ከአላህ ፍራቻ) ሰማያት ከበላያቸው ሊቀደዱ ይቀርባሉ፤መላእክትም ጌታቸውን እያመሰገኑ ያወድሳሉ፤በምድርም ላለው ፍጡር ምሕረትን ይለምናሉ፤ንቁ አላህ እርሱ መሓሪው አዛኙ ነው።››

[አልሹራ፡5]

አላህ ﷻ አንድን ባሪያ ከወደደው በመልካም ሥራ ላይ እያለ ይገድለዋል። ረሱል ﷺ እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹አላህ ﷻ ለአንድ ባሪያው በጎውን ከሻለት ዝነኛ ተወዳጅ ያደርገዋል፤ዝነኛ ተወዳጅ መሆን ምን ማለት ነው?! ሲባሉ ከመሞቱ በፊት አላህ ﷻ የበጎ ሥራን በር ይከፍትለትና በዚያ ላይ እያለ እንዲሞት ያደርገዋል፣አሉ።››

(በአሕመድ የተዘገበ)

አላህ ﷻ ባሪያውን ከደደው በሚሞትበት ጊዜ መረጋጋትን ይሰጠዋል ፦

አላህﷻ አንድን ባሪያ ከደደው በቅርቢቱ የዱንያ ሕይወት ጸጥታና መረጋጋትን፣በሚሞትበት ጊዜም እርጋታና ጽናትን ያድለዋል። ነፍሱን በጥንቃቄና በዝግታ የሚያወጡ፣ነፍሱ ስትወጣ የሚያረጋጉት፣በጀነት በማብሰር የሚያጽናኑት መላእክትን ይልክለታል። አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(إِنَّ ٱلَّذِينَ قَالُواْ رَبُّنَا ٱللَّهُ ثُمَّ ٱسۡتَقَٰمُواْ تَتَنَزَّلُ عَلَيۡهِمُ ٱلۡمَلَٰٓئِكَةُ أَلَّا تَخَافُواْ وَلَا تَحۡزَنُواْ وَأَبۡشِرُواْ بِٱلۡجَنَّةِ ٱلَّتِي كُنتُمۡ تُوعَدُونَ ٣٠)

‹‹እነዚያ ጌታችን አላህ ነው ያሉ፣ከዚያም ቀጥ ያሉ፦ አትፍሩ፤አትዘኑም፤በዚያችም ተስፋ ቃል ትደረግላችሁ በነበራችሁት ገነት ተበሰሩ፤በማለት በነሱ ላይ መላእክት ይወርዳሉ።››

[ሓ ሚም አልሰጅዳህ፡30]

አላህ ﷻ አንድን ባሪያ ከደደው ጀነት ውስጥ ለዘለዓለም ነዋሪ ያደርገዋል ፦

አላህ የደደው ሰው፣በወዲያኛው የኣኽራ ሕይወት በርሱ ጀነት ውስጥ ይሆናል። እዚያ የተደገሰለት ታላቅ መስተንግዶ በማንም አእምሮ ታስቦ የማያውቅ ድሎትና ምችት፣ነፍስ የምትፈልገው ሁሉ ያለ ገደብ የምታገኝበት፣ በቃላት የማይገለጽ ተድላ ነው። ቀጥሎ ባለው ሐዲሥ አልቁድሲ እንደተገለጸው ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹አላህ፦ ለደጋግ ባሮቼ ዓይን አይቶት የማያውቀውን፣ጆሮም ሰምቶት የማያውቀውንና በሰው ልጅ አእምሮ ውስጥ ታስቦ የማያውቀውን (ድሎት) አዘጋጅቻለሁ፣ብሏል።›› ከፈለጋችሁ፦

(فَلَا تَعۡلَمُ نَفۡسٞ مَّآ أُخۡفِيَ لَهُم مِّن قُرَّةِ أَعۡيُنٖ)

‹‹ከዓይኖች መርጊያ ለነሱ የተደበቀላቸውን (ጸጋ)፣ማንኛይቱም ነፍስ አታውቅም።›› የሚለውን አንብቡ።

(በቡኻሪ የተዘገበ)

የዱንያ ሕይወት የርሱ ﷻ ፍቅርና ለርሱ መታዘዝ ባይኖር ኖሮ፣በጀነትም እርሱን ማየትና መመልከት ባይኖር ኖሮ ባልጣሙ ነበር።

የአላህ ፍቅር ለባሪያው ከሚያስገኛቸው ፍሬዎች መካከል አንዱ እርሱን ﷻ መመልከት ነው ፦

ኃያሉ ጌታ አላህ ﷻ ለሚወዳቸው ባሮቹ በብርሃኑ ይገለጥላቸውና ያዩታል። ከዚያ ይበልጥ የሚወደድ ነገር ፈጽሞ አያዩም። ይህም ነቢዩ ﷺ አንድ ሌሊት ሙሉ ጨረቃን ተመልክተው በተናገሩት ሐዲሥ መሰረት ነው፦

‹‹ይህን ጨረቃ እንደምታዩ ጌታችሁን (በኣኽራ) ታዩታላችሁ፤በማየቱም ላይ መጨናነቅ አይኖርም። ፀሐይ ከመውጣቷና ከመጥለቋ በፊት ከመሰገድ አለመታከት ከቻላችሁ አድርጉ፣ብለው ፦

(وَسَبِّحۡ بِحَمۡدِ رَبِّكَ قَبۡلَ طُلُوعِ ٱلشَّمۡسِ وَقَبۡلَ ٱلۡغُرُوبِ ٣٩)”

‹‹ጌታህንም ከማመስገን ጋር ፀሐይ ከመውጣቷ በፊት፣ከመግባቷም በፊት አወድሰው።›› የሚለውን አነበቡ።

(በቡኻሪ የተዘገበ)

የአላህን ፍቅር የሚመለከቱ ብያኔዎችና ማሳሰቢያዎች፦

1-

አላህ ﷻ ባሪያውን መውደዱ መከራና ፈተናን ከርሱ አይከላከልም። የአላህ መልክተኛﷺ እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹የሽልማትና የምንዳ ክብደትት እንደ ፈተናው ክብደትና ግዝፈት ነው። አላህ ሰዎችን ሲወዳቸው በፈተና ይሞክራቸዋል። ወዶ የተቀበለ ውዴታውን ያገኛል፤የጠላውም ጥላቻውን ያተርፋል።››

(በትርምዚ የተዘገበ)

ከኃጢአት እስኪያጸዳውና ልቡ በዱንያ ከመጠመድ ነጻ እስኪሆን ድረስ አላህ ﷻ ባሪያውን በመከራዎች ይፈትነዋል። አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(وَلَنَبۡلُوَنَّكُمۡ حَتَّىٰ نَعۡلَمَ ٱلۡمُجَٰهِدِينَ مِنكُمۡ وَٱلصَّٰبِرِينَ وَنَبۡلُوَاْ أَخۡبَارَكُمۡ ٣١)

‹‹ከናንተም ታጋዮችንና ታጋሾቹን እስከምናውቅ፣ወሬዎቻችሁንም እስከምንገልጽ ድረስ በእርግጥ እንሞክራችኋለን።››

[ሙሐመድ፡31]

በተጨማሪም አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(وَلَنَبۡلُوَنَّكُم بِشَيۡءٖ مِّنَ ٱلۡخَوۡفِ وَٱلۡجُوعِ وَنَقۡصٖ مِّنَ ٱلۡأَمۡوَٰلِ وَٱلۡأَنفُسِ وَٱلثَّمَرَٰتِۗ وَبَشِّرِ ٱلصَّٰبِرِينَ ١٥٥ ٱلَّذِينَ إِذَآ أَصَٰبَتۡهُم مُّصِيبَةٞ قَالُوٓاْ إِنَّا لِلَّهِ وَإِنَّآ إِلَيۡهِ رَٰجِعُونَ ١٥٦ أُوْلَٰٓئِكَ عَلَيۡهِمۡ صَلَوَٰتٞ مِّن رَّبِّهِمۡ وَرَحۡمَةٞۖ وَأُوْلَٰٓئِكَ هُمُ ٱلۡمُهۡتَدُونَ ١٥٧)

‹ከፍርሃትና ከረኃብምም በጥቂት ነገር፣ከገንዘቦችና ከነፍሶችም ከፍራፍሬዎችም በመቀነስ በእርግጥ እንሞክራችኋለን፣ታጋሾችንም (በገነት) አብስር።››

[አልበቀራህ፡155-157]

2-

ባሪያው የጌታውንﷻ ትእዛዝ ሲጥስ ለአላህ ያለው ውዴታ ይቀንሳል፤ኃጢአቱ ፍቅሩን ጎደሎ ያደርጋል። የአላህ ፍቅር እንደ ኢማን ሁሉ መነሻ መሰረትና ሙላት ያለው ሲሆን፣ምሉእነቱ እንደ ኃጢአቱ ሁኔታ ይቀንሳል። ግለሰቡ ወደ ጥርጣሬና መናፍቅነት ደረጃ ከወረደ፣ስረ መሰረቱ ተነቅሎ ይጠፋል። ልቡ ውስጥ ምንም የአላህ ፍቅር የሌለው ሰው ተቀልባሽ ከሓዲና ከሃይማኖቱ እጣ ፈንታ የሌለው መናፊቅ ነው። ኃጢአን ግን የአላህﷻ ፍቅር በውስጣቸው የለም ማለት አይቻልም፤ለአላህ ያላቸው ፍቅር ጎደሎ ነው ተብለው በዚህ መሰረት ይፈረጃሉ። ነቢዩﷺ እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹እናንተ ኃጢአት የማትሠሩ ብትኾኑ ኖሮ፣አላህ ﷻ ኃጢአት የሚሠሩና ምሕረት የሚያደርግላቸውን ሰዎች በፈጠረ ነበር።››

(በአሕመድ የተዘገበ)

‹‹ነጻነት ማለት የልብ ከሽርክ፣ከስሜታዊ ዝንባሌዎችና ከውዥንብሮች ነጻ መሆን ነው። ተገዥነትና ባርነት ደግሞ የልብ ለአንድ አላህ ብቻ ተገዥና ታዛዥ መሆንና ለሌላ ለማንምና ለምንም ተገዥ አለመሆን ነው።››

3-

አላህን መውደድ የሰው ነፍስ በተፍጥሮ የምታዘነብልባቸውንና ምግብን መጠጥንና ወሲብን የመሳሰሉትን ነገሮች ከመውደድ ጋር አይጻረርም። ነቢዩﷺ እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹ከቅርቢቱ ዓለም ሕይወት ሴቶችና ሽቶ ለእኔ የተወደዱ እንዲሆኑ ተደርገዋል።››

(በአሕመድ የተዘገበ)

ስለዚህም ነቢዩﷺ የወዳዷቸው በመሆኑ በዱንያ ላይ እነሱን ማፍቀር ከሽርክና ከማጋራት ጋር የማይመደብ ነገሮች አሉ ማለት ነው። በዚህም መሰረት ሐራም እስካልሆነ ድረስ አንድ ሰው የዓለማዊ ሕይወት ጉዳዮች የሆኑትን ነገሮች ማፍቀር ይችላል።

4-

አላህን የሚወደውን ያህል ሌላውን የወደደ ሰው፣በአላህ ያጋራ ሙሽሪክ ነው። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(وَمِنَ ٱلنَّاسِ مَن يَتَّخِذُ مِن دُونِ ٱللَّهِ أَندَادٗا يُحِبُّونَهُمۡ كَحُبِّ ٱللَّهِۖ وَٱلَّذِينَ ءَامَنُوٓاْ أَشَدُّ حُبّٗا لِّلَّهِۗ وَلَوۡ يَرَى ٱلَّذِينَ ظَلَمُوٓاْ إِذۡ يَرَوۡنَ ٱلۡعَذَابَ أَنَّ ٱلۡقُوَّةَ لِلَّهِ جَمِيعٗا وَأَنَّ ٱللَّهَ شَدِيدُ ٱلۡعَذَابِ ١٦٥)

‹‹እነዚያ ያመኑትም፣አላህን በመውደድ (ከነርሱ) ይበልጥ የበረቱ ናቸው፤እነዚያም የበደሉት ሰዎች ቅጣትን (በትንሣኤ ቀን) ባዩ ጊዜ፣ኃይል ሁሉ ለአላህ ብቻ መኾኑንና አላህም ቅጣቱ ብርቱ መኾኑን (በአዱኛ ዓለም) ቢያውቁ ኖሮ፣(ባላንጣዎችን በመያዛቸው በተጸጸቱ ነበር)።››

[አልበቀራህ፡165]

በዚህ አንቀጽ በአምልኮና በአክብሮት የአላህን ፍቅር ከሌላ ማናቸውም ፍቅር ጋር እኩል በሚያደርግ ሰው ላይ ብርቱ ማስጠንቀቂያ ተላልፏል።

‹‹ከሥራዎች ሁሉ ይበልጥ አላህ ዘንድ ተወዳጁ ለአላህ ብሎ መውደድና ለአላህም ብሎ መጥላት ነው።›› (በአሕመድ የተዘገበ)

አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(قُلۡ إِن كَانَ ءَابَآؤُكُمۡ وَأَبۡنَآؤُكُمۡ وَإِخۡوَٰنُكُمۡ وَأَزۡوَٰجُكُمۡ وَعَشِيرَتُكُمۡ وَأَمۡوَٰلٌ ٱقۡتَرَفۡتُمُوهَا وَتِجَٰرَةٞ تَخۡشَوۡنَ كَسَادَهَا وَمَسَٰكِنُ تَرۡضَوۡنَهَآ أَحَبَّ إِلَيۡكُم مِّنَ ٱللَّهِ وَرَسُولِهِۦ وَجِهَادٖ فِي سَبِيلِهِۦ فَتَرَبَّصُواْ حَتَّىٰ يَأۡتِيَ ٱللَّهُ بِأَمۡرِهِ)

‹‹፦ አባቶቻችሁና ወንዶች ልጆቻችው፣ወንድሞቻችሁም፣የሰበሰባችኋቸው ሀብቶችም፣መክሰሩዋን የምትፈሩዋት ንግድም፣የምትወዷቸው መኖሪያዎችም፣እናንተ ዘንድ ከአላህና ከመልክተኛው፣በርሱ መንገድም ከመታገል፣ይበልጥ የተወደዱ እንደኾኑ፣አላህ ትእዛዙን እስኪያመጣ ድረስ ተጠባበቁ፣በላቸው፤››

[አልተውባህ፡24]

የተዘረዘሩትን ስምንቱን ነገሮች ከአላህ ይበልጥ ለወደደ ሰው በዚህ አንቀጽ ብርቱ ማስፈራሪያ ተላልፎበታል። ከአነስ በተላለፈው መሰረት የአላህ መልክተኛﷺ እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹እኔ ከልጁ ከአባቱና ከሰዎች ሁሉ ይበልጥ እርሱ ዘንድ የተወደድኩ እስክሆን ድረስ አንዳችሁ (የተሟላ እምነት) አያምንም።››

(በእብን ማጃህ የተዘገበ)

5-

ከምእመናን ሌላ ሙሽሪኮችን መውደድና ረዳቶች አድርጎ መያዝ፣በሙሽሪኩ ሃይማኖትና በማጋራቱ ምክንያት አላህንﷻ ከማፍቀር ጋር ይጻረራል። ለአላህ ብሎ መውደድና ለአላህ ብሎ መጥላት ከኢማን መሠረቶች ውስጥ አንዱ ጽኑ መሰረት ነው። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(لَّا يَتَّخِذِ ٱلۡمُؤۡمِنُونَ ٱلۡكَٰفِرِينَ أَوۡلِيَآءَ مِن دُونِ ٱلۡمُؤۡمِنِينَۖ وَمَن يَفۡعَلۡ ذَٰلِكَ فَلَيۡسَ مِنَ ٱللَّهِ فِي شَيۡءٍ إِلَّآ أَن تَتَّقُواْ مِنۡهُمۡ تُقَىٰةٗ)

‹‹ምእምናን፣ከሓዲዎችን ከምእምናን ሌላ ረዳቶች አድርገው አይያዙ፤ይኸንንም የሚያደርግ ሰው፣ከአላህ (ሃይማኖት) በምንም ውስጥ አይደለም፤ከነርሱ መጠበቅን ብትጠበቁ እንጂ፤››

[ኣል ዒምራን፡28]

በዚህም ምእመናን ከሓዲዎችን የልብ ወዳጆችና ረዳቶች አድርገው እንዳይይዙ ተከልክለዋል። ይህን የሚያደርግ ሰው ከአላህ ሃይማኖት በምንም ውስጥ አይደለም። የሚያፈቅሩትን ማፍቀርና የርሱን ጠላት የሆነውንም ማፍቅር እርስ በርስ የሚጋጩ ነገሮች ናቸው።

(إِلَّآ أَن تَتَّقُواْ مِنۡهُمۡ تُقَىٰةٗ)

‹‹ከነርሱ መጠበቅን ብትጠበቁ እንጂ፤››

[ኣል ዒምራን፡28]

ያንን ካላደረጉ መልካም አብሮነት አይኖርም ብለው ከፈሩ ግን አላህﷻ እነሱን መወዳጀት ፈቅዷል። በዚህ ሁኔታ ልብ በኢማን እንደጸና እና እንደተረጋጋ ክሕደትና ከሓዲዎችን መጥላቱን እንደቀጠለ፣ላይላዩን ብቻ መወዳጀትና መቻቻልን መፍጠር ይፈቀዳል። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(إِلَّا مَنۡ أُكۡرِهَ وَقَلۡبُهُۥ مُطۡمَئِنُّۢ بِٱلۡإِيمَٰنِ)

‹‹ልቡ በእምነት የረጋ ኾኖ (የክሕደት ቃል ለመናገር) የተገደደ ሰው ብቻ ሲቀር፤››

[አልነሕል፡106]

ነቢያችንﷺ በዱንያ ላይ ለዘለዓለም ከመኖርና አላህﷻ ከመገናኘት አንዱን እንዲመርጡ ሲደረጉ፦

‹‹(ምርጫዬ) የላይኛው ጓደኝነት (ከነቢያት ከጻድቃን፣ከሰማዕታትና ከደጋጎቸቹ ጋር መሆን) ነው።››

(በአሕመድ የተዘገበ)

በማለት ነቢዩﷺ ከዱንያ ፍቅርና ከመደሰቻዎቿ በማብለጥና በማስቀደም የአላህን ፍቅርና ከርሱ ጋር መገናኘትን መርጠዋል።

የአላህ ፍቅር ምልክቱ እርሱን በብዛት ማስታወስና ስሙን መዘከር፣ከርሱ ጋር መገናኘትን መናፈቅ ነው። አንድን ነገር ያፈቀረ ሰው አብዝቶና ደጋግሞ የሚያወሳው ሲሆን ከርሱ ጋር መገናኘትንም ይናፍቃል።

ረቢዕ ብን አነስ


ነቢዩﷺ እንዲህ ብለዋል፦ ‹‹ነገሮችን አቅልሉ እንጂ አታካብዱ፣ብስራት ንገሩ እንጂ አታስበርግጉ።›› (በቡኻሪ የተዘገበ)

 

ተስፋ የማድረግ (የረጃእ) ጽንሰ ሀሳብ ፦

ተስፋ ማድረግ ማለት፦

የአላህን የችሮታውንና የርኅራሄውን መኖር መገንዘብ፣ስሜት ማሳደር፣ችሮታና ጸጋዎቹን በመከጀል መደሰት፣በዚህም መተማመን ማለት ነው። ረጃእ ልቦችን ወደ አላህና ወደ ጀነቱ የሚነዳ ሞተር ነው። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

( وَمَن يَعۡمَلۡ سُوٓءًا أَوۡ يَظۡلِمۡ نَفۡسَهُۥ ثُمَّ يَسۡتَغۡفِرِ ٱللَّهَ يَجِدِ ٱللَّهَ غَفُورٗا رَّحِيمٗا ١١٠)

‹‹መጥፎም የሚሠራ ሰው፣ወይም ነፍሱን የሚበድል፣ከዚያም (ተጸጽቶ) አላህን ምሕረትን የሚለምን፣አላህን መሓሪ አዛኝ ኾኖ ያገኘዋል።››

[አልኒሳእ፡110]

የረጃእ ዓይነቶች ፦

ተስፋ ማድረግ (ረጃእ) ሦስት ዓይነት ነው። ሁለቱ ዓይነት የተመሰገኑ ሲሆኑ አንደኛው ዓይነት ግን የተወገዘ መዘናጋትና ራስን መሸንገል ነው።

1-

የአላህን ትእዛዝ በአላህ ብርሃን ተመርቶ በመፈጸም ምንዳውን ተስፋ የሚያደርግ ሰው ረጃእ።

2-

ኃጢአት ሰርቶ በመጸጸት የተመለሰና የአላህን ምሕረት፣ይቅርታውንና የኃጢአቱን መታበስና ከውርደት መዳንን ተስፋ የሚያደርግ ሰው ረጃእ።

3-

የአላህን ትእዛዝ በመጣስ፣በኃጢአት ሥራ፣በእኩይ ተግባራት ላይ መሰማራቱን እየቀጠለ፣የአላህን እዝነትና ምሕረቱን ያለ በጎ ሥራ ተስፋ የሚያደርግ ሰው!! ይህ ራስን መሸንገል፣ከንቱ ተስፋና ባዶ ምኞት ሲሆን፣ፈጽሞ የሚወደስ ተስፋ ሊሆን አይችልም። የምእመናን ተስፋ (ረጃእ) ከተግባር ጋር የተቆራኘ ተስፋ ነው። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(إِنَّ ٱلَّذِينَ ءَامَنُواْ وَٱلَّذِينَ هَاجَرُواْ وَجَٰهَدُواْ فِي سَبِيلِ ٱللَّهِ أُوْلَٰٓئِكَ يَرۡجُونَ رَحۡمَتَ ٱللَّهِۚ وَٱللَّهُ غَفُورٞ رَّحِيمٞ ٢١٨)

‹‹እነዚያ ያመኑትና እነዚያም (ከአገራቸው) የተሰደዱት፣በአላህም መንገድ ላይ የተጋደሉት፣እነዚያ የአላህን እዝነት ይከጅላሉ፤አላህም እጅግ መሓሪ አዛኝ ነው።››

[አልበቀራህ፡218]

እርከኖቹና ደረጃዎቹ ፦

ተስፋ ማድረግ (ረጃእ) ደረጃና እርከኖች ያሉት ሲሆን፣እነሱም የሚከተሉት ናቸው ፦

1-

ለዕባዳና ለጥረት የሚገፋፋ፣ከባድና አስቸጋሪ ቢሆን እንኳ ዕባዳውን ሲያከናውን ባለቤቱ ዘንድ ደሰታና እርካታን በመፍጠር ከኃጢኣቶችና ከእኩይ ነገሮች እንዲርቅ የሚያደርግ ተስፋ።

2-

የነፍስያቸውን ልማዶችና ከፈጣሪያቸው ፍላጎት የሚያዘናጋቸውን ፍላጎቶች ሁሉ በመተውና ልቦቻቸውን ለርሱ አንድ ወጥ በማድረግ ረገድ ትጉሃን አገልጋዮች የሚያሳድሩት ተስፋ (ረጃእ)።

3-

የልቦና ባለቤቶች ተስፋ (ረጃእ) ፦ ይህ ከፈጣሪ አምላክ ጋር መገናኘትን በመናፈቅ፣ልቦናን ለርሱ ብቻ ፍጹም በማድረግ በርሱ ፍቅር የመመሰጥ ተስፋ (ረጃእ) ነው። ይህ ከተስፋ ማደረግ ዓይነቶች ሁሉ በላጩና ከፍተኛው ነው። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(فَمَنْ كَانَ يَرْجُوا لِقَاءَ رَبِّهِ فَلْيَعْمَلْ عَمَلًا صَالِحًا وَلَا يُشْرِكْ بِعِبَادَةِ رَبِّهِ أَحَدًا)

‹‹የጌታውንም መገናኘት የሚፈልግ ሰው፣መልካም ሥራን ይሥራ፤በጌታውም መገዛት አንድንም አያጋራ፣በላቸው።››

[አልከህፍ፡110]

በተጨማሪም አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(مَنْ كَانَ يَرْجُو لِقَاءَ اللَّهِ فَإِنَّ أَجَلَ اللَّهِ لَآَتٍ وَهُوَ السَّمِيعُ الْعَلِيمُ)

‹‹የጌታውንም መገናኘት ተስፋ የሚያደርግ ሰው፣(ይዘጋጅ) የአላህ ቀጠሮ በእርግጥ መጪ ነውና፤እርሱም ሰሚው፣ዐዋቂው ነው።››

[አልዐንከቡት፡5]

አንድን ነገር ለማግኘት ተስፋ የሚያደርግ ሰው አጥብቆ ይፈልገዋል።

ረጃእ አላህንﷻ ፣ስሞቹንና ባሕርያቱን ከማወቅ ጋር ያለው ትስስር ፦

ተስፋ አድራጊ ሙእምን የአላህን ትእዛዛት በፈጸም ላይ የሚተጋ፣የኢማን ግዴታዎችን የሚያከናውን፣አላህﷻ እንዳያጠመው፣ሥራውን ከርሱ እንዲቀበልና ውድቅ እንዳያደርግበት ተስፋ የሚያደርግ፣ምንዳና አጅሩን እጥፍ ድርብ እንዲያደርግለት ተስፋና ምኞቱን በርሱ ላይ የሚጥል ሰው ነው። አላህን፣ስሞቹንና ባሕርያቱን ለማወቅ በጌታው እዝነት ላይ ተስፋ የሚጥል፣ ማድረግ የሚችላቸውን ነገሮች ሁሉ ያደረገ፣የሚገበያየው በጣም አዛኝ፣በጣም አፍቃሪ፣በጣም አመስጋኝ፣ቸር፣ለጋሽ፣መሓሪ፣ርኅሩህ ከሆነ ጌታ ጋር ነው። በዚህች ዓለም ላይ ስጉ ሲሆን ነገ ወደ ጌታው ፊት ሲቀርብ መድህን ለማግኘት ተስፋ ያደርጋል።

የተስፋ ማድረግ (የረጃእ) ፍሬዎች ፦

1-

በበጎ ሥራዎችና በአላህ ትእዛዛት ትግባራ (ጧዓት) ላይ የባለቤቱን ጥረትና ትጋት ያጎለብታል።

2-

ሁኔታዎች የፈለገውን ያህል ቢለዋወጡና አስቸጋሪ ቢሆኑም፣ባለቤቱ የአላህ ትእዛዛት ትግባራን (ጧዓትን) ልማዱ አድርጎ እንዲያዘወትር ያላምደዋል።

3-

ባለቤቱ ፊቱን ዘውትር ወደ አላህ በመመለስ እርሱን በመማጸን፣በመለማመን፣በጸሎቱና በጥሪው ላይ መትጋትን ልማዱ አድርጎ እንዲይዝ ያደርጋል።

4-

ባሪያው ለአላህﷻ ያለውን ተገዥነት፣ድህነቱን፣ፈላጊነቱን፣ከርሱ ችሮታና ከቸርነቱ ለአንዲት ሰከንድ እንኳ መብቃቃት የማይችል መሆኑን ያመለክታል።

5-

ለአላህﷻ መኖር፣ለቸርነቱና ለትሩፋቱ ዕውቀትና እርግጠኝነትን ያስጨብጣል። እርሱﷻ ከሚለመኑት ሁሉ ይበልጥ ቸር፣ከሰጭዎች ሁሉ ይበልጥ አስፍቶ የሚሰጥ፣መልሰው መላልሰው የሚለምኑትንና በርሱ ላይ ተስፋ የጣሉትን ባሮቹን የሚወድ ጌታ ነው።

6-

ተስፋ ማድረግ (ረጃእ) ባሪያውን በአላህ ፍቅር ደጃፍ ላይ እንዲወድቅ በማድረግ ወደ ተሟላ አፍቃሪነት ደረጃ ያደርሰዋል። ተስፋ በጠነከረና ተስፋ ያደረገውን ነገር ባገኘ ቁጥር፣ለጌታው ያለው ፍቅርና አመስጋኝነቱ እየበረታ ይሄዳል። ይህ ከተገዥነት (ዑቡዲይያህ) ግዴታዎችና ከማእዘናቱ አንዱ ነው።

ተስፋ አድራጊው ዘውትር የጌታውን ችሮታ በመከጀል በተስፋና በስጋት ውስጥ ሆኖ ከጌታው በጎውን ይመኛል፣ደግ ደጉን ይጠቃል።

ሙእምን ሰው በጌታው ላይ በጎ ግምት ያሳድርና በጎ በጎውን ይሠራል። አመጸኛ ሰው ግን በጌታው ላይ ክፉ ግምት ያሳድራና ክፉ ክፉውን ይሠራል።

በአላህ ላይ በጎ ግምት ከማሳደር (ሑስን አዝዟን) አንዱ አላህﷻ ወደርሱ የተጠጋውንና በርሱ የተከለለውን ሰው የማይጥለው መሆኑን ማወቅ ነው።

7-

ተስፋ መቋጠር የአላህንﷻ ጸጋዎች በተግባር ወደ ማመስገን ደረጃ እንዲራመድ ስለሚገፋፋው፣ወደ አመስጋኝነት ደረጃ እንዲደርስ ባሪያውን ያበረታታል። ይህ የተገዥነት (የዑቡዲይያህ) ንጥርና አስኳል ነው።

8-

ረጃእ የአላህንﷻ ስሞችና ባሕርያት (አልአስማእ ወስስፋት) ያስተዋውቃል። እርሱ በጣም አዛኙ፣ቸሩ፣ለጋሱ፣ጸሎት ተቀባዩ፣ውቡና ሀብታሙ ጌታﷻ ነው። ምንኛ ኃያል ጌታ!

9-

ረጃእ ባሪያው ተስፋ ያደረገውን ነገር እንዲያገኝ ምክንያት ይሆናል። የተመኙትን ማግኘት ተጨማሪ ለመጠየቅና ለማግኘት ፊቱን ወደ አላህ እንዲመለስ ያደፋፍረዋል። በዚህ መልኩ ኢማኑና ወደ አላህ ያለው ቀረቤታ እየጨመረ መሄዱን ይቀጥላል።

10-

ምእመናን በትንሣኤ ቀን የተመኙትን የአላህ ውዴታ (ሪዷ) ጀነቱንና ወደርሱ ፊት መመልከትን ታድለው የሚደሰቱት፣በዱንያ ዓለም ሕይወታቸው በአላህﷻ ላይ በጣሉት ተስፋ (ረጃእ) እና ለርሱ ባላቸው ፍራቻ ልክ ነው።

ረጃእን የሚመለከቱ ብያኔዎችና ማሳሰቢያዎች ፦

1-

በሙእምኑ ዘንድ ፍራቻ (ኸውፍ) ከተስፋ ማድረግ (ከረጃእ) ጋር የተጎዳኘ ነው። ለዚህ ነው የፍራቻ መኖር መልካም በሆነበት ሁሉ ተስፋ ማድረግ (ረጃእ) መኖሩ መልካም የሆነው ፦

(مَّا لَكُمۡ لَا تَرۡجُونَ لِلَّهِ وَقَارٗا ١٣ )

‹‹ለአላህ ልቅናን የማትሹት ለናንተ ምን አላችሁ።››

[ኑሕ፡13]

በተጨማሪም አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(قُل لِّلَّذِينَ ءَامَنُواْ يَغۡفِرُواْ لِلَّذِينَ لَا يَرۡجُونَ أَيَّامَ ٱللَّهِ)

‹‹ለነዚያ ለአመኑት ሰዎች (ምሕረት አድርጉ)፣በላቸው፤ለነዚያ የአላህን ቀኖች ለማይፈሩት ይምራሉና፣››

[አልጃሢያ፡14]

ከነሱ በፊት በነበሩት ሕዝቦች ላይ የደረሰውን ዓይነት ጥፋትና ውድመት አላህ ያደርስብናል ብለው አይፈሩም ማለት ነው።

2-

ተስፋ ማድረግ (ረጃእ) በሚከተሉት ሁኔታዎች የምንፈልገው መድኃኒት ነው ፦

- ነፍስያ ቀቢጠ ተስፋ መሆን አይሎባት ዕባዳ በምትተውበት ጊዜ።

- ፍርሃቱ ከተፈላጊው ሸሪዓዊ ገደብ አልፎ፣አንድ ሰው ራሱንና ቤተሰቡን ለአደጋ እስከማጋለጥ ድረስ በፍርሃት ቁጥጥር ስር ሲሆን። በዚህ ጊዜ ሁኔታውን መለወጥና ሚዛን የሚያስጠብቅ ነገር እንዲሰነቅ ማድረግ ግድ ይላል። ያም በሙእምኑ ዘንድ የተለመደው ተፈጥሯዊ ሁኔታ የሆነውን ተስፋ (ረጃእ) መሰነቅ ነው።

3-

ተስፋ ማድረግ (ረጃእ) የቀቢጠ ተስፋ ተቃራኒ ነው። ተስፋ መቁረጥ የአላህ እዝነት ማምለጡን ማስታወስ፣ርኅራሄውን ከመሻት መቋረጥ ሲሆን፣ይህን ማድረግ የኩፍርና የጥመት መንስኤ ነው። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(وَلَا تَاْيۡئسُواْ مِن رَّوۡحِ ٱللَّهِۖ إِنَّهُۥ لَا يَاْيۡئسُ مِن رَّوۡحِ ٱللَّهِ إِلَّا ٱلۡقَوۡمُ ٱلۡكَٰفِرُونَ ٨٧)

‹‹ከአላህም እዝነት ተስፋ አትቁረጡ፤እነሆ ከአላህ እዝነት ከሐዲዎች ሕዝቦች እንጂ ተስፋ አይቆርጥም (አለ)።››

[ዩሱፍ፡87]

ሚዛን ቀርቦ የአንድ ሙእምን ተስፋና ፍርሃቱ ቢመዘን ሁለቱ እኩልና ተመጣጣኝ ይሆኑ ነበር።

የእኔ ምርመራ በወላጅ አባቴ እጅ እንዲሆን አልሻም፤ጌታዬ ከአባቴ ይሻለኛልና።

ኢማም ሱፍያን አሥሠውሪ

ዕባዳ በፍርሃትና በተስፋ (ረጃእ) ማድረግ እንጂ ሊከናወን አይችልም። አማኙ በፍርሃት ከተከለከሉ ነገሮች ይታቀባል፤በተስፋ ደግሞ የትእዛዛትን ትግበራዎች (ጧዓት) ያበዛል።

ኢማም እብን ከሢር


(وَيُحَذِّرُكُمُ ٱللَّهُ نَفۡسَهُ) [آل عمران: 30]

 

‹‹አላህ ነፍሱን ያስጠነቅቃችኋል።›› [ኣል ዒምራን፡30]

የፍርሃት (ኸውፍ) ጽንሰ ሀሳብ ፦

አላህን መፍራት ከታላላቅ የልቦና ዕባዳዎች አንዱ ነው። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(إِنَّمَا ذَٰلِكُمُ ٱلشَّيۡطَٰنُ يُخَوِّفُ أَوۡلِيَآءَهُۥ فَلَا تَخَافُوهُمۡ وَخَافُونِ إِن كُنتُم مُّؤۡمِنِينَ ١٧٥)

‹‹ይሃችሁ፣ሰይጣን ብቻ ነው፣ወዳጆቹን ያስፈራራችኋል፤አትፍሩዋቸውም፤ምእምናንም እንደኾናችሁ ፍሩኝ።››

[ኣል ዒምራን፡175]

ከዚህ አንቀጽ አንድ አላህን ብቻ መፍራት ግዴታ መሆኑን፣ለኢማን መሟላት ካለባቸው ነገሮችም አንዱ መሆኑ በአጽንኦት ተገልጿል። አንድ ሰው አላህን የሚፈራው በኢማኑ ጥንካሬ መጠን ነው።

እመ ምእመናን ዓእሻ (ረ.ዐ) እንዲህ ብለዋል ፦

ነቢዩንﷺ ስለዚህ አንቀጽ ጠየቅኋቸው ፦

(وَٱلَّذِينَ يُؤۡتُونَ مَآ ءَاتَواْ وَّقُلُوبُهُمۡ وَجِلَةٌ)؛

‹‹እነዚያም የሚሰጡትን ነገር እነርሱ ወደ ጌታቸው ተመላሾች መኾናቸውን፣ልቦቻቸው የሚፈሩ ኾነው የሚሰጡት።››

እነዚህ አስካሪ መጠጥ የሚጠጡና የሚሰርቁ ናቸውን?! ‹‹የአስሲድዲቅ ልጅ ሆይ! አይደሉም፤ግና እነዚያ ተቀባይነት እንዳያጡ እየፈሩና እየሰጉ የሚጾሙ፣የሚሰግዱና ምጽዋት የሚሰጡ ናቸው›› አሉ።

(በትርምዚ የተዘገበ)

አላህንﷻ ለመፍራት የሚገፋፉ ነገሮች ፦

1-

ስሞቹንና ባሕርያቱን አስመልክቶ በሚኖር ዕውቀት ምክንያት፣ለኃያልነቱና ለግርማ ሞገሱ ተገቢ በሆነ ሁኔታ አላህንﷻ ማክበርና ማላቅ።

(يَخَافُونَ رَبَّهُم مِّن فَوۡقِهِمۡ)

‹‹‹ጌታቸውን ከበላያቸው ሲኾን ይፈሩታል፤››

[አልነሕል፡50]

2-

የፍጻሜው መጨረሻ ወደሚጠላውና ወደ አስከፊው አሳማሚ የገነም እሳት እንዳይሆን መፍራት ።

3-

ሙእምን ሰው አላህﷻ ነገሩን ሁሉ የሚያይና በዝርዝር የሚያውቀው መሆኑን፣በርሱ ላይም ፍጹማዊ ሥልጣን ያለው መሆኑን መገንዘብ፣ያሉበትን ግዴታዎች በመወጣት ረገድ ተገቢውን ያደረጉ የመሆንን ስሜት ሁሌም ማሳደር። ጥፋት ከፈጸመበት ኃያል ፈጣሪ ታላቅነት አንጻር የተፈጸመውን ጥፋትም አቅልሎ አለመመልከት።

4-

በርሱ ላይ ባመጸና ከሸሪዓው ባፈነገጠ፣ወደርሱ የተላከውን ብርሃን ችላ ባለ ሰው ላይ በተላለፈ ማስጠንቀቂያና ማስፈራሪያ የተሞላውን የአላህንﷻ ንግግር አስተውሎ ማስተንተን።

5-

ቁርኣንና የነቢዩን ሐዲሥ አስተውሎ መረዳትና የነቢዩንﷺ የሕይወት ታሪክ (ሲራ) ማጥናት።

6-

የ አላህንﷻ ኃያልነት ማሰብ ማሰላሰልና ማስተንተን። ይህን አስተንትኖ ያስተዋለ ሰው፣የላቁ ባሕርያቱን (ስፋቱን)፣ግርማ ሞገሱንና ኃያልነቱን ይረዳል። ልቡ የአላህንﷻ ኃያልነትና ግርማ ሞገሱን የመሰከረ ሰውም፣የርሱ ማስጠንቀቂያና ማስፈራሪያ ምን ማለት እንደሆነ የግድ ይገነዘባል። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(وَيُحَذِّرُكُمُ ٱللَّهُ نَفۡسَهُۥ)

‹‹አላህ ነፍሱን ያስጠነቅቃችኋል።››

[ኣል ዒምራን፡28]

አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(وَمَا قَدَرُواْ ٱللَّهَ حَقَّ قَدۡرِهِۦ وَٱلۡأَرۡضُ جَمِيعٗا قَبۡضَتُهُۥ يَوۡمَ ٱلۡقِيَٰمَةِ وَٱلسَّمَٰوَٰتُ مَطۡوِيَّٰتُۢ بِيَمِينِهِ)

‹‹አላህንም በትንሣኤ ቀን ምድር በመላ (አንድ) ጭብጡ ስትኾን፤ሰማያትም በኃይሉ የሚጠቀለሉ ሲኾኑ፣(ከርሱ ጋር ሌላን በማጋራታቸው) ተገቢ ክብሩን አላከበሩትም።››

[አልዙመር፡67]

አላህን መፍራት እርሱን ማወቅ ያስከትላል። እርሱን ማወቅ ደግሞ እረሱን መስጋት ያስከትላል። ቅጣቱንና ማስጠንቀቂያውን መስጋት ደግሞ ለርሱ ተገዥና ታዛዥ መሆንን ያስገኛል።

7-

ሞትና ጭንቁን፣ደራሽና አይቀሬ መሆኑን ማሰብና ማስተንተን ፦

(قُلۡ إِنَّ ٱلۡمَوۡتَ ٱلَّذِي تَفِرُّونَ مِنۡهُ فَإِنَّهُۥ مُلَٰقِيكُمۡ)

‹‹ያ ከርሱ የምትሸሹት ሞት እርሱ በእርግጥ አግኛችሁ ነው፤››

[አልጁሙዓህ፡8]

ሞት ለአላህ ያለንን ፍራቻ ይጨምራል። ነቢዩﷺ ከእንዲህ ብለዋል፦

‹‹የደስታና የእርካታዎችን ቆራጭ (ሞትን) ማስታወስ አብዙ፤በጭንቅ ኑሮ ላይ ሆኖ ያስታወሰው ማንኛውም ሰው (ኑሮው) ይሰፋለታል፤በድሎት ላይ ሆኖ ያስታወሰው ማንኛውም ሰው ደግሞ (ምንም ቢደላው ድሎቱን) ይጠብበታል።››

(በጠበራኒ የተዘገበ)

8-

ከሞት በኋላ ያሉትን ነገሮች፣መቃብርንና በውስጡ ያሉ አስበርጋጊ ሁኔታዎችን ማሰብና ማስተንተን። ነቢዩﷺ እንዲህ ብለዋል፦

‹‹መቃብሮችን ከመጎብኘት ከልክያችሁ ነበር፣ኣኽራን (የወዲያኛውን ዓለም) ስለሚያስታውሷችሁ ጎብኟቸው፡››

(በእብን ማጃህ የተዘገበ)

በራእ  የሞከተለውን አስተላልፈዋል፦

‹‹በአንድ የቀብር ስነ ሥርዓት ላይ ከአላህ መልክተኛﷺ ጋር ነበርን፤በመቃብሩ አፋፍ ላይ ተቀመጡና አፈሩ እስኪረጥብ ድረስ አለቀሱ፤ከዚያም፦ ወንድሞቼ ሆይ! ለእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ራሳችሁን አዘጋጁ፣አሉን።››

(በእብን ማጃህ የተዘገበ)

አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(يَٰٓأَيُّهَا ٱلنَّاسُ ٱتَّقُواْ رَبَّكُمۡ وَٱخۡشَوۡاْ يَوۡمٗا لَّا يَجۡزِي وَالِدٌ عَن وَلَدِهِۦ وَلَا مَوۡلُودٌ هُوَ جَازٍ عَن وَالِدِهِۦ شَيًۡٔاۚ إِنَّ وَعۡدَ ٱللَّهِ حَقّٞۖ فَلَا تَغُرَّنَّكُمُ ٱلۡحَيَوٰةُ ٱلدُّنۡيَا وَلَا يَغُرَّنَّكُم بِٱللَّهِ ٱلۡغَرُورُ ٣٣)

‹‹እላንተ ሰዎች ሆይ! ጌታችሁን ፍሩ፤ወላጅም ከልጁ (በምንም) የማይጠቅምበትን፣ተወላጅም እርሱ ወላጅን በምንም ጠቃሚ የማይኾንበትን ቀን ፍሩ፤የአላህ ቀጠሮ እውነት ነውና፤ቅርቢቱም ሕይወት አትሸንግላችሁ፤በአላህም (መታገስ) አታላዩ (ሰይጣን) አያታላችሁ።››

[ሉቅማን፡33]

9-

ሰዎች አሳንሰው የሚመለከቷቸው ጥቃቅን ኃጢአቶች ውጤት ምን ሊሆን እንደሚችል ማሰብና ማስተነትን። ነቢዩﷺ ጉዳዩን በምሳሌ አስቀምጠውልናል። የሰዎች ስብስብ አንድ ሸለቆ ላይ ሰፈረሩና እያንዳንዱ ሰው አንዳንድ እንጨት አምጥቶ ምግባቸውን ማብሰል የሚያስችል ማገዶ መሰብሰብ ቻሉ። ጥቃቅን እንጨቶች ተሰብስበው ምግቡን እንዳበሰሉ ሁሉ፣ጥቃቅን ኃጢአቶችም ተሰብስበው የኃጢአንን ገላ በገሀነም እሳት ያቃጥላሉ ፦

(كُلَّمَا نَضِجَتۡ جُلُودُهُم)

‹‹ቆዳዎቻቸው በተቃጠሉ ቁጥር ሌሎችን ቆዳዎች እንለውጥላቸዋለን፤››

[አልኒሳእ፡56]

10-

አንድ የአላህ ባሪያ በኃጢአቱ ተጸጽቶ ተውበት ከማድረጉ በፊት በድንገተኛ ሞት ሊቀደም እንዲችል ማወቅ ይኖርበታል። ጊዜው ካለፈ በኋላ መጸጸት ጥቅም የለውም። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(حَتَّىٰٓ إِذَا جَآءَ أَحَدَهُمُ ٱلۡمَوۡتُ قَالَ رَبِّ ٱرۡجِعُونِ ٩٩)

‹‹አንዳቸውንም ሞት በመጣባቸው ጊዜ፣እንዲህ ይላል፦ ጌታዬ ሆይ! (ወደ ምድረ ዓለም) መልሱኝ፤››

[አልሙእሚኑን፡99]

በተጨማሪም አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(وَأَنذِرۡهُمۡ يَوۡمَ ٱلۡحَسۡرَةِ)

‹‹የቁጭቱን ቀን አስፈራራቸው።››

[መርየም፡39]

11-

ክፉ ፍጻሜን (ሱኡል ኃትማ) ማሰብና ማስተንተን። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(ٱلۡمَلَٰٓئِكَةُ يَضۡرِبُونَ وُجُوهَهُمۡ وَأَدۡبَٰرَهُمۡ)

‹‹መላእክት ፊቶቻቸውንና ጀርቦቻቸውን እየመቱ . . ››

[አልአንፋል፡50]

12-

ፈሪሃ አላህ እንዲያድርብህና እርሱን እንድትፈራ ከሚያደርጉህ ሰዎች ጋር መቀመጥ። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(وَٱصۡبِرۡ نَفۡسَكَ مَعَ ٱلَّذِينَ يَدۡعُونَ رَبَّهُم بِٱلۡغَدَوٰةِ وَٱلۡعَشِيِّ يُرِيدُونَ وَجۡهَهُۥ)

‹‹ነፍስህንም፣ከነዚያ ጌታቸውን ፊቱን (ውዴታውን) የሚሹ ኾነው በጧትና በማታ ከሚግገዙት ጋር አስታግስ፤››

[አልከህፍ፡28]

አላህን መፍራት ከሁለት ነገሮች ጋር የተያያዘ ነው ፦

ሀ- ቅጣቱን ከመፍራት ፦

ይህ ከርሱ ጋር ሌላን ለአጋራው፣ኃጢአት ለፈጸመውና በትእዛዛቱ ላይ ላመጸው የተሰናዳውን አስከፊ ቅጣቱን መፍራት ነው።

ለ- አላህን ከመፍራት ፦

ይህ ደግሞ ዓሊሞችና እርሱን ያወቁ ጻድቃን ባሮቹ የሚፈሩት የፍርሃት ዓይነት ነው ፦

(وَيُحَذِّرُكُمُ ٱللَّهُ نَفۡسَهُ)

‹‹አላህ ነፍሱን ያስጠነቅቃችኋል።››

[ኣል ዒምራን፡28]

ስለ አላህﷻ የሚኖረው ዕውቀት በጨመረ ቁጥር እርሱን መፍራትም እየጨመረ ይሄዳል። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(إِنَّمَا يَخۡشَى ٱللَّهَ مِنۡ عِبَادِهِ ٱلۡعُلَمَٰٓؤُاْ)

‹‹አላህን ከባሮቹ ውስጥ የሚፈሩት፣ዐዋቂዎቹ ብቻ ናቸው፤››

[ፋጢር፡28]

ለጌታቸው ለአላህﷻ ፣ለስሞቹና ለባሕርያቱ ያላቸው ዕውቀት የተሟላ በሚሆንበት ጊዜ፣ከምንም በላይ እርሱን መፍራት ስለሚመርጡ ተጽእኖውና አሻራው በአካላዊ ድርጊቶች ላይ አርፎ ይስተዋላል።

የአላህ ፍርሃት ልብ ውስጥ ከሰፈረ፣የስሜታዊ ዝንባሌዎችንና የቁሳዊ ፍላጎቶችን ሰፈሮች አቃጥሎ ዱንያን ከልብ ያስወጣል።

አላህን መፍራት ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች መካከል የሚከተሉት ይገኛሉ ፦

ሀ- በቅርቢቱ የዱንያ ሕይወት ፦

1-

በምድር ላይ መመቻቸትን ከሚያመጡ፣ ኢማንን ከሚያፋፉና መረጋጋትን ከሚያስገኙ ምክንያቶች አንዱ ነው። ቃል የተገባ ነገር ተፈጽሞ ሲገኝ መተማመንን ይጨምራል። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(وَقَالَ ٱلَّذِينَ كَفَرُواْ لِرُسُلِهِمۡ لَنُخۡرِجَنَّكُم مِّنۡ أَرۡضِنَآ أَوۡ لَتَعُودُنَّ فِي مِلَّتِنَاۖ فَأَوۡحَىٰٓ إِلَيۡهِمۡ رَبُّهُمۡ لَنُهۡلِكَنَّ ٱلظَّٰلِمِينَ ١٣ وَلَنُسۡكِنَنَّكُمُ ٱلۡأَرۡضَ مِنۢ بَعۡدِهِمۡۚ ذَٰلِكَ لِمَنۡ خَافَ مَقَامِي وَخَافَ وَعِيدِ ١٤)

‹‹እነዚያም የካዱት፣ለመልክተኞቻቸው ፦ ከምድራችን በእርግጥ እናወጣችኋለን፤ወይም ወደ ሃይማኖታችን በእርግጥ ትመለሳላችሁ፣አሉ፤ወደነርሱም ጌታቸው እንዲህ ሲል ላከ ፦ ከሓዲዎችን በእርግጥ እናጠፋለን። ከነሱም በኋላ ምድሪቱን በእርግጥ እናስቀምጣችኋለን፤ይኸ በፊቴ መቆሙን ለሚፈራ፣ዛቻየንም ለሚፈራ ሰው ነው።››

[ኢብራሂም፡13-14]

2-

በበጎ ሥራዎችና በልቦና ፍጹምነት (እኽላስ) ላይ ያበረታታል። የኣኽራው ታላቅ ምንዳ ሳይቀንስ በዱንያ ላይ መካካሻ ያለመፈለግ ተነሳሽነትን ያነቃቃል። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(إِنَّمَا نُطۡعِمُكُمۡ لِوَجۡهِ ٱللَّهِ لَا نُرِيدُ مِنكُمۡ جَزَآءٗ وَلَا شُكُورًا ٩ إِنَّا نَخَافُ مِن رَّبِّنَا يَوۡمًا عَبُوسٗا قَمۡطَرِيرٗا ١٠)

‹‹የምናበላችሁ ለአላህ ውዴታ ብቻ ነው፤ከናንተ ዋጋንም ማመስገንንም አንፈልግም። እኛ (ፊትን) የሚያጨፈግግን ብርቱ ቀን ከጌታችን እንፈራለንና፤(ይላሉ)።››

[አልደህር፡9-10]

በተጨማሪም አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(فِي بُيُوتٍ أَذِنَ ٱللَّهُ أَن تُرۡفَعَ وَيُذۡكَرَ فِيهَا ٱسۡمُهُۥ يُسَبِّحُ لَهُۥ فِيهَا بِٱلۡغُدُوِّ وَٱلۡأٓصَالِ ٣٦ رِجَالٞ لَّا تُلۡهِيهِمۡ تِجَٰرَةٞ وَلَا بَيۡعٌ عَن ذِكۡرِ ٱللَّهِ وَإِقَامِ ٱلصَّلَوٰةِ وَإِيتَآءِ ٱلزَّكَوٰةِ يَخَافُونَ يَوۡمٗا تَتَقَلَّبُ فِيهِ ٱلۡقُلُوبُ وَٱلۡأَبۡصَٰرُ ٣٧)

‹‹አላህ እንድትከበርና ስሙ በውስጧ እንዲወሳ ባዘዘው ቤቶች ውስጥ፣(አወድሱት)፤በውስጧ፣በጧትና በማታ ለርሱ ያጠራሉ፣አላህን ከማውሳትና ሶላትን ከመስገድ፣ዘካንም ከመስጠት፣ንግድም ሽያጭም የማያታልላቸው፣ልቦችና ዓይኖች በርሱ የሚገለባበጡበትን ቀን የሚፈሩ የኾኑ ሰዎች፣(ያጠሩታል)።››

[አልኑር፡36]

ልቦችና ዓይኖች በርሱ የሚገለባበጡበትን ቀን የሚፈሩ መሆናቸው፣መድህን እንዲፈልጉ፣አስፈሪውን ቀን እንዲጠነቀቁና መዝገባቸውን በግራ እንዳይቀበሉ በመስጋት ለበጎ ሥራ እንዲነሳሱ አድርጓቸዋል።

የአላህ ፍርሃት ልብ ውስጥ ከሰፈረ የስሜታዊ ዝንባሌዎችንና የቁሳዊ ፍላጎቶችን ሰፈሮች አቃጥሎ ዱንያን ከልብ ያስወጣል።

አላህን የፈራ ሰው ፍርሃቱ ወደ በጎ ነገር ሁሉ ይመራዋል።

ለ- በወዲያኛው የኣኽራ ሕይወት ፦

1-

ባሪያው በትንሣኤ ቀን በአላህንﷻ ዙፋን (ዐርሽ) ጥላ ስር ይሆናል። የአላህ መልክተኛﷺ እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹ማዕረግና ቁንጅና ያላት ሴት (ለዝሙት) ጠይቃው፣እኔ አላህን እፈራለሁ ያለ ሰው፣ . . . ››

(በቡኻሪ የተዘገበ)

ከሐዲሡ በግልጽ የምንረዳው ሴቲቱን ከተግባሯ ለመገሰጽና ራሱንም ለመምከር በአንደበቱ የተናገረ መሆኑን ነው። መርሁን ካወጀ በኋላ በአቋሙ ጸንቶ ገፍቶ የቀጠለ መሆኑንም እንገነዘባለን።

‹‹(ሌላው) ለብቻው ሆኖ አላህን አስታውሶ ዓይኖቹ ያነቡ ሰው ነው . . .››

(በቡኻሪ የተዘገበ)

ዓይኖችን እንዲያለቅሱ ያደረገ የአላህ ፍራቻ በትንሣኤ ቀን ዓይኑ በጀሀነም እሳት እንዳትነካ ያደርጋል ማለት ነው።

2-

ከአላህﷻ ምሕረት ለማግኘት ምክንያት ነው። ለዚህ ማስረጃው ቀጣዩ የነቢዩﷺ ሐዲሥ ነው ፦

‹‹ከናንተ በፊት በነበሩት ሕዝቦች ውስጥ አላህ ሀብት የሰጠው አንድ ሰው ነበር። ለሞት ሲያጣጥር ለወንዶች ልጆቹ እንዲህ አለ ፦ እንዴት ያለ አባት ነበርኩ? ምርጥ አባት ነበርክ፣አሉት። እኔ ፈጽሞ መልካም ነገር ሠርቼ አላውቅምና ሲሞት ሬሳዬን አቃጥሉ፤ከዚያም አድቅቃችሁ ፍጩኝ፤ከዚያም በነፋሻ ቀን አመዴን አየር ላይ በትኑት፣አላቸው። ያላቸውን ፈጸሙ። አላህﷻ ሰበሰበውና ፦ ይህን እንድታደርግ ያደረገህ ምንድን ነው? አለው። የአንተ ፍራቻ ነው አለ፤(አላህም) በርኅራሄው ተቀበለው።››

(በቡኻሪ የተዘገበ)

አላህﷻ አለአዋቂነቱን አይቶ ምክንያቱን ተቀብሎት፣ጌታውን መፍራቱም አማላጅ ሆነው እንጂ ዳግም ከሞት መቀስቀስን የሚክድ ሰው ካፍር ነው።

3-

አላህን መፍራት ባለቤቱን ወደ ጀነት ያደርሳል። ነቢዩﷺ እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹የፈራ ሰው በሌሊቱ መመጀመሪያ ላይ ጉዞ ይጀምራል፤በሌሊቱ መመጀመሪያ ላይ የተጓዘም ካሰበበት ይደርሳል፤ንቁ! የአላህ ወረት (ዕቃ) ውድ ነው፤ንቁ! የአላህ ወረት (ዕቃ) ጀነት ነው።››

(በትርምዚ የተዘገበ)

4-

በትንሣኤ ቀን ጸጥታና መረጋጋትን ማግኘት። አላህﷻ ሐዲሥ አልቁድሲ ውስጥ እንዲህ ብሏል ፦

‹‹በኃያልነቴ ይሁንብኝ በባሪዬ ላይ ሁለት ፍርሃቶችንና ሁለት ጸጥታዎችን አላጣምርበትም፤በዱንያ ላይ ከፈራኝ በትንሣኤ ቀን ጸጥታና ደህንነት እሰጠዋለሁ፤በዱንያ ላይ የኔን አዘናግቶ መያዝ ያልፈራ ከሆነ ግን በትንሣኤ ቀን አስፈራዋለሁ።››

(በበይሀቂ የተዘገበ)

5-

አላህንﷻ በክብር ከገለጻቸው ትጉሃን ምእመናን አገልጋዮቹ ተርታ መቀላቀል። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(إِنَّ ٱلۡمُسۡلِمِينَ وَٱلۡمُسۡلِمَٰتِ وَٱلۡمُؤۡمِنِينَ وَٱلۡمُؤۡمِنَٰتِ وَٱلۡقَٰنِتِينَ وَٱلۡقَٰنِتَٰتِ وَٱلصَّٰدِقِينَ وَٱلصَّٰدِقَٰتِ وَٱلصَّٰبِرِينَ وَٱلصَّٰبِرَٰتِ وَٱلۡخَٰشِعِينَ وَٱلۡخَٰشِعَٰتِ وَٱلۡمُتَصَدِّقِينَ وَٱلۡمُتَصَدِّقَٰتِ وَٱلصَّٰٓئِمِينَ وَٱلصَّٰٓئِمَٰتِ وَٱلۡحَٰفِظِينَ فُرُوجَهُمۡ وَٱلۡحَٰفِظَٰتِ)

‹‹ሙስሊሞች ወንዶችና ሙስሊሞች ሴቶች፣ምእምናንና ምእምናትም፣ታዛዦች ወንዶችና ታዛዦች ሴቶችም፣እውነተኞች ወንዶችና እውነተኞች ሴቶችም፣ታጋሾች ወንዶችና ታጋሾች ሴቶችም፣አላህን ፈሪዎች ወንዶችና አላህን ፈሪዎች ሴቶችም፣መጽዋቾች ወንዶችና መጽዋቾች ሴቶችም፣ጿሚዎች ወንዶችና ጿሚዎች ሴቶችም፣(ካልተፈቀደ ሥራ) ብልቶቻቸውን ጠባቂዎች ወንዶችና ብልቶቻቸውን ጠባቂ ሴቶችም፣››

[አልአሕዛብ፡35]

እነዚህ ባሕርያት በነሱ ለመገለጽ ሁሉም ሰው መትጋት ያለበት ክቡር ባሕርያት ናቸው።

አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(تَتَجَافَىٰ جُنُوبُهُمۡ عَنِ ٱلۡمَضَاجِعِ يَدۡعُونَ رَبَّهُمۡ خَوۡفٗا وَطَمَعٗا وَمِمَّا رَزَقۡنَٰهُمۡ يُنفِقُونَ ١٦ فَلَا تَعۡلَمُ نَفۡسٞ مَّآ أُخۡفِيَ لَهُم مِّن قُرَّةِ أَعۡيُنٖ جَزَآءَۢ بِمَا كَانُواْ يَعۡمَلُونَ ١٧)

‹‹ጌታቸውን ለመፍራትና ለመከጀል የሚጠሩት ኾነው፣ጎኖቻቸው ከመጋደሚያ ስፍራዎች ይራራቃሉ፤ከሰጠናቸውም (ጸጋ) ይለገሳሉ። ይሠሩትም በነበሩት ለመመንዳት፣ከዓይኖች መርጊያ ለነሱ የተደበቀላቸውን (ጸጋ)፣ማንኛይቱም ነፍስ አታውቅም።››

[አልሰጅዳህ፡16]

በተጨማሪም አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(أَمَّنۡ هُوَ قَٰنِتٌ ءَانَآءَ ٱلَّيۡلِ سَاجِدٗا وَقَآئِمٗا يَحۡذَرُ ٱلۡأٓخِرَةَ وَيَرۡجُواْ رَحۡمَةَ رَبِّهِۦۗ قُلۡ هَلۡ يَسۡتَوِي ٱلَّذِينَ يَعۡلَمُونَ وَٱلَّذِينَ لَا يَعۡلَمُونَۗ إِنَّمَا يَتَذَكَّرُ أُوْلُواْ ٱلۡأَلۡبَٰبِ ٩)

‹‹እርሱ የመጨረሻይቱን ዓለም (ቅጣት) የሚፈራ፣የጌታውንም ችሮታ የሚከጅል ሲኾን፣በሌሊት ሰዓቶች ሰጋጅና ቋሚ ኾኖ ለጌታው የሚግገዛ ሰው፣(እንደ ተስፋ ቢሱ ከሓዲ ነውን? በለው)፤እነዚያ የሚያውቁና እነዚያ የማያውቁ ይተካከላሉን? በላቸው፤የሚገነዘቡት ባለ አእምሮዎቹ ብቻ ናቸው።››

[አልዙመር፡9]

አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(وَٱلَّذِينَ هُم مِّنۡ عَذَابِ رَبِّهِم مُّشۡفِقُونَ ٢٧ إِنَّ عَذَابَ رَبِّهِمۡ غَيۡرُ مَأۡمُونٖ ٢٨)

‹‹እነዚያ እነሱ ከጌታቸው ቅጣት ፈሪዎች የኾኑት። የጌታቸው ቅጣት (መምጣቱ) የማያስተማምን ነውና።››

[አልመዓሪጅ፡27-28]

አላህንﷻ ከአገልጋዮቹ ሁሉ ይበልጥ ቅርቡ የሆኑትን ነቢያት፣እርሱን የሚፈሩት በመሆናቸው አወድሷቸዋል ፦

(إِنَّهُمۡ كَانُواْ يُسَٰرِعُونَ فِي ٱلۡخَيۡرَٰتِ وَيَدۡعُونَنَا رَغَبٗا وَرَهَبٗا)

‹‹እነሱ በበጎ ሥራዎች የሚቻኮሉ፣ከጃዮችና ፈሪዎች ኾነው የሚለምኑንም፣ነበሩ፤ለኛ ተዋራጆችም ነበሩ፤››

[አልአንቢያ፡90]

መላእክትም ጭምር ጌታቸውን ይፈራሉ። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(يَخَافُونَ رَبَّهُم مِّن فَوۡقِهِمۡ وَيَفۡعَلُونَ مَا يُؤۡمَرُونَ۩ ٥٠)

‹‹ጌታቸውን ከበላያቸው ሲኾን ይፈሩታል፤የታዘዙትንም ሁሉ ይሠራሉ።››

[አልነሕል፡50]

6-

የአላህንﷻ ውዴታ ማግኘት። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(رَّضِيَ ٱللَّهُ عَنۡهُمۡ وَرَضُواْ عَنۡهُۚ ذَٰلِكَ لِمَنۡ خَشِيَ رَبَّهُۥ ٨)

‹‹አላህ ከነሱ ወደደ፤ከርሱም ወደዱ፤ይህ ጌታውን ለፈራ ሰው ነው።››

[አልበይናህ፡8]

አላህንﷻ የሚያውቁ ትጉሃን አገልጋዮች ፍርሃት

አላህንﷻ ከሌሎች ይበልጥ የሚያውቁ ትጉሃን አገልጋዮች፣ካላቸው በጎ ሥራና ጥልቅ ተስፋ (ረጃእ) ጋር ከማንም በላይ አብዝተው ይፈሩታል። ይህን ከሚያሳዩ ምሳሌዎች የሚከተሉትን እናገኛለን ፦

-

ነቢዩﷺ ቆመው በመስገድ ላይ እያሉ፣ከተከበረው ደረታቸው ውስጥ ከማልቀስ ብዛት የድስት መንተክተክን የሚመስል ድምጽ እስኪሰማ ድረስ ማልቀሳቸው። (በአሕመድ፣በአቡ ዳውድና በነሳኢ የተዘገበ)

-

አቡ በክር  ምላሳቸውን ይዘው እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹ይህ ነው ለአደጋ ያጋለጠኝ››

በተጨማሪም እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹ምነው የሚበላ ዛፍ በሆንኩ ኖሮ!››

ዑመር ብን አልኸጧብም  እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹ምነው ምንም የማይወሳ ነገር በሆንኩ ኖሮ! ምነው እናቴ ባልወለደችኝ ኖሮ!››

በተጨማሪም እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹አንድ አህያ በኤፍራጠስ ወንዝ ዳርቻ በርሃብ ቢሞት፣በትንሣኤ ቀን አላህ በዚያ (በመራቡ) እንዳይጠይቀኝ እፈራለሁ።››

በተጨማሪም እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹እናንተ ሰዎች ሆይ! ሁላችሁም ከአንድ ሰው በስተቀር ወደ ጀነት ገቢዎች ናችሁ ተብሎ በሰማይ ጠሪ ቢያውጅ፣እኔ ያ ሰው እንዳልሆን በእርግጥ እፈራለሁ።››

ዑሥማን ብን ዐፍፋን  እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹ከሞትኩ በኋላ ዳግም ባልቀሰቀስ እወድ ነበር።››

ሌሊቱን ሙሉ በአላህ ውዳሴ፣በሶላትና በቁርኣን ንባብ ያሳልፉ የነበሩ ሰው ናቸው እንዲህ ያሉት።

እመ ምእመናን ዓእሻ (ረ.ዐ) የሚከተለውን የአላህ ቃል ፦

(فَمَنَّ ٱللَّهُ عَلَيۡنَا وَوَقَىٰنَا عَذَابَ ٱلسَّمُومِ ٢٧)

‹‹አላህም በኛ ላይ ለገሰ፤የመርዛም እሳት ቅጣትንም ጠበቀን።››

[አልጡር፡27]

ሶላታቸው ውስጥ ያነቡና ሳያቋርጡ ያለቅሱ ነበር . . ።

(إِن تُعَذِّبۡهُمۡ فَإِنَّهُمۡ عِبَادُكَۖ وَإِن تَغۡفِرۡ لَهُمۡ فَإِنَّكَ أَنتَ ٱلۡعَزِيزُ ٱلۡحَكِيمُ ١١٨)

‹‹ብትቀጣቸው እነሱ ባሮችህ ናቸው፤ለነርሱ ብትምርም አንተ አሸናፊው ጥበበኛው ነህ (ይላል)።››

[አልማኢዳህ፡118]

አላህን መፍራት (ኸውፍን) የሚመለከቱ ብያኔዎችና ማሳሰቢያዎች ፦

1-

ስጋት (ኸሽያህ) ከፍርሃት (ኸውፍ) የጠለቀና ለየት ያለ ነው። ስጋት አላህን ይበልጥ ለሚያውቁ ትጉሃን አገልጋዮች ነው ፦

إِنَّمَا يَخۡشَى ٱللَّهَ مِنۡ عِبَادِهِ ٱلۡعُلَمَٰٓؤُاْۗ إِنَّ ٱللَّهَ عَزِيزٌ غَفُورٌ ٢٨)

‹‹አላህን ከባሮቹ ውስጥ የሚፈሩት፣ዐዋቂዎቹ ብቻ ናቸው፤አላህ አሸናፊ መሓሪ ነው።››

[ፋጢር፡28]

ፍርሃታቸው እርሱን ከማወቅ ጋር የተቆራኘ ፍርሃት ነው። ነቢዩﷺ እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹በአላህ እምላለሁ፣እኔ ከሁላችሁም ይበልጥ እርሱን ’ምፈራና እርሱን ’ምሰጋ ነኝ።››

(በሙስሊም የተዘገበ)

ለርሱ የሚኖረን ፍርሃትና ስጋት አላህን፣ስሞቹን፣ባሕርያቱን፣ምሉእነቱን፣ግርማ ሞገሱንና ኃልልነቱን አስመልክቶ በሚኖረን ዕውቀትና ግንዛቤ ደረጃ ነው።

2-

ፍርሃት ለጥረት ለበጎ ሥራ፣ኃጢአትን እርግፍ አድርጎ በመተው ተጸጽቶ ተውበት ለማድረግ የሚያነሳሳ ሲሆን ጠቃሚ ይሆናል። ፍርሃት የሚመነጨው የኃጢአትን አስቀያሚነት ከማወቅ፣የተላለፈውን ማስጠንቀቂያ እውነተኛነት ከማረጋገጥ፣ኃያሉን ቻይ አምላክ ከማወቅ ነው። ለሰናይ ተግባር ለጥረት፣ለትጋትና ለተውበት የማያበረታታ የአላህ ፍርሃት የሚታሰብ አይደለም።

3-

አላህንﷻ መፍራት ከግዴታዎች አንዱ ሲሆን፣ለኢማን መገኘት ካለባቸው ነገሮች ውስጥም አንዱ ነው። ወደ አላህﷻ በሚደረገው ጉዞ ውስጥ ክቡር ከሆኑ ምዕራፎችም አንደኛውና ለልብ እጅግ ጠቃሚው ምዕራፍ ነው። በሁሉም ሰው ላይ ግዴታ (ዋጅብ) ሲሆን፣ከኃጢአቶች፣ከዱንያ፣ከመጥፎ ጓደኞች፣ከዝንጋታ፣ከቸልታና ከሕሊና ዝገት ይከላከላል።

(إِنَّمَا يَخۡشَى ٱللَّهَ مِنۡ عِبَادِهِ ٱلۡعُلَمَٰٓؤُاْۗ إِنَّ ٱللَّهَ عَزِيزٌ غَفُورٌ ٢٨) [فاطر: 28]

‹‹አላህን ከባሮቹ ውስጥ የሚፈሩት፣ዐዋቂዎቹ ብቻ ናቸው፤አላህ አሸናፊ መሓሪ ነው።›› [ፋጢር፡28]

አላህን የፈራ ሰው፣ማንም አይጎዳውም፤ከርሱ በስተቀር ሌለውን የፈራ ሰውን ማንም አይጠቅመውም።

ፈዲል ብን ዕያድ

መልመጃ

1- ለአላህﷻ ያለህን ፍራቻ የሚጨምሩ ነገሮችን ጥቀሳቸው፣በቁጥር አስቀምጣቸው።

2- የርሱን ፍራቻ የሚያመጡና የምታውቃቸውን የአላህንﷻ ስሞችና ባሕርያት ጥቀስ።

3- አላህን የሚፈራ ሰው ምን ማድረግ ይገባዋል?

ሁለተኛው ምድብ - በተግባራትና በስነምግባር ላይ የሚኖረው ዕባዳዊ አሻራዎች ፦

የአላህ ተውሒድ በሰው ስነምግባርና በድርጊቶቹ ውስጥ፣እንዲሁም በልቦናውና በጥንቁቅነቱ ላይም ይንጸባረቃል። በበግላዊ ስነምግባሩና ከሌሎች ጋር በሚኖረው ማህበራዊ ስነምግባሩ ውስጥም ይንጸባረቃል። ሕይወት በጥቅሉ ከኢማን፣ከተውሒድና ከዕባዳ መገለጫ አሻራዎች አንዱ ነው። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

( وَمَا خَلَقۡتُ ٱلۡجِنَّ وَٱلۡإِنسَ إِلَّا لِيَعۡبُدُونِ ٥٦ )

‹‹ጋኔንንና ሰውንም ሊግገዙኝ እንጅ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም።››

[አልዛሪያት፡56]