የፍጹምነት (እኽላስ) ትርጉም፦ 1

የፍጹምነት (እኽላስ) ትርጉም፦ 1
ፍጹምነት የፍጹሞች (የሙኽሊሶች) ጀነትና አላህን የሚፈሩ ትጉሃን አገልጋዮቹ መንፈስ፣በፈጣሪና በባሪያው መካከል የሚገኝ ምስጢር ነው። መመጻደቅንና ልታይባይነትን ገቺ ነው። የሚሠራውን ሥራ አላህን ብቻ በማሰብና ለርሱ ብቻ ብሎ መሥራት ነው። ልብ ውስጥ ከአላህ በስተቀር ሌላ የሚታሰብ ነገር አለመኖር ነው። በሚሠራው ሥራ ከሰዎች ምንም ምስጋናም ሆነ ውዳሴ አለመጠበቅ ነው። የሥራን ዋጋ ከአላህﷻ ብቻ እንጂ ከማንም አለመጠበቅ ነው።

 

እኽላስ የሥራ ምልአትና ውበት ነው። በዱንያ ላይ በጣም ውዱ ነገር ነው። እኽላስ አላህንﷻ ብቻ የዕባዳ ዓላማና ግብ በማድረግ ዘውትር የርሱን ተቆጣጣሪነት እያሰቡ ፍጡራንን መርሳት ነው። ለርሱ ብቻ ተብሎ ለተሠራው ሥራ ቸሩ አላህ ﷻ ተገቢውን ምንዳ የሚሰጥ ሲሆን ለሌው ተብሎ የተሠራው ግን ከንቱ ልፋት ሆኖ ይቀራል። ነቢዩﷺ እንዲህ ብለዋል፦

‹‹ሥራዎች (የሚለኩት ከጀርባቸው ባለው ቁርጠኛ) ውሳኔ ነው፤እያንዳንዱ ሰውም በንይ'ያው መሰረት ነው የሚያገኘው፡፡ ስደቱ ወደሚያገኘው ዓለማዊ ጥቅም ወይም ወደሚያገባት ሴት የሆነ ሰው፣ስደቱ ለተሰደደበት ዓላማ ነው።››

(በቡኻሪ የተዘገበ)

አዩብ አስሰኽትያኒ ሌሊቱን ሙሉ በዕባዳ ያሳልፉ ነበር፤ሲነጋ ገና አሁን እንደ ነቁ ለማስመሰል ድምጻቸውን ከፍ ያደርጉ ነበር።

ፍጹምነት (እኽላስ) ያለው ደረጃ ፦

እኽላስ አቻ የሌለው የላቀ ደረጃ ያለው ሲሆን፣እኽላስ የሌለበት ሥራ ተቀባይነት የለውም። አላህﷻ ሥራችን እኽላስ እንዲኖረው ቅዱስ ቁርኣን ውስጥ በብዙ አንቀጾች ያሳሰበ ሲሆን፣የሚከተሉት ጥቂቶቹ ናቸው፦

(وَمَآ أُمِرُوٓاْ إِلَّا لِيَعۡبُدُواْ ٱللَّهَ مُخۡلِصِينَ لَهُ ٱلدِّينَ)

‹‹አላህን ሃይማኖትን ለርሱ ብቻ አጥሪዎች፣ ቀጥተኞች ኾነው ሊግገዙት፣. . እንጅ ያልታዘዙ ሲኾኑ (ተለያዩ)።››

[አልበይይናህ፡5]

አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(قُلۡ إِنَّ صَلَاتِي وَنُسُكِي وَمَحۡيَايَ وَمَمَاتِي لِلَّهِ رَبِّ ٱلۡعَٰلَمِينَ١٦٢لَا شَرِيكَ لَهُۥۖ وَبِذَٰلِكَ أُمِرۡتُ وَأَنَا۠ أَوَّلُ ٱلۡمُسۡلِمِينَ١٦٣)

‹‹ስግደቴ፣መገዛቴም፣ሕይወቴም፣ሞቴም፣ለዓለማት ጌታ ነው በል። ለርሱ ተጋሪ የለውም፤በዚህም (በማጥራት) ታዘዝኩ፤እኔም የሙስሊሞች መጀመሪያ ነኝ (በል)።››

[አልአንዓም፡162-163]

በተጨማሪም አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(ٱلَّذِي خَلَقَ ٱلۡمَوۡتَ وَٱلۡحَيَوٰةَ لِيَبۡلُوَكُمۡ أَيُّكُمۡ أَحۡسَنُ عَمَلٗا)

‹‹ያ የትኛችሁ ሥራው ይበልጥ ያማረ መኾኑን ሊሞክራችሁ፣ሞትንና ሕይወትን የፈጠረ ነው፤››

[አልሙልክ፡2]

በተጨማሪም እንዲህ ብሏል፦

(إِنَّآ أَنزَلۡنَآ إِلَيۡكَ ٱلۡكِتَٰبَ بِٱلۡحَقِّ فَٱعۡبُدِ ٱللَّهَ مُخۡلِصٗا لَّهُ ٱلدِّينَ٢أَلَا لِلَّهِ ٱلدِّينُ ٱلۡخَالِصُ)

‹‹እኛ ወደ አንተ መጽሐፉን በውነት (የተሞላ) ሲኾን አወረድነው፤አላህንም ሃይማኖትን ለርሱ ብቻ ያጠራህ ኾነህ ተገዛው። ንቁ! ፍጹም ጥሩ የኾነው ሃይማኖት የአላህ ብቻ ነው።››

[አልዙመር፡2-3]

አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(فَمَن كَانَ يَرۡجُواْ لِقَآءَ رَبِّهِۦ فَلۡيَعۡمَلۡ عَمَلٗا صَٰلِحٗا وَلَا يُشۡرِكۡ بِعِبَادَةِ رَبِّهِۦٓ أَحَدَۢا١١٠)

‹‹የጌታውንም መገናኘት የሚፈልግ ሰው፣መልካም ሥራን ይሥራ፤በጌታውም መገዛት አንድንም አያጋራ፣በላቸው።››

[አልከህፍ፡11]


ቅርጽና ይዘቱ፣ውጭና ውስጡ የማይጣጣም ሥራ ሁሉ ውድቅ ነው።

 

አንደኛ - የአላህንﷻ ተውሒድ እውን በማድረግ። አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(مُخۡلِصٗا لَّهُ ٱلدِّينَ٢أَلَا لِلَّهِ ٱلدِّينُ ٱلۡخَالِصُ)

‹‹ሃይማኖትን ለርሱ ብቻ ያጠራህ ኾነህ ተገዛው። ንቁ! ፍጹም ጥሩ የኾነው ሃይማኖት የአላህ ብቻ ነው።››

[አልዙመር፡2-3]

በተጨማሪም አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

( وَمَآ أُمِرُوٓاْ إِلَّا لِيَعۡبُدُواْ ٱللَّهَ مُخۡلِصِينَ لَهُ ٱلدِّينَ)

‹‹አላህን ሃይማኖትን ለርሱ ብቻ አጥሪዎች፣ ቀጥተኞች ኾነው ሊግገዙት፣. . እንጅ ያልታዘዙ ሲኾኑ (ተለያዩ)።››

[አልበይይናህ፡5]

ሁለተኛ - ለአላህ መልክተኛ ﷺ ተከታይ መሆንን በማረጋገጥ፣ያዘዙትን በመፈጸም፣ከከለከሉት ሁሉ በመራቅና የተናገሩት ሁሉ እውነት መሆኑን በመቀበል። አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(يَٰٓأَيُّهَا ٱلَّذِينَ ءَامَنُوٓاْ أَطِيعُواْ ٱللَّهَ وَأَطِيعُواْ ٱلرَّسُولَ وَأُوْلِي ٱلۡأَمۡرِ مِنكُمۡۖ فَإِن تَنَٰزَعۡتُمۡ فِي شَيۡءٖ فَرُدُّوهُ إِلَى ٱللَّهِ وَٱلرَّسُولِ إِن كُنتُمۡ تُؤۡمِنُونَ بِٱللَّهِ وَٱلۡيَوۡمِ ٱلۡأٓخِرِۚ ذَٰلِكَ خَيۡرٞ وَأَحۡسَنُ تَأۡوِيلًا٥٩)

‹‹እላንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን ተገዙ፤መልክተኛውንና ከናንተም የሥልጣን ባለቤቶችን ታዘዙ፤በማንኛውም ነገር ብትከራከሩ፣በአላህና በመጨረሻው ቀን የምታምኑ ብትኾኑ (የተከራከራችሁበትን ነገር) ወደ አላህና ወደ መልክተኛው መልሱት፤ይህ የተሻለ፣መጨረሻውም ያማረ ነው።››

[አልኒሳእ፡59]

ሦስተኛ - ሙኽሊስ መሆን ከፈለግህ በመልካም ሥራህ ላይ ትጋት ይኑርህ፤ከርሱ ጥላ በስተቀር ሌላ ጥላ በሌለበት የቅያማ ቀን አላህﷻ በጥላው ስር ከሚያስጠልላቸው ሰባቱ ውስጥ አንዱ፦

‹‹ . . መጽዋትን መስጠቱን የደበቀ (ደብቆ የሰጠ) ሰው . . ›› መሆኑን ሁሌ አስታውስ።

(በቡኻሪ የተዘገበ)

በተጨማሪም ፦

‹‹ሥራዎች (የሚለኩት) በንይ'ያ (ከጀርባቸው ባለው ቁርጠኛ) . . ›› መሆኑን አስታውስ።

(በቡኻሪ የተዘገበ)

አራተኛ - ልብህ የሰውን ምስጋና እና ውዳሴ ወደ መውደድ አያምራ። በሰዎች እጅ ካለው ነገር ሁሉ ተስፋ ቆርጠህ በፈጣሪህ ላይ ብቻ ተስፋህን ጣል። ለጌታው ፍጹም የሆነ ሙኽሊስ ሰው ለሚያገኘው ሀብት ወይም ለሚያገባት ሴት አይጓጓም፤የሚከጅለውና የሚጓጓው ለአላህﷻ እዝነትና ችሮታ ነው።

አምስተኛ - ፍጹምነትንና ቅን ልቦናን ይሰጥህ ዘንድ፣ከልታይባይነት አጥርቶህ ያለፉ ኃጢቶችህን ይምርህ ዘንድ ከጌታህ ፊት ወድቀህ ከደጁ በመንከባለል እርሱን መለመንና መማጸን ይኖርብሃል።

ከአላህﷻ በስተቀር ለሥራህ መስካሪና ሸላሚ ባለመፈለግ ለርሱ ብቻ ፍጹም ሁን።

ስድስተኛ - ከታይታና ከመመጻደቅ መራቅና መጠንቀቅ። አንድ የአላህ አገልጋይ ታይታ (ሪያእ) ወደ ልቡ የሚመጣበትን መንገድና መግቢያ በሩን ካላወቀ፣ከእኽላስ መንገድ ይርቃል። በዚህ ምክንያት ነው አንዳንድ ሰዎች የአላህ ጻድቅ (ወሊይ) አድርገው ራሳቸውን ሲገልጹ የሚስተዋሉት፣ወይም ሌሎች እንደዚያ ተብለው መጠራትን የሚወዱት፣ወይም ስለ ዕባዳቸውና ስለ በጎ ሥራዎቻቸው ማውራትና መመጻደቅን የሚያዘወትሩት።

አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(مَن كَانَ يُرِيدُ ٱلۡحَيَوٰةَ ٱلدُّنۡيَا وَزِينَتَهَا نُوَفِّ إِلَيۡهِمۡ أَعۡمَٰلَهُمۡ فِيهَا وَهُمۡ فِيهَا لَا يُبۡخَسُونَ١٥أُوْلَٰٓئِكَ ٱلَّذِينَ لَيۡسَ لَهُمۡ فِي ٱلۡأٓخِرَةِ إِلَّا ٱلنَّارُۖ وَحَبِطَ مَا صَنَعُواْ فِيهَا وَبَٰطِلٞ مَّا كَانُواْ يَعۡمَلُونَ ١٦)

‹‹ቅርቢቱን ሕይወትና ጌጣጌጧን የሚሹ የኾኑትን ሰዎች፣ሥራዎቻቸውን (ምንዳዋን) በርሷ ውስጥ ወደነሱ እንሞላላቸዋለን፤እነርሱም በርሷ ውስጥ ምንም አይጎድልባቸውም። እነዚያ እነርሱ በመጨረሻይቱ ዓለም ለነርሱ ከእሳት በቀር የሌለላቸው ናቸው፤የሠሩትም ሥራ በርሷ ውስጥ ተበላሸ፤(በቅርቢቱ ዓለም) ይሠሩት የነበሩትም በጎ ሥራ ብልሹ ነው።››

[ሁድ፡15-16]

ታይታ ትንሹ ሽርክ (በአላህ ማጋራት) ነው። ከአስከፊ ፍጻሜው መካከል ሥራዎች ላይ ላዩን በጎ ቢመስሉ እንኳ በእኽላስ ካልተሠሩ ተቀባይነት የማይኖራቸውና ወደ ባለቤቶቻቸው የሚመለሱ ወዳቂ መሆናቸው ብቻ በቂ ነው።

ሰባተኛ - እኽላስ ካላቸው ሰዎች ጋር መጎዳኘት። ነቢዩﷺ እንዲህ ብለዋል፦

‹‹ሰው በወዳጁ ሃይማኖት ላይ ነው (አርአያነቱን ይከተላል) . . ››

(በትርምዚ የተዘገበ)

እኽላስና ምስጋና እና ውዳሴን መውደድ በአንድ ልብ ውስጥ አብረው አይኖሩም፤ውሃ እሳትን እንደሚያጠፋ አንዱ ሌላውን ያወድማል ያጠፋዋል።

ስምንተኛ - ዕባዳን በድብቅና በስውር ማድረግ። አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(إِن تُبۡدُواْ ٱلصَّدَقَٰتِ فَنِعِمَّا هِيَۖ وَإِن تُخۡفُوهَا وَتُؤۡتُوهَا ٱلۡفُقَرَآءَ فَهُوَ خَيۡرٞ لَّكُمۡ)

‹‹ምጽዋቶችን ብትገልጹ፣እርሷ ምንኛ መልካም ናት፤ብትደብቋትና ለድኾች ብትሰጧትም፣እርሱ ለናንተ በላጭ ነው።››

[አልበቀራህ፡271]

ዘጠነኛ- የገዛ ራስን በማያቋርጥ ሁኔታ ሁሌ በጥብቅና በጥልቀት መመርመር። አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(وَٱلَّذِينَ جَٰهَدُواْ فِينَا لَنَهۡدِيَنَّهُمۡ سُبُلَنَا)

‹‹እነዚያም በኛ መንገድ የታገሉ፣መንገዳችንን በእርግጥ እንመራቸዋለን፤››

[አልዐንከቡት፡69]

የሚከተለውን የአላህﷻ ቃል አስተውል፦

(فِينَا)!!‹‹በኛ መንገድ››!!

ዐስረኛ - አዘውትሮ ወደ አላህ መጸለይና ፊትን ወርሱ መመለስ። ደሃውና ጎስቋላው ሰው የቸር ጌታውን ደጃፍ ካዘወተረ ይራራለታል፣ያዘንለታል፤የለመነውን ይሰጠዋል፤ችግሩን ይፈታለታል፤የጎደለውንም ያሟላለታል። . . የሚለመነውና የሚጠየቀው አላህﷻ ብቻ ነውና።


1- የሥራዎች ተቀባይነት፦

 

ይህ እጅግ በጣም አስፈላጊ ጉዳይ ሲሆን፣እኽላስ ሥራዎች አላህﷻ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖራቸው መሟላት ያለበት ዋነኛው መስፈርት (ሸርጥ) ነው። ነቢዩﷺ ይህን በማስመልከት እንዲህ ብለዋል፦

‹‹አላህ ﷻ ከሥራ ለርሱ ብቻ ተብሎ በፍጹምነት (በእኽላስ) የተሰራውንና የርሱ ፊት የታለመበትን ብቻ እንጂ አይቀበልም።››

(በነሳኢ የተዘገበ)

በተጨማሪም ነቢዩﷺ እንዲህ ብለዋል፦

‹‹አላህ ﷻ ይህችን ኡምማ የሚያግዘው በደካሞቿ፣በዱዓቸው፣በሶላቶቻቸውና በፍጹምነታቸው (በእኽላሳቸው) ነው።››

(በነሳኢ የተዘገበ)

2-

የልቦና ሰላምና ከበሽታዎች ነጻ መሆን፦

ይህ እንደ ጥላቻ፣ክህደት፣እምነት ማጉደልና ምቀኝነት ካሉ የውስጥ ደዌዎች ነጻ መሆን ማለት ነው። የአላህ መልክተኛ ﷺ በመሰናበቻው ሐጅ ላይ እንዲህ ብለዋል፦

‹‹በሦስት ነገሮች እስከተካነ ድረስ የሙስሊም ልብ በክህደትና በመናፍቅነት በሽታ አይጠቃም እነሱም፦ ሥራን ለአላህ ብቻ ፍጹም ማድረግ፣ሙስሊም መሪዎችን መምከር፣የሙስሊሞችን ኅብረት (ጀማዓቸውን) አጥብቆ መያዝ ሲሆኑ፣ጥሪው ከጀርባቸው ያሉትንም ያጠቃልላል።››

(በትርምዚ የተዘገበ)

እብኑ ዑመር እንዲህ ብለዋል፦ አላህ ﷻ አንዲቷን ሱጁድና የአንዲት ድርሃም ምጽዋት ከኔ መቀበሉን ባውቅ ኖሮ፣ርቆ ከሚገኝ ነገር ሁሉ ከሞት ይበልጥ ለኔ የተወደደ ባልኖረ ነበር። አላህ ከማን እንደሚቀበል ታውቃለህን?

(إِنَّمَا يَتَقَبَّلُ ٱللَّهُ مِنَ ٱلۡمُتَّقِينَ ٢٧) [المائدة: 27] .

‹‹አላህ የሚቀበለው እኮ ከጥንቁቁቹ ብቻ ነው።›› [አልማኢዳህ፡27]

4- ዓለማዊ ሥራን ከመንፈሳዊ በጎ ሥራ ጋር ማጣመር ፦

ነቢዩﷺ እንዲህ ብለዋል፦

‹‹አንዳችሁ (ከሚስቱ ጋር) ግብረ ሥጋ መፈጸሙ ምጽዋት (ሶደቃ) ነው›› ሲሉ፣የአላህ መልክተኛ ሆይ! አንዳችን የራሱን ሥጋዊ ፍላጎት በማርካቱ ምንዳ ያገኝበታል ማለት ነው?! ብለው ጠየቋቸው። ‹‹ሐራም በሆነ ግንኙነት ያን ፈጽሞ ቢሆን ኖሮ ኃጢኣቱን ይሸከም የለምን?! እንደዚያው ሁሉ ሐላል በሆነ ግንኙነት በመርካቱ ምንዳ ያገኝበታል።›› አሉ።

(በሙስሊም የተዘገበ)

5- ሰይጣናዊ ሀሳቦችን፣ክፉና ጎትጓች ግምቶችን ማበረር፦

አላህﷻ ከእዝነቱ ጎራ ሲያባርረውና ከቸርነቱ ሲያርቀው ሰይጣንን አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦

(قَالَ رَبِّ بِمَآ أَغۡوَيۡتَنِي لَأُزَيِّنَنَّ لَهُمۡ فِي ٱلۡأَرۡضِ وَلَأُغۡوِيَنَّهُمۡ أَجۡمَعِينَ٣٩إِلَّا عِبَادَكَ مِنۡهُمُ ٱلۡمُخۡلَصِينَ ٤٠)

‹‹(ኢብሊስ) አለ፦ ጌታዬ ሆይ! እኔን በማጥመምህ ይኹንብኝ ለነርሱ በምድር ላይ (ኀጢአትን) እሸልምላቸዋለሁ፤መላቸውን አጠማቸውም አለሁ፤ከነርሱ ፍጹሞቹ ባሮችህ ብቻ ሲቀሩ።››

[አልሒጅር፡39-40]

6- ችግሮችንና መከራዎችን ማስወገድ፦ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው በቡኻሪና ሙስሊም በተዘገው ሐዲሥ ውስጥ የሰፈረውና ዋሻ ውስጥ ለማደር ተገደው የዋሻው አፍ የተዘጋባቸው የሦስቱ ሰዎች ታሪክ ነው።

7- ከፈተናዎች አደጋ ነጻ መሆንና መዳን፦ በዚህ ረገድ የነቢዩ ዩሱፍ  ገጠመኝ ሁሌም ይጠቀሳል። ይህንኑ በማስመልከት አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(وَلَقَدۡ هَمَّتۡ بِهِۦۖ وَهَمَّ بِهَا لَوۡلَآ أَن رَّءَا بُرۡهَٰنَ رَبِّهِۦۚ كَذَٰلِكَ لِنَصۡرِفَ عَنۡهُ ٱلسُّوٓءَ وَٱلۡفَحۡشَآءَۚ إِنَّهُۥ مِنۡ عِبَادِنَا ٱلۡمُخۡلَصِينَ٢٤)

‹‹በርሱም በእርግጥ አሰበች፤በርሷም አሰበ፤የጌታውን ማስረጃ ባላዬ ኖሮ፣(የተፈጥሮ ፍላጎቱን ባረካ ነበር)፤እንደዚሁ መጥፎ ነገርንና ኀጢአትን ከርሱ ላይ ልንመልስለት (አስረጃችንን አሳየነው)፤እርሱ ከተመረጡት ባሮቻችን ነውና።››

[ዩሱፍ፡24]

በአካሉ ከዱንያ የራቀ ብዙ ሰው በልቡ እውስጧ እየዳከረ ሊሆን ይችላል፤በአካሉ በውስጧ የሚገኝ ብዙ ሰው ደግሞ በልቡ ከርሷ ጋር የተቆራረጠ ሊሆን ሲችል ይኸኛው ከሁለቱ በጣም አስተዋዩ ነው።

8- የሥራ መጠን አነስተኛ ቢሆን እንኳ ምንዳን ማግኘት። አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

( وَلَا عَلَى ٱلَّذِينَ إِذَا مَآ أَتَوۡكَ لِتَحۡمِلَهُمۡ قُلۡتَ لَآ أَجِدُ مَآ أَحۡمِلُكُمۡ عَلَيۡهِ تَوَلَّواْ وَّأَعۡيُنُهُمۡ تَفِيضُ مِنَ ٱلدَّمۡعِ حَزَنًا أَلَّا يَجِدُواْ مَا يُنفِقُونَ ٩٢ )

‹‹በነዚያም ልትጭናቸው በመጡህ ጊዜ፣በርሱ ላይ የምጭናችሁ (አጋሰስ) አላገኝም ያልካቸው ስትኾን፣የሚያወጡት ገንዘብ ባለማግኘታቸው ለማዘናቸው ዓይኖቻቸው እንባን እያፈሰሱ በዞሩት ላይ (የወቀሳ መንገድ የለባቸውም)።››

[አልተውባህ፡92]

ነቢዩﷺ ይህን አስመልክተው እንዲህ ብለዋል፦

‹‹ሰማእትነትን (ሸሃዳን) ለማግኘት በፍጹም ልቦና አላህን የለመነን ሰው፣በመኝታው ላይ እያለ ቢሞት እንኳ አላህ ከሰማእታት ደረጃዎች ያደርሰዋል።››

(በሙስሊም የተዘገበ)

9- ጀነት መግባት። አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

( وَمَا تُجۡزَوۡنَ إِلَّا مَا كُنتُمۡ تَعۡمَلُونَ ٣٩ )

‹‹ትሠሩትም የነበራችሁትን እንጂ ሌላን አትመነዱም።››

[አልሷፍፋት፡39]

በተጨማሪም አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(إِلَّا عِبَادَ ٱللَّهِ ٱلۡمُخۡلَصِينَ٤٠ أُوْلَٰٓئِكَ لَهُمۡ رِزۡقٞ مَّعۡلُومٞ٤١ فَوَٰكِهُ وَهُم مُّكۡرَمُونَ٤٢فِي جَنَّٰتِ ٱلنَّعِيمِ٤٣عَلَىٰ سُرُرٖ مُّتَقَٰبِلِينَ٤٤يُطَافُ عَلَيۡهِم بِكَأۡسٖ مِّن مَّعِينِۢ٤٥بَيۡضَآءَ لَذَّةٖ لِّلشَّٰرِبِينَ٤٦لَا فِيهَا غَوۡلٞ وَلَا هُمۡ عَنۡهَا يُنزَفُونَ٤٧وَعِندَهُمۡ قَٰصِرَٰتُ ٱلطَّرۡفِ عِينٞ٤٨كَأَنَّهُنَّ بَيۡضٞ مَّكۡنُونٞ٤٩)

‹‹ግን ምርጥ የኾኑት የአላህ ባሮች (ቅጣትን አይቀምሱም)። እነዚያ ለነርሱ የታወቀ ሲሳይ አልላቸው። ፍራፍሬዎች፣(አሏቸው)፤እነርሱም የተከበሩ ናቸው፤በድሎት ገነቶች ውስጥ። ፊት ለፊት የሚተያዩ ሲኾኑ፣በአልጋዎች ላይ፣(ይንፈላሰሳሉ)። ከሚመነጭ ወይን ጠጅ በያዘ ብርጭቆ በነርሱ ላይ ይዝዞርባቸዋል። ነጭ፣ለጠጪዎች ጣፋጭ ከኾነች፤በርሷ ውስጥም ምታት የሌለባትም፤እነርሱም ከርሷ የሚሰክሩ አይደሉም። እነርሱም ዘንድ ዓይናቸውን (በባሎቻቸው ላይ) አሳጣሪዎች የኾኑ ዓይናማዎች አልሉ፤እነርሱ ልክ የተሸፈነ (የሰጎን) ዕንቁላል ይመስላሉ።››

[አልሷፍፋት፡40-49]

ይህ ከእኽላስ ፍሬዎች እጅግ የላቀው ነው።

ብዙውን ትንሽ ሥራ ንይያ ትልቀ ሲያደርገው፣ብዙውን ትልቅ ሥራ ንይያ ትንሽ ያደርገዋል።

እብን አልሙባረክ

መጥፎ ሥራዎችህን እንደምትደብቅ ሁሉ መልካም ሥራዎችህንም (ከታይታ) ደብቅ።

አቡ ሃዝም አልመዲኒይ