አላህን በመገናኘት ማመን

አላህን በመገናኘት ማመን
ፍጥረታት ሁሉ ወደ ፈጣሪ አምላካቸው ተመላሾች ናቸው፤መጨረሻቸውና ፍጻሜያቸው ወደርሱ ብቻ ነው። ይህ በአላህ ከማመን መሰረታዊ ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን ከኢማን ማእዘናትም አንዱ ነው። በመጨረሻው ቀን ማመን አንዱ የእምነት ማእዘን ሲሆን፣ነቢያችን ﷺ ከሶሓባ ጋር በተቀመጡበት መልኣኩ ጅብሪል መጥቶ ሶሓባ ይማሩበት ዘንድ ስለ ኢማን ማእዘናት ሲጠይቃቸው፣ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦

‹‹በአላህ፣በመላእኮቹ፣በመጽሐፎቹ፣በመልእክተኞቹ፣በመጨረሻው ቀን፣በጎም ሆነ ክፉ በቀድር (በቅድመ ውሳኔው) የሚከሰት መሆኑን ማመን ነው።››

(በሙስሊም የተዘገበ)

የመጨረሻው ቀን ተብሎ የተሰየመው ከዚያ በኋላ የጀነት ሰዎች በጀነት፣የእሳት ሰዎችም በጀሀነም ወደየቤቶቻቸው የሚገቡ በመሆኑ ሌላ ቀን የሌለለ በመሆኑ ነው። ቅዱስ ቁርኣን ውስጥ ደረጃውንና በዚህ ቀን የሚከሰቱትን ነገሮች ከባድነት በሚያመለክቱ አያሌ ስሞች ተጠቅሷል። ከነዚህም መካከል፣መከሰቷ የተረጋገጠ በመሆኑ ኋኝቷ ቀን፣ከፊሎቹን ጀነት ውስጥ ከፍ ስታደርግ ሌሎቹን እሳት ውስጥ ዝቅ የምታደርግ በመሆኗም ከፍ አድራጊ ዝቅ አድራጊዋ ቀን፣ የምርመራና የፍርድ ቀን፣አላህ የተናገራቸው ሁሉ የሚረጋገጡበት ቀን በመሆኗ አረጋጋጭቱ ቀን የሚሉ ይገኙበታል። በተጨማሪም አጥለቅላቂቱ ቀን፣የሚነፋው የቀንዱ ድምጽ ስለሚያደነቁር አደንቋሪቱ ቀን፣አላህ በከሓዲዎች ላይ ያስተላለፈው ዛቻ እውን ስለሚሆን የዛቻው ቀን፣የሚጸጸቱበትና የሚቆጩበት ቀን በመሆኗ የቁጭት ቀን፣ሁሉም በአንድ አደባባይ የሚገናኙበት ቀን በመሆኗ የመገናኛ ቀን፣የተቃረበች ቀን በመሆኗም የቀረበችው ቀን፣የጀነት ሰዎች የጀነት ሰዎችን፣የእሳት ሰዎችም የእሳት ሰዎችን የሚጣሩበት ቀን በመሆኗም የመጠራራት ቀን፣ቀጣይ ቀን የሌላት በመሆኗም መካኗ ቀን፣የመጨረሻዋ አገር፣የመርጊያ አገር፣ሰዎችን የምትሸፍን በመሆኗም ሸፋኝቱ ቀን . . የመሳሰሉ ሌሎች ስሞችም አሉት።

በመጨረሻው ቀን በማመን ውስጥ የሚካተቱ ነገሮች፦

አንደኛ- ከሞት በኋላ ባሉት ነገሮች ማመን

የመቃብር ውስጥ ፈተና፦

ይህ ሟቹ ከተቀበረ በኋላ መቃብሩ ውስጥ ስለ ጌታው፣ስለ ሃይማኖቱ፣ስለ ነቢዩ የሚጠየቅበት ፈተና ነው። አላህ ﷻ ለአማኝ አገልጋዮቹ ጽናት ይሰጥና ‹‹ጌታዬ አላህ ነው፤ሃይማኖቴ እስላም ነው፤ነቢዬ ሙሐመድ ናቸው›› ብለው ይመልሳሉ። አላህ ﷻ ግፈኞቹን ያጠማቸውና ከሓዲው፦ ‹‹ሃህ . . ሃህ . . አላውቅም›› ይላል። ተጠራጣሪው መናፍቅ ደግሞ፦ ‹‹እኔ እንጃ፣ሰዎች ሲሉ ሰምቼ ነው ያልኩት›› ብሎ ይመልሳል።

የመቃብር ውስጥ ስቃይና ድሎት፦

መቃብር ውስጥ የሚሰቃዩት ግፈኞች፣መናፍቃን፣ከሓዲዎችና ኃጢኣን አማኞች ናቸው። አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

(وَلَوۡ تَرَىٰٓ إِذِ ٱلظَّٰلِمُونَ فِي غَمَرَٰتِ ٱلۡمَوۡتِ وَٱلۡمَلَٰٓئِكَةُ بَاسِطُوٓاْ أَيۡدِيهِمۡ أَخۡرِجُوٓاْ أَنفُسَكُمُۖ ٱلۡيَوۡمَ تُجۡزَوۡنَ عَذَابَ ٱلۡهُونِ بِمَا كُنتُمۡ تَقُولُونَ عَلَى ٱللَّهِ غَيۡرَ ٱلۡحَقِّ وَكُنتُمۡ عَنۡ ءَايَٰتِهِۦ تَسۡتَكۡبِرُونَ ٩٣)

‹‹በደለኞችንም በሞት መከራዎች ውስጥ በኾኑ ጊዜ መላእክት እጆቻቸውን ዘርጊዎች ኾነው (ለቅጥጥብ) ነፍሶቻችሁን አውጡ፤በአላህ ላይ እውነት ያልኾነን ነገር ትናገሩ በነበራችሁትና ከአንቀጾቹም ትኮሩ በነበራችሁት ምክንያት፣ዛሬ የውርደትን ቅጣት ትመነዳላችሁ፣(የሚሏቸው ሲኾኑ) ብታይ ኖሮ፣(አስደናቂን ነገር ባየህ ነበር)።››

[አልአንዓም፡93]

አላህ ﷻ የፈርዖንን ቤተሰቦች አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦

(ٱلنَّارُ يُعۡرَضُونَ عَلَيۡهَا غُدُوّٗا وَعَشِيّٗاۚ وَيَوۡمَ تَقُومُ ٱلسَّاعَةُ أَدۡخِلُوٓاْ ءَالَ فِرۡعَوۡنَ أَشَدَّ ٱلۡعَذَابِ ٤٦ )

‹‹እሳት በጧትና በማታ በርሷ ላይ ይቀርባሉ፤ሰዓቲቱም በምትኾንበት ቀን የፈርዖንን ቤተሰቦች ብርቱ ቅጣት (ገሀነምን) አግቡዋቸው (ይባላል)።››

[አልሙእምን፡46]

ዘይድ ብን ሣብት ባስተላለፉት ሐዲሥ ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦

‹‹መቀባበርን ትተዋላችሁ ብዬ ባልሰጋ ኖሮ እኔ ‘ምሰማውን የመቃብር ውስጥ ስቃይ እንዲያሰማችሁ አላህን እለምን ነበር።›› ከዚያም ነቢዩ ፊታቸውን ወደኛ አዞሩና፦ ‹‹ከመቃብር ውስጥ ስቃይ የአላህን ጥበቃ ለምኑ›› አሉን። ‹‹ከመቃብር ውስጥ ስቃይ በአላህ እንጠበቃለን›› አልን። ‹‹ከእሳት ስቃይ የአላህን ጥበቃ ለምኑ›› አሉን። ‹‹ከእሳት ስቃይ በአላህ እንጠበቃለን›› አልን። ‹‹ግልጽ ከሆኑትና ስውር ከሆኑትም ፈተናዎች ሁሉ ለመጠበቅ አላህን ለምኑ አሉን›› ‹‹ግልጽ ከሆኑትና ስውር ከሆኑትም ፈተናዎች ሁሉ በአላህን እንጠበቃለን አልን።›› በመቀጠልም ‹‹ከደጅጃል (ሐሳዊ መሲሕ) ፈተና የአላህን ጥበቃ ለምኑ›› አሉን። ‹‹ከደጅጃል (ሐሳዊ መሲሕ) ፈተና በአላህ እንጠበቃለን›› አልን።

(በሙስሊም የተዘገበ)

ዑሥማን መቃብር አጠገብ ሲቆሞ ጺማቸው እስኪርስ ያለቅሱ ነበር። ጀነትና ጀሀነም ሲወሱ አያለቅሱም፣በዚህ ያለቅሳሉን? ተብለው ሲጠየቁ፣የአላህ መልእክተኛ ﷺ ፦ ‹‹መቃብር ከኣኽራ ማረፊያ ቦታዎች የመጀመሪያው ማረፊያ ነው፣ከርሱ መዳን ከተቻለ ቀጥሎ ያለው ከርሱ የቀለለ ነው፤በዚያ መዳን ካልተቻለ ግን ቀጥሎ ያለው ከርሱ የከፋ ነው።›› ብለዋል፣አሉ። በማከልም ነቢዩ ﷺ ፦ ‹‹ከመቃብር ይበልጥ አስበርጋጊ የሆነ ምንም የከፋ ትእይንት አይቼ አላውቅም።›› አሉ፣ብለዋል።

(በአሕመድ የተዘገበ)

የመቃብር ውስጥ ድሎት ለእውነተኞቹ ምእመናን ሲሆን፣አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

(إِنَّ ٱلَّذِينَ قَالُواْ رَبُّنَا ٱللَّهُ ثُمَّ ٱسۡتَقَٰمُواْ تَتَنَزَّلُ عَلَيۡهِمُ ٱلۡمَلَٰٓئِكَةُ أَلَّا تَخَافُواْ وَلَا تَحۡزَنُواْ وَأَبۡشِرُواْ بِٱلۡجَنَّةِ ٱلَّتِي كُنتُمۡ تُوعَدُونَ ٣٠)

‹‹እነዚያ ጌታችን አላህ ነው ያሉ፣ከዚያም ቀጥ ያሉ፦ አትፍሩ፤አትዘኑም፤በዚያችም ተስፋ ቃል ትደረግላችሁ በነበራችሁት ገነት ተበሰሩ፤በማለት በነሱ ላይ መላእክት ይወርዳሉ።››

[ሓ ሚም አልሰጅዳህ፡30]

አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

( فَلَوۡلَآ إِذَا بَلَغَتِ ٱلۡحُلۡقُومَ ٨٣ وَأَنتُمۡ حِينَئِذٖ تَنظُرُونَ ٨٤ وَنَحۡنُ أَقۡرَبُ إِلَيۡهِ مِنكُمۡ وَلَٰكِن لَّا تُبۡصِرُونَ ٨٥ فَلَوۡلَآ إِن كُنتُمۡ غَيۡرَ مَدِينِينَ ٨٦ تَرۡجِعُونَهَآ إِن كُنتُمۡ صَٰدِقِينَ ٨٧ فَأَمَّآ إِن كَانَ مِنَ ٱلۡمُقَرَّبِينَ ٨٨ فَرَوۡحٞ وَرَيۡحَانٞ وَجَنَّتُ نَعِيمٖ ٨٩ وَأَمَّآ إِن كَانَ مِنۡ أَصۡحَٰبِ ٱلۡيَمِينِ ٩٠ فَسَلَٰمٞ لَّكَ مِنۡ أَصۡحَٰبِ ٱلۡيَمِينِ ٩١ وَأَمَّآ إِن كَانَ مِنَ ٱلۡمُكَذِّبِينَ ٱلضَّآلِّينَ ٩٢ فَنُزُلٞ مِّنۡ حَمِيمٖ ٩٣ وَتَصۡلِيَةُ جَحِيمٍ ٩٤ إِنَّ هَٰذَا لَهُوَ حَقُّ ٱلۡيَقِينِ ٩٥ فَسَبِّحۡ بِٱسۡمِ رَبِّكَ ٱلۡعَظِيمِ ٩٦ )

‹‹(ነፍስ) ጉረሮንም በደረሰች ጊዜ። እናንተ ያን ጊዜ የምታዩ ስትኾኑ። እኛም፣ግን አታዩም እንጅ ከናንተ ይልቅ ወደርሱ የቀረብን ስንኾን። የማትዳኙም ከኾናችሁ። እውነተኞች እንደ ኾናችሁ፣(ነፍሲቱን ወደ አካሉ) ለምን አትመልሷትም። (ሟቹ) ከባለሟሎቹ ቢኾንማ። (ለርሱ) ዕረፍት መልካም ሲሳይም፣የመጠቀሚያ ገነትም አልለው። ከቀኝ ጓዶች ቢኾንማ። ከቀኝ ጓዶች ስለ ኾንክ ላንተ ሰላም አልለህ (ይባላል)። ከሚያስዋሹት ጠማማዎችም ቢኾንማ። ከፈላ ውሃ የኾነ መስተንግዶ አልለው። በገሀነም መቃጠልም (አልለው)። ይህ እርሱ እርግጠኛ እውነት ነው። የታላቁንም ጌታህን ስም አውድስ። ››

[አልዋቅዓህ፡83-93]

ሙእምን የሆነ ሰው፣መቃብር ውስጥ የሁለቱን መላእኮች ጥያቄዎች ከመለሰ የሚሆነውን ሁኔታ አስመልክተው ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦

‹‹ጠሪ ከሰማይ ይጣራና፦ ‹ባሪያዬ እውነቱን ተናገሯልና ከጀነት በሆነ ነገር አንጥፉለት፤ከጀነትም ልብስ አልብሱት፤ወደ ጀነት የሚወስድ በርም ክፈቱለት› ይላል። በዚህም ነፋስዋና የሽታዋ መዓዛ ይመጣለታል፤የዓይን እይታ እስከደረሰበት ድረስም መቃብሩ ይሰፋለታል።››

(በአሕመድና በአቡዳውድ ረዘም ባለ የሐዲሥ ትረካ ውስጥ የተዘገበ)

ሁለተኛ- ከሞት ዳግም መቀስቀስ (በዕሥ) በመኖሩ ማመን

በቀንዱ ለሁለተኛ ጊዜ ሲነፋ ሙታን፣ባዶ እግራቸውን ያለ ጫማ፣ራቆታቸውን ያለ ልብስ፣ያልተገረዙ ሆነው ወደ ዓለማት ጌታ የሚቀሰቀሱበት ሁኔታ ነው። አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

(كَمَا بَدَأۡنَآ أَوَّلَ خَلۡقٖ نُّعِيدُهُۥۚ وَعۡدًا عَلَيۡنَآۚ إِنَّا كُنَّا فَٰعِلِينَ ١٠٤)

‹‹የመጀመሪያን ፍጥረት እንደ ጀመርን፣እንመልሰዋለን፤(መፈጸሙ) በኛ ላይ የኾነን ቀጠሮ ቀጠርን፤እኛ (የቀጠርነውን) ሠሪዎች ነን።››

[አልአንቢያ፡104]

ዳግም ከሞት መነሳት በቁርኣን፣በሱንና አና በሙስሊሞች የጋራ አቋም የተረጋገጠ እውነታ ነው። አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

( ثُمَّ إِنَّكُم بَعۡدَ ذَٰلِكَ لَمَيِّتُونَ ١٥ ثُمَّ إِنَّكُمۡ يَوۡمَ ٱلۡقِيَٰمَةِ تُبۡعَثُونَ ١٦ )

‹‹ከዚያም እናንተ ከዚህ በኋላ ሟቾች ናችሁ። ከዚያም እናንተ በትንሣኤ ቀን ትቀሰቀሳላችሁ።››

[አልሙእምኑን፡15-16]

ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦

‹‹ሰዎች በትንሳኤ ቀን ባዶ እግራቸውን ያለ ጫማና ያልተገረዙ ሆነው ይሰበሰባሉ።››

(በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ)

ጸንቶ የተረጋገጠ በመሆኑ ላይ ሙስሊሞች በሙሉ ድምጽ የተስማሙበት ሲሆን፣በመልእክተኞች አንደበት የተጣለባቸውን ኃላፊነትና ግዴታ በተመለከተ እንደ አፈጻጸማቸው ተገቢ ዋጋቸውን ሊሰጣቸው፣አላህﷻ ለፍጥረታት መመለሻ እንዲኖራቸው ማድረጉ ጥበባዊም ነው። አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

( أَفَحَسِبۡتُمۡ أَنَّمَا خَلَقۡنَٰكُمۡ عَبَثٗا وَأَنَّكُمۡ إِلَيۡنَا لَا تُرۡجَعُونَ ١١٥ )

‹‹የፈጠርናችሁ ለከንቱ መኾኑን እናንተም ወደኛ የማትመለሱ መኾናችሁን ጠረጠራችሁን? (ለከንቱ የፈጠርናችሁ መሰላችሁን?)››

[አልሙእምኑን፡115]

አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

(إِنَّ الَّذِي فَرَضَ عَلَيْكَ الْقُرْآَنَ لَرَادُّكَ إِلَى مَعَادٍ )

‹‹ቁርኣንን ባንተ ላይ ያወረደው፣(አምላክ)፣ወደ መመለሻ (መካ) በእርግጥ መላሺህ ነው፤››

[አልቀሶስ፡85]

ሦስተኛ- የትንሣኤን ቀን ምልክቶችና የመቃረቡ አመላካች የሆኑ ነገሮችን በሚመለከት በተላለፉት ማመን፦

እነዚህ ከቅያማ ቀን አስቀድመው የሚከሰቱና መቃረቡን የሚጠቁሙ ነገሮች ሲሆኑ፣መለስተኛና ከፍተኛ ተብለው በሁለት ይከፈላለሉ።

መለስተኛ ምልክቶች፦

እነዚህ በአብዛኛው ከትንሳኤ ቀን ረዘም ያለ ጊዜ አስቀድመው የሚታዩ ምልክቶች ናቸው። ከነዚህ ከፊሎቹ ተከስተው ያለፉ ሲሆኑ ተደጋግመው ሊከሰቱም ይችላሉ። ከፊሎቹ ደግሞ የታዩና አሁንም በመከታተል መታየታቸውን የቀጠሉ ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ እስካሁን ያልተከሰቱ ሲሆኑ፣እውነተኛውና ተአማኒው ነቢይﷺ እንደ ገነገሩን ሁሉ በእርግጥ የሚከሰቱ ናቸው። እነዚህም የነቢዩ ሙሐመድን ﷺ መላክ፣መሞታቸውን፣የቤተል መቅድስን (እየሩሳሌም) በድል መያዝ፣የተፈታታኝ መከራዎችን መከሰት፣የእምነት አጉዳይነት መስፋፋትን፣የሸሪዓዊ ዕውቀት ማነስና የማይምነት መብዛትን፣የዝሙትና የወለድ መስፋፋትን፣የሙዚቃና ጭፈራ መሰራጨትን፣የአስካሪ መጠጥ በብዛት መጠጣትን፣የበግ እረኞች በሕንጻዎች ግንባታ መሽቀዳደምን፣እንደ ጌታ እስከማዘዝ ድረስ የልጆች እናቶቻቸውን ማስከፋትና ማስቀየምን፣የነፍስ ግድያ መበራከትን፣የመሬት መንቀጥቀጥ መብዛትን፣የመሬት መደርባትን፣የገጽታ ወደ መጥፎ መቀየርን፣የተራቆቱ ለባሽ ሴቶች መታየትን፣በሐሰት መመስከርን፣ እውነተኛ ምስክርነትን መደበቅ መበራከትንና በቁርኣንና በነቢዩ ሱንና ውስጥ የተመለከቱ ሌሎች ብዙዎችን የመሳሰሉ ናቸው።

ከፍተኛዎቹ ምልክቶች፦

እነዚህ መከሰታቸው የቅያማ ቀን መቃረቡንና ያ አስፈሪ ታላቅ ቀን መምጫው አጭር ጊዜ ብቻ የቀረው መሆኑን የሚጠቁሙ በጣም የከበዱና የገዘፉ ጉዳዮች ናቸው። እነሱም ዐሥር ምልክቶች ሲሆኑ፣የደጅጃል (ሐሳዊ መሲሕ) መታየት፣የነቢዩ ዒሳ መምጣት፣የየእጁጅና መእጁጅ መታየት፣ሦስት ግዙፍ የምድር መደርበቶች፣አንድ መደርበት በምሥራቅ፣አንድ መደርበት በምዕራብ፣አንድ መደርበት በዐረቢያ ልሳነምድር መከሰት፤የተለየ ጭስ መታየት፣የፀሐይ በምዕራብ በኩል ከመጥለቂያዋ ተመልሳ መውጣት፣የምድር እንስሳ (ዳባህ) መውጣት፣ሰዎችን ወደ መሰብሰቢያው አደባባይ የምትነዳቸው እሳት ናቸው። እነዚህ ምልክቶች የሚታዩት በተከታታይነት ሲሆን፣የመጀመሪያው ከታየ ሌሎቹ ተከታትለው ይመጣሉ።

አራተኛ- በትንሣኤ ቀን የሚከሰቱትን አስፈሪና አንቀጥቃጭ ትእይንቶችና ሁነቶች በሚመለከት በተላለፈው ማመን። ለምሳሌ፦

1-

የታላላቅ ተራሮች ተፍረክርከው መናድና ከመሬት ወለል ጋር እኩል መሆን። አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

( وَتَرَى ٱلۡجِبَالَ تَحۡسَبُهَا جَامِدَةٗ وَهِيَ تَمُرُّ مَرَّ ٱلسَّحَابِۚ )

‹‹ጋራዎችንም እነርሱ እንደ ደመና አስተላለፍ የምታልፍ ስትኾን የቆመች ናት ብለህ የምታስባት ኾና ታያታለህ፤››

[አልነምል፡88]

በተጨማሪም አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

( وَبُسَّتِ ٱلۡجِبَالُ بَسّٗا ٥ فَكَانَتۡ هَبَآءٗ مُّنۢبَثّٗا ٦)

‹‹ተራራዎችም መፍፈርፈርን በተፈረፈሩ ጊዜ (እንደ ተፈጨ ዱቄት በኾኑ ጊዜ)። የተበተነ ብናኝ በኾኑም ጊዜ፤››

[አልዋቅዓህ፡5-6]

አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

( وَتَكُونُ ٱلۡجِبَالُ كَٱلۡعِهۡنِ ٩ )

‹‹ጋራዎችም በተለያዩ ቀለማት እንደ ተነከረ ሱፍ፣(ነፋስ እንደሚያበረው) በሚኾኑበት ቀን።››

[አልመዓሪጅ፡9]

አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

( وَيَسۡؤلُونَكَ عَنِ ٱلۡجِبَالِ فَقُلۡ يَنسِفُهَا رَبِّي نَسۡفٗا ١٠٥ فَيَذَرُهَا قَاعٗا صَفۡصَفٗا ١٠٦ لَّا تَرَىٰ فِيهَا عِوَجٗا وَلَآ أَمۡتٗا ١٠٧ )

‹‹ከጋራዎችም ይጠይቁሃል፤በላቸው፦ ጌታዬ መበተንን ይበትናቸዋል። ትክክል ሜዳም ኾና ይተዋታል። በርሷ ዝቅታና ከፍታን አታይም።››

[ጣሃ፡105-107]

2-

የባሕሮችና የውቅያኖሶች ፍንዳታና ተቀጣጥለው የሚነዱ መሆናቸው። የምድራችንን አብዛኛውን ክፍል የሚሸፍኑ ባሕሮች በዚያ ቀን ተደበላልቀው ይፈነዳሉ። አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(وَإِذَا ٱلۡبِحَارُ فُجِّرَتۡ ٣)

‹‹ባሕሮችም በተከፈቱና በተደበላለቁ ጊዜ፤››

[አልእንፍጣር፡3]

(وَإِذَا ٱلۡبِحَارُ سُجِّرَتۡ ٦)

‹‹ባሕሮችም በተቃጠሉ ጊዜ፤››

[አልተክዊር፡6]

3-

ሰዎች የለመዷት ምድርና ሰማያትም እንዲሁ ይለወጣሉ። ምልክትም ሆነ አሻራ በሌላት ሌላ ምድር ላይ ዳግም ይቀሰቀሳሉ። አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

(يَوۡمَ تُبَدَّلُ ٱلۡأَرۡضُ غَيۡرَ ٱلۡأَرۡضِ وَٱلسَّمَٰوَٰتُۖ وَبَرَزُواْ لِلَّهِ ٱلۡوَٰحِدِ ٱلۡقَهَّارِ ٤٨)

‹‹ምድር በሌላ ምድር የምትለወጥበትን፣ሰማያትም፣(እንደዚሁ)፣አንድ አሸናፊ ለኾነው አላህም (ፍጡራን ሁሉ) የሚገለጹበትን ቀን (አስታውስ)።››

[ኢብራሂም፡48]

ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦

‹‹በቅያማ ቀን ሰዎች እንደ ስንዴ ዳቦ ነጭ አፈርማ በሆነች መሬት ላይ ይሰበሰባሉ።››

(በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ)

ምንም ምልክት የሌላት ነጭ ትሆናለች።

4-

ሰዎች ያልለመዱትን ነገር ይመለከታሉ። ፀሐይና ጨረቃን አንድ ላይ ሆነው ያያሉ። አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

(فَإِذَا بَرِقَ ٱلۡبَصَرُ ٧ وَخَسَفَ ٱلۡقَمَرُ ٨ وَجُمِعَ ٱلشَّمۡسُ وَٱلۡقَمَرُ ٩ يَقُولُ ٱلۡإِنسَٰنُ يَوۡمَئِذٍ أَيۡنَ ٱلۡمَفَرُّ ١٠)

‹‹ዓይንም በዋለለ ጊዜ፤ጨረቃም በጨለመ ጊዜ፤ፀሐይና ጨረቃም በተሰበሰቡ ጊዜ፤ሰው በዚያ ቀን መሻሻው የት ነው ይላል?››

[አልቅያማህ፡7-10]

5-

የቀንዱ መነፋት የዚህች የዱንያ ዓለም የመጨረሻ ፍጻሜ ይሆናል። ያች ቀን ስትመጣ የቀንዱ መነፋት በምድርና በሰማያት ላለው ሕይወት ሁሉ ፍጻሜ ይሰጣል።

( وَنُفِخَ فِي ٱلصُّورِ فَصَعِقَ مَن فِي ٱلسَّمَٰوَٰتِ وَمَن فِي ٱلۡأَرۡضِ إِلَّا مَن شَآءَ ٱللَّهُۖ )

‹‹በቀንዱም ይነፋል፤በሰማያት ውስጥ ያለው ፍጡርና በምድርም ውስጥ ያለው ፍጡር ሁሉ፣አላህ የሻው ሲቀር በድንጋጤ ይሞታል፤››

[አልዙመር፡68]

ከቀንዱ የሚወጣው ድምጽ መገመት ከሚቻለው በላይ ከባድና ነገሮችን ሁሉ የሚያወድም ሲሆን፣የሰማው ሰው መናዘዝም ሆነ ወደ ቤተሰቡና ጓደኞቹ መመለስ አይችልም።

( مَا يَنظُرُونَ إِلَّا صَيۡحَةٗ وَٰحِدَةٗ تَأۡخُذُهُمۡ وَهُمۡ يَخِصِّمُونَ ٤٩ فَلَا يَسۡتَطِيعُونَ تَوۡصِيَةٗ وَلَآ إِلَىٰٓ أَهۡلِهِمۡ يَرۡجِعُونَ ٥٠ )

‹‹እነርሱ የሚከራከሩ ሲኾኑ፣በድንገት የምትይዛቸው የኾነችን አንዲትን ጩኸት እንጂ ሌላን አይጠባበቁም። (ያን ጊዜ) መናዘዝንም አይችሉም፤ወደ ቤተሰቦቻቸውም አይመለሱም።››

[ያሲን፡49-50]

ነቢዩም ﷺ እንዲህ ብለዋል፦

‹‹ከዚያም በቀንዱ ይነፋና አንገቱን የሚያዘነብልና ቀና የሚያደርግ ቢሆን እንጅ ማንም አይሰማውም። መጀመሪያ የሚሰማው ሰው ለግመሎቹ የመጠጫ ኩሬውን የሚመርግ ሰው ሲሆን በድንጋጤውና በእንቅጥቃጤው ይሞታል፤ሰዎችም ይሞታሉ።››

(በሙስሊም የተዘገበ)

6-

አላህ ﷻ በመሰባሰቢያው ምድር ላይ ከመጀመሪያው አንስቶ የፈጠራቸውን ፍጥረታት ሁሉ ይሰበስባቸዋል። በዚያች ምድር ላይ ሁሉም ሰውና ጋኔኑም እንስሳት እንኳ ሳይቀሩ ከመጀመሪያ እስከመጨረሻ ይሰበሰቡባታል። አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

(إِنَّ فِي ذَٰلِكَ لَأٓيَةٗ لِّمَنۡ خَافَ عَذَابَ ٱلۡأٓخِرَةِۚ ذَٰلِكَ يَوۡمٞ مَّجۡمُوعٞ لَّهُ ٱلنَّاسُ وَذَٰلِكَ يَوۡمٞ مَّشۡهُودٞ ١٠٣)

‹‹በዚህ ውስጥ የመጨረሻውን ቀን ቅጣት ለሚፈሩ ሁሉ መገሠጫ አልለ። ይህ (የትንሣኤ ቀን)፣ሰዎች በርሱ የሚሰበሰቡበት ቀን ነው፤ይህም የሚጣዱት ቀን ነው።››

[ሁድ፡103]

በተጨማሪም ﷻ እንዲህ ብሏል፦

(قُلۡ إِنَّ ٱلۡأَوَّلِينَ وَٱلۡأٓخِرِينَ ٤٩ لَمَجۡمُوعُونَ إِلَىٰ مِيقَٰتِ يَوۡمٖ

مَّعۡلُومٖ ٥٠)

‹‹በላቸው፦ ፊተኞቹም ኋለኞቹም። በተወሰነ ቀነ ቀጠሮ በእርግጥ ተሰብሳቢዎች ናቸው።››

[አልዋቅዓህ፡49-50]

7-

ሰዎች አላህ እንደፈጠራቸው ራቆታቸውን ሆነው ይሰበሰባሉ። ከትእይንቱ አስጨናቂነትና አስበርጋጊነት የተነሳ አንዱ ሌላውን የሚያይበት ሁኔታ የለም። እመ ምእመናን ዓእሻ (ረ.ዐ) በዚህ ሁኔታ ተገርመዋል። ይህን በተመለከተ ባስተላለፉት ሐዲሥ እንዲህ ብለዋል፦

የአላህ መልክተኛ ﷺ ፦ ‹‹ያለ ጫማ፣ራቆታችሁን፣ያልተገረዛችሁ ሆናችሁ ትሰበሰባላችሁ›› ሲሉ፣የአላህ መልክተኛ ሆይ! ወንዶችና ሴቶች አንዱ ሌላውን እየተመለከተ? አልኳቸው። እሳቸውም፦ ‹‹ሁኔታው ያ የሚያሳስባቸው ከመሆን እጅግ የከበደ ነው›› አሉ።

(በቡኻሪ የተዘገበ)

8-

እንስሳት እንኳ ሳይቀሩ ተበዳይ በዳይን ይበቀላል። ነቢዩﷺ እንዲህ ብለዋል፦

‹‹ቀንድ ለሌላት ፍየል ቀንድ ባላት ፍየል ላይ በቀሏ እስኪወሰድላት ድረስ፣በትንሣኤ ቀን የተጣሱ መብቶችን ለባለቤቶቻቸው በእርግጥ ትጠየቁበታላችሁ።››

(በሙስሊም የተዘገበ)

ነቢዩﷺ እንዲህ ብለዋል፦

‹‹በክብሩም ሆነ በሌላ ነገር በወንድሙ ላይ በደል የፈጸመ ሰው፣ዲናርም ሆነ ድርሀም የማይኖሩ ከመሆናቸው በፊት ዛሬውኑ ራሱን ነጻ ያድርግ። መልካም ሥራ ያለው ከሆነ በበደሉ ልክ ይወሰድበታል፤በጎ ሥራዎች ከሌሉት ደግሞ ከተበዳዩ ኃጢአቶች ተወስደው በርሱ ላይ ይቆለላሉ።››

(በቡኻሪ የተዘገበ)

9-

ሰዎች እንደ ሥራዎቻቸው ደረጃ በገዛ ላባቸው እስኪጥለቀለቁ ድረስ ፀሐይ ወደ አናታቸው ትቀርባለች። ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦

‹‹በትንሣኤ ቀን፣ፀሐይ ወደ ፍጥረታት እስከ አንድ ማይል ድረስ ትቀርባለች፤(ሚል ሲሉ የርቀት መለኪያ ይሁን ወይም የዓይን መኳያ እንጨት ማለታቸው ይሁን ግን በእርግጥ አላውቅም፣ብለዋል ዘጋቢው እብን ዓምር)። የሰዎች ላብ መጠንም እንደ ሥራዎቻቸው ደረጃ ሲሆን፣ላቡ እስከ ቁርጭምጭሚቶች የሚደርስ፣ላቡ እስከ ጉልበቶቹ የሚደርስ፣ላቡ እስከ ዳሌው የሚደርስ፣ላቡ አጥለቅልቆት ከአፉ ደርሶ የሚለጉመው ይገኝባቸዋል።›› ካሉ በኋላ ረሱል ﷺበእጃቸው ወደ አፋቸው አመለከቱ።

(በሙስሊም የተዘገበ)

10-

መጽሐፉን በቀኝ እጁ የሚወስድና በግራ እጁ የሚወስድ ሲኖር፣እያንዳንዱ ሰው መጽሐፉ ወደ እጁ እስኪገባ ድረስ ሰዎች በግራ መጋባት፣በፍርሃትና በስጋት ውስጥ እንደ ዋለሉ ይቆያሉ። ለሙእምኖች መጽሐፎቻቸው በቀኝ እጆቻቸው ሲሰጧቸው መዳኛቸው በመቃረቡ ይጽናናሉ። ከሓዲዎችና መናፍቃን ግን መጽሐፎቻቸው በግራ እጃቸው ሲሰጧቸው ተገቢ ዋጋቸውን በማግኘታቸው ጭንቀትና ውጥረታቸው ይጨምራል። አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

( فَأَمَّا مَنۡ أُوتِيَ كِتَٰبَهُۥ بِيَمِينِهِۦ فَيَقُولُ هَآؤُمُ ٱقۡرَءُواْ كِتَٰبِيَهۡ ١٩ إِنِّي ظَنَنتُ أَنِّي مُلَٰقٍ حِسَابِيَهۡ ٢٠ فَهُوَ فِي عِيشَةٖ رَّاضِيَةٖ ٢١ فِي جَنَّةٍ عَالِيَةٖ ٢٢ قُطُوفُهَا دَانِيَةٞ ٢٣ كُلُواْ وَٱشۡرَبُواْ هَنِيٓئا بِمَآ أَسۡلَفۡتُمۡ فِي ٱلۡأَيَّامِ ٱلۡخَالِيَةِ ٢٤ وَأَمَّا مَنۡ أُوتِيَ كِتَٰبَهُۥ بِشِمَالِهِۦ فَيَقُولُ يَٰلَيۡتَنِي لَمۡ أُوتَ كِتَٰبِيَهۡ ٢٥ وَلَمۡ أَدۡرِ مَا حِسَابِيَهۡ ٢٦ يَٰلَيۡتَهَا كَانَتِ ٱلۡقَاضِيَةَ ٢٧ مَآ أَغۡنَىٰ عَنِّي مَالِيَهۡۜ ٢٨ هَلَكَ عَنِّي سُلۡطَٰنِيَهۡ ٢٩ )

‹‹መጽሐፉን በቀኙ የተሰጠ ሰውማ፣(ለጓደኞቹ) እንኩ፤መጽሐፌን አንብቡ ይላል። እኔ ምርመራየን የምገናኝ መኾኑን አረጋገጥኩ፤(ተዘጋጀሁም፣ይላል)። እርሱም በተወደደች ኑሮ ውስጥ ይኾናል። በከፍተኛይቱ ገነት ውስጥ። ፍሬዎችዋ ቅርቦች የኾኑ። በአለፉት ቀናት ውስጥ (በምድረ ዓለም) ባስቀደማችሁት ምክንያት ብሉ፤ጠጡም፤(ይባላሉ)። መጽሐፉንም በግራው የተሰጠውማ ዋ ጥፋቴ! ምነው መጽሐፌን ባልተሰጠሁ፣ይላል። ምርመራየንም ምን እንደ ኾነ ባላወቅሁ። እርሷ (ሞት፣ሕይወቴን) ምነው ፈጻሚ በኾነች (እንደ ሞትኩ ዳግም ሳልነሳ በቀረሁ)። ገንዘቤ ከኔ ምንንም አላብቃቃኝ፤(አልጠቀመኝም)። ኀይሌ ከኔ ላይ ጠፋ (ይላል)።››

[አልሓቃህ፡19-29]

11-

በሁኔታው አስጨናቂነትና በሰፈነው ከባድ ጭንቀትና ውጥረት ምክንያት፣ሰው በነፍስ አውጭኝ ስለራሱ ብቻ መጨነቅ እንጂ ማንንም አይጠይቅም። አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

(يَوۡمَ لَا يَنفَعُ مَالٞ وَلَا بَنُونَ ٨٨)

‹‹ገንዘብም ልጆችም በማይጠቅሙበት ቀን፤››

[አልሹዐራእ፡88]

አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(يَوۡمَ يَفِرُّ ٱلۡمَرۡءُ مِنۡ أَخِيهِ ٣٤ وَأُمِّهِۦ وَأَبِيهِ ٣٥ وَصَٰحِبَتِهِۦ وَبَنِيهِ ٣٦ لِكُلِّ ٱمۡرِيٕٖ مِّنۡهُمۡ يَوۡمَئِذٖ شَأۡنٞ يُغۡنِيهِ ٣٧)

‹‹ሰው ከወንድሙ በሚሸሽበት ቀን፣ከናቱም፣ካባቱም፣ከሚስቱም፣ከልጁም፣ከነሱ ሌላው ሁሉ በዚህ ቀን (ከሌላው) የሚያብቃቃው ኹኔታ አልለው (ለራሱ ብቻ ማሰብና መጨነቅ ይኖርበታል)።››

[ዐበሰ፡34-37]

አምስተኛ- ምርመራና ለሁሉም እንደሥራው የሚሰጥ መሆኑን ማመን፦

አንድ የአላህ ባሪያ በዚህ ዓለም ላይ በፈጸማቸው ነገሮች ሁሉ የሚጠየቅና የሚመረመር ሲሆን፤ሁሉም የሥራውን ዋጋ ይቀበላል። አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

(إِنَّ إِلَيۡنَآ إِيَابَهُمۡ ٢٥ ثُمَّ إِنَّ عَلَيۡنَا حِسَابَهُم ٢٦)

‹‹መመለሻቸው ወደኛ ብቻ ነው። ከዚያም ምርመራቸው በኛ ላይ ብቻ ነው።››

[አልጋሽያህ፡25-26]

አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

(مَن جَآءَ بِٱلۡحَسَنَةِ فَلَهُۥ عَشۡرُ أَمۡثَالِهَاۖ وَمَن جَآءَ بِٱلسَّيِّئَةِ فَلَا يُجۡزَىٰٓ إِلَّا مِثۡلَهَا وَهُمۡ لَا يُظۡلَمُونَ ١٦٠)

‹‹በመልካም ሥራ የመጣ ሰው፣ለርሱ ዐሥር ብጤዎችዋ አሉት፤በክፉ ሥራም የመጣ ሰው፣ብጤዋን እንጅ አይመነዳም፤እነርሱም አይበደሉም።››

[አልአንዓም፡160]

አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

(وَنَضَعُ ٱلۡمَوَٰزِينَ ٱلۡقِسۡطَ لِيَوۡمِ ٱلۡقِيَٰمَةِ فَلَا تُظۡلَمُ نَفۡسٞ شَيۡئاۖ وَإِن كَانَ مِثۡقَالَ حَبَّةٖ مِّنۡ خَرۡدَلٍ أَتَيۡنَا بِهَاۗ وَكَفَىٰ بِنَا حَٰسِبِينَ ٤٧)

‹‹በትንሣኤም ቀን፣ትክክለኛ ሚዛኖችን እናቆማለን፣ማንኛይቱም ነፍስ ምንንም አትበደልም፤(ሥራው) የሰናፈጭ ቅንጣት ያክል ቢኾንም እርሷን እናመጣታለን፤ተቆጣጣሪዎችም በኛ በቃ።››

[አልአንቢያ፡47]

ከእብን ዐመር (ረ.ዐ) በተላለፈው መሰረት ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦

‹‹አላህ ሙእምን የሆነውን ሰው ያቀርበውና መከለያውን በርሱ ላይ በማድረግ ይሸፍነዋል። እንዲህ ያለውን ኃጢአትህን ታውቃለህ? እንደዚያ ያለውን ኃጢአትህንስ ታውቃለህ? ይለዋል። አዎ ጌታዬ አውቃለሁ ብሎ ኃጢአቱን አምኖ ሲቀበልና በቃ ጠፋሁ ብሎ በውስጡ ሲያስብ፣በዱንያ ላይ ሸፍኜልሃለሁ፣እነሆ ዛሬም እምርሃለሁ፣ይለዋል። ከዚያም የበጎ ሥራዎቹ መዝገብ ይሰጠዋል። ከሓዲዎችና መናፍቃን ግን በፍጥረታት ፊት፦

(هؤلاء ٱلَّذِينَ كَذَبُواْ عَلَىٰ رَبِّهِمۡۚ أَلَا لَعۡنَةُ ٱللَّهِ عَلَى ٱلظَّٰلِمِينَ ١٨)

‹‹፦ እነዚህ በጌታቸው ላይ የዋሹት ናቸው ይላሉ፤ንቁ የአላህ ርግማን በበዳዮች ላይ ይኹን።›› ተብሎ ይታወጅባቸዋል።

[ሁድ፡18]

(በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ)

ነቢዩﷺ ከጌታቸው በሚተላለፍላቸው የሚከተለውን ማለታቸው ተረጋግጧል፦

‹‹አላህ ሰናይ ሥራዎችንና እኩይ ሥራዎችንንም የመዘገበ ሲሆን፣ሁሉንም አብርርቷል። በጎ ነገር ለመሥራት አስቦ ላልሠራው ሰው አንድ ሙሉ በጎ ሥራ (ምንዳውን) እርሱ ዘንድ ይመዘግብለታል። ካሰበውና ከሠራው ደግሞ ከዐሥር እስከ ሰባት መቶ ብዙ እጥፍ ድርብ በጎ ሥራዎችን (ምንዳ) ይመዘግብለታል። ክፉ መሥራት አስቦ ያልሰራው ከሆነ ደግሞ ሙሉ በጎ ሥራ ይመዘግብለታል። ክፉ ሥራ ካሰበና ከሠራ አንድ ክፉ ሥራ ብቻ ይመዘግብበታል።››

(በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ)

ሐሰን አልበስሪ፣‹‹ከሰሓባ ትውልድ የቀጠሉት ታብዕዮች በዕባዳ ብዛት ከሶሓባ የሚበልጡ መሆናቸውን አይተናል፤እናም ሶሓባ በምንድን ነው የቀደሟቸው?›› ተብለው ሲጠየቁ ‹‹እነዚህ ዕባዳ የሚያደርጉት ልቦቻቸው ውስጥ ዱንያን በማኖር ነው፤ሶሓባ ደግሞ ዕባዳ ያደረጉት በልቦቻቸው ውስጥ ኣኽራን አስቀምጠው ነው።›› ብለዋል።

ሰዎች በዚህ ዓለም በሚሠሩት ሥራ የሚጠየቁና የሚመረመሩ፣እንደሥራቸውም ዋጋቸውን የሚያገኙ መሆናቸው የተረጋገጠ በመሆኑ ላይ ሙስሊሞች በሙሉ ድምጽ ተስማምተዋል። ይህም በጥበብ ላይ የተመሰረተ ሲሆን፣አላህ ﷻ መጻሕትን አውርዷል፤መልክተኞችን ልኳል፤በባሮቹ ላይ ማመንንና መታዘዝን ግዴታ አድርጓል። በርሱና በመልክተኞቹ በላመነውና ትእዛዛቸውን በጣሰው ሰው ላይ፣አሳማሚ ቅጣት እንደሚጠብቀው ከባድ ማስጠንቀቂያ አስተላልፎበታል። ምርመራም ሆነ የሥራ ዋጋ ባይኖር ኖሮ ሕይወት ከንቱ በሆነች ነበር። አላህﷻ ግን ከዚህ ፍጹም የጠራ ነው። አላህ ﷻ ይህንኑ ሲጠቁም እንዲህ ብሏል፦

(فَلَنَسۡئلَنَّ ٱلَّذِينَ أُرۡسِلَ إِلَيۡهِمۡ وَلَنَسۡئلَنَّ ٱلۡمُرۡسَلِينَ ٦ فَلَنَقُصَّنَّ عَلَيۡهِم بِعِلۡمٖۖ وَمَا كُنَّا غائبين ٧)

‹‹እነዚያንም ወደነሱ የተላከባቸውን (ሕዝቦች) በእርግጥ እንጠይቃቸዋለን። በነርሱም ላይ (የነበሩበትን ሁሉ) ከዕውቀት ጋር በእርግጥ እንተርክላቸዋለን፤የራቅንም አልነበርንም።››

[አልአዕራፍ፡6-7]

ስድስተኛ- በጀነትና በጀሀነም እሳት መኖር ማመን፦

እነዚህ ሁለቱ የፍጥረታት የመጨረሻው መመለሻ ናቸው። ጀነት፣እንዲያምኑባቸው ግዴታ ባደረገባቸው ነገሮች ላመኑ፣አላህንና መልክተኛውን በቅንነት ለታዘዙ፣ለአላህ ፍጹም ሆነው የመልክተኛውን ፈለገ ሕይወት ለተከተሉ፣ትጉሃን ምእመናን አላህ ﷻ ያሰናዳላቸው የድሎት አገር ነው። ጀነት ውስጥ ‹‹ዓይን አይቶት፣ጆሮም ሰምቶት፣በሰው አእምሮም ታስቦ የማያውቅ›› ድሎትና የምቾት ዓይነቶች ያሉበት አገር ነው። አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

(إِنَّ ٱلَّذِينَ ءَامَنُواْ وَعَمِلُواْ ٱلصَّٰلِحَٰتِ أُوْلَٰٓئِكَ هُمۡ خَيۡرُ ٱلۡبَرِيَّةِ ٧ جَزَآؤُهُمۡ عِندَ رَبِّهِمۡ جَنَّٰتُ عَدۡنٖ تَجۡرِي مِن تَحۡتِهَا ٱلۡأَنۡهَٰرُ خَٰلِدِينَ فِيهَآ أَبَدٗاۖ رَّضِيَ ٱللَّهُ عَنۡهُمۡ وَرَضُواْ عَنۡهُۚ ذَٰلِكَ لِمَنۡ خَشِيَ رَبَّهُۥ ٨)

‹‹እነዚያ ያመኑትና መልካሞችንም የሠሩት፣እነዚያ እነሱ ከፍጥረት ሁሉ በላጭ ናቸው። በጌታቸው ዘንድ ምንዳቸው ከሥሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸው የመኖሪያ ገነቶች ነው፤በውስጣቸው ዘለዓለም ዘውታሪዎች ሲኾኑ፣(ይገቡባቸዋል)። አላህ ከነሱ ወደደ፤ከርሱም ወደዱ፤ይህ ጌታውን ለፈራ ሰው ነው።››

[አልበይይናህ፡7-8]

በተጨማሪም አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

( فَلَا تَعۡلَمُ نَفۡسٞ مَّآ أُخۡفِيَ لَهُم مِّن قُرَّةِ أَعۡيُنٖ جَزَآءَۢ بِمَا كَانُواْ يَعۡمَلُونَ ١٧ )

‹‹ይሠሩትም በነበሩት ለመመንዳት፣ከዓይኖች መርጊያ ለነሱ የተደበቀላቸውን (ጸጋ) ማንኛይቱም ነፍስ አታውቅም።››

[አልሰጅዳህ፡17]

ከጀነት ድሎቶችና ደስታዎች ሁሉ ትልቁ ወደ አላህ ﷻ ፊት መመልከት። አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

( وُجُوهٞ يَوۡمَئِذٖ نَّاضِرَةٌ ٢٢ إِلَىٰ رَبِّهَا نَاظِرَةٞ ٢٣ )

‹‹ፊቶች በዚያ ቀን አብሪዎች ናቸው። ወደ ጌታቸው ተመልካቾች ናቸው።››

[አልቅያማህ፡22-23]

በተጨማሪም አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

(لِّلَّذِينَ أَحۡسَنُواْ ٱلۡحُسۡنَىٰ وَزِيَادَةٞۖ )

‹‹ለነዚያ መልካም ለሠሩት መልካም ነገርና ጭማሪም አላቸው፤››

[ዩኑስ፡26]

መልካሙ ነገር ‹‹አልሑስና›› ማለት ጀነት ስትሆን፣ጭማሪው የአላህን ﷻ ፊት ስብሐት መመልከት ነው። ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦

‹‹የጀነት ሰዎች ወደ ጀነት ሲገቡ፣አላህ ﷻ ፦ ’ምጨምርላችሁ ነገር አለን? ይላል። ፊታችንን አንጽተህልን የለምን? ጀነት አስገብህተን ከእሳት አድነኸን የለምን? ይላሉ። በዚህ ጊዜ መጋረጃውን ይገልጣል። ወደ ጌታቸው ﷻ ከመመልከት ይበልጥ ለነሱ ተወዳጅ የሆነ ምንም ነገር አልተሰጡም።›› የአላህ መልክተኛ ﷺ በመቀጠል ይህን የቁርኣን አንቀጽ አሰሙ፦

(لِّلَّذِينَ أَحۡسَنُواْ ٱلۡحُسۡنَىٰ وَزِيَادَةٞۖ )

‹‹ለነዚያ መልካም ለሠሩት መልካም ነገርና ጭማሪም አላቸው፤››

[ዩኑስ፡26]

(በሙስሊም የተዘገበ)

እሳት ደግሞ በርሱ ላስተባበሉና በመልእክተኞቹ ላይ ላመጹ ከሓዲዎችና ግፈኞች አላህ ﷻ የደገሰላቸው የመሰቃያ ቦታ ስትሆን፣አእምሮ ሊገምታቸው የማይችል ሁሉም የስቃይና የሰቆቃ ዓይነቶች ይገኙባታል። አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(وَٱتَّقُواْ ٱلنَّارَ ٱلَّتِيٓ أُعِدَّتۡ لِلۡكَٰفِرِينَ ١٣١)

‹‹ያችንም ለከሓዲዎች የተደገሰችውን እሳት ተጠንቀቁ።››

[ኣል ዒምራን፡131]

በተጨማሪም አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

(إِنَّآ أَعۡتَدۡنَا لِلظَّٰلِمِينَ نَارًا أَحَاطَ بِهِمۡ سُرَادِقُهَاۚ وَإِن يستغيثوا يُغَاثُواْ بِمَآءٖ كَٱلۡمُهۡلِ يَشۡوِي ٱلۡوُجُوهَۚ بِئۡسَ ٱلشَّرَابُ وَسَآءَتۡ مُرۡتَفَقًا ٢٩)

‹‹እኛ ለበደለኞች አጥርዋ በነሱ የከበበ የኾነችውን እሳት አዘጋጅተናል፤(ከጥም) እርዳታንም ቢፈልጉ እንደ ዘይት ዝቃጭ ባለ፣ፊቶችን በሚጠብስ ውሃ ይረዳሉ፤መጠጡ ከፋ! መደገፊያይቱም ምንኛ አስከፋች!››

[አልከህፍ፡29]

አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(إِنَّ ٱللَّهَ لَعَنَ ٱلۡكَٰفِرِينَ وَأَعَدَّ لَهُمۡ سَعِيرًا ٦٤ خَٰلِدِينَ فِيهَآ أَبَدٗاۖ لَّا يَجِدُونَ وَلِيّٗا وَلَا نَصِيرٗا ٦٥ يَوۡمَ تُقَلَّبُ وُجُوهُهُمۡ فِي ٱلنَّارِ يَقُولُونَ يَٰلَيۡتَنَآ أَطَعۡنَا ٱللَّهَ وَأَطَعۡنَا ٱلرَّسُولَا۠ ٦٦)

‹‹አላህ ከሓዲዎችን በእርግጥ ረግሟቸዋል፤ለነርሱም የተጋጋመችን እሳት አዘጋጅቷል። በርሷ ውስጥ ዘለዓለም ዘውታሪዎች ሲኾኑ፤ወዳጅም ረዳትም አያገኙም። ፊቶቻቸው በእሳት ውስጥ በሚገለባበጡ ቀን፣ዋ ምኞታችን! አላህን በተገዛን፣መልክተኛውንም በታዘዝን ኖሮ እያሉ ይጸጸታሉ።››

[አልአሕዛብ፡64-66]

በጀሀነም እሳት ውስጥ - አላህ ይጠብቀንና - ስቃዩ አነስ የሚለው ነቢዩﷺ እንዲህ ሲሉ የገለጹት ሰው ነው፦

‹‹በትንሣኤ ቀን ከእሳት ሰዎች ሁሉ ቅጣቱ አነስ ያለ ነው የሚባለው፣በሁለት የውስጥ እግሮቹ አንጎሉን የሚያቀልጥ ፍም የሚደረግለት ሰው ነው።››

(በቡኻሪ የተዘገበ)

በመጨረሻው ቀን የማመን ፍሬዎች፦

1-

በአላህ ማመን በመጨረሻው ቀን በማመን እንጂ እውን የማይሆን ከመሆኑ አንጻር፣ከኢማን ማእዘናት ውስጥ አንዱን ማእዘን እውን ያደርጋል። ለዚህ ነው አላህ ﷻ በርሱ የማያምኑትን መዋጋት ግዴታ ያደረገብን። አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

(قَٰتِلُواْ ٱلَّذِينَ لَا يُؤۡمِنُونَ بِٱللَّهِ وَلَا بِٱلۡيَوۡمِ ٱلۡأٓخِرِ)

‹‹እነዚያን በአላህና በመጨረሻው ቀን የማያምኑትን፣ . . . ተዋጉዋቸው።››

[አልተውባህ፡29]

2-

በዱንያም ሆነ በወዲያኛው የኣኽራ ሕይወት ከፍርሃት መጠበቅና የደህንነት ዋስትና ማግኘት። አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

( أَلَآ إِنَّ أَوۡلِيَآءَ ٱللَّهِ لَا خَوۡفٌ عَلَيۡهِمۡ وَلَا هُمۡ يَحۡزَنُونَ ٦٢ )

‹‹ንቁ፣የአላህ ወዳጆች በነሱ ላይ ፍርሃት የለባቸውም፤እነሱም አያዝኑም።››

[ዩኑስ፡62]

3-

ታላቅ ምንዳና ሽልማት የማግኘት ቃል ኪዳን የተሰጠ መሆኑ። አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

( إِنَّ ٱلَّذِينَ ءَامَنُواْ وَٱلَّذِينَ هَادُواْ وَٱلنَّصَٰرَىٰ وَٱلصَّٰبِئينَ مَنۡ ءَامَنَ بِٱللَّهِ وَٱلۡيَوۡمِ ٱلۡأٓخِرِ وَعَمِلَ صَٰلِحٗا فَلَهُمۡ أَجۡرُهُمۡ عِندَ رَبِّهِمۡ وَلَا خَوۡفٌ عَلَيۡهِمۡ وَلَا هُمۡ يَحۡزَنُونَ ٦٢ )

‹‹እነዚያ ያመኑ፣እነዚያም ይሁዳውያን የኾኑ፣ክርስቲያኖችም፣ሳቢያኖችም፣(ከነርሱ) በአላህና በመጨረሻው ቀን ያመነ፣መልካምንም ሥራ የሠራ፣ለነርሱ በጌታቸው ዘንድ ምንዳቸው አላቸው፤በነርሱም ላይ ፍርሃት የለባቸውም፤እነሱም አያዝኑም።››

[አልበቀራህ፡62]

4-

ሰናይ ሥራዎች እንዲሠራ ያበረታታል ። አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

( يَٰٓأَيُّهَا ٱلَّذِينَ ءَامَنُوٓاْ أَطِيعُواْ ٱللَّهَ وَأَطِيعُواْ ٱلرَّسُولَ وَأُوْلِي ٱلۡأَمۡرِ مِنكُمۡۖ فَإِن تَنَٰزَعۡتُمۡ فِي شَيۡءٖ فَرُدُّوهُ إِلَى ٱللَّهِ وَٱلرَّسُولِ إِن كُنتُمۡ تُؤۡمِنُونَ بِٱللَّهِ وَٱلۡيَوۡمِ ٱلۡأٓخِرِۚ ذَٰلِكَ خَيۡرٞ وَأَحۡسَنُ تَأۡوِيلًا ٥٩ )

‹‹እላንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን ተገዙ፤መልክተኛውንና ከናንተም የሥልጣን ባለቤቶችን ታዘዙ፤በማንኛውም ነገር ብትከራከሩ፣በአላህና በመጨረሻው ቀን የምታምኑ ብትኾኑ (የተከራከራችሁበትን ነገር) ወደ አላህና ወደ መልክተኛው መልሱት፤ይህ የተሻለ፣መጨረሻውም ያማረ ነው።››

[አልኒሳእ፡59]

አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

( إِنَّمَا يَعۡمُرُ مَسَٰجِدَ ٱللَّهِ مَنۡ ءَامَنَ بِٱللَّهِ وَٱلۡيَوۡمِ ٱلۡأٓخِرِ)

‹‹የአላህን መስጊዶች የሚሠራው፣በአላህና በመጨረሻው ቀን ያመነ፣ . . . ሰው ብቻ ነው፤››

[አልተውባህ፡18]

በተጨማሪም ﷻ እንዲህ ብሏል፦

( لَّقَدۡ كَانَ لَكُمۡ فِي رَسُولِ ٱللَّهِ أُسۡوَةٌ حَسَنَةٞ لِّمَن كَانَ يَرۡجُواْ ٱللَّهَ وَٱلۡيَوۡمَ ٱلۡأٓخِرَ وَذَكَرَ ٱللَّهَ كَثِيرٗا ٢١ )

‹‹ለናንተ፣አላህንና የመጨረሻውን ቀን የሚከጅል ለኾነ ሰው፣አላህንም በብዙ ለሚያወሳ፣በአላህ መልክተኛ መልካም መከተል [አርአያ] አላቸው።››

[አልአሕዛብ፡21]

በተጨማሪም አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

( لَقَدۡ كَانَ لَكُمۡ فِيهِمۡ أُسۡوَةٌ حَسَنَةٞ لِّمَن كَانَ يَرۡجُواْ ٱللَّهَ وَٱلۡيَوۡمَ ٱلۡأٓخِرَۚ)

‹‹ለናንተ አላህንና የመጨረሻውን ቀን ለሚፈራ ሰው፣በነርሱ መልካም መከተል [አርአያ] አላችሁ።››

[አልሙምተሕናህ፡6]

አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(وَأَقِيمُواْ ٱلشَّهَٰدَةَ لِلَّهِۚ ذَٰلِكُمۡ يُوعَظُ بِهِۦ مَن كَانَ يُؤۡمِنُ بِٱللَّهِ وَٱلۡيَوۡمِ ٱلۡأٓخِرِۚ)

‹‹ምስክርነትንም ለአላህ አስተካክሉ፤ይሃችሁ በአላህና በመጨረሻው ቀን የሚያምን የኾነ ሰው ሁሉ በርሱ ይገሠጽበታል፤››

[አልጦላቅ፡2]

እመ ምእመናን ዓእሻ (ረ.ዐ) ለአንዲት ሴት እንዲህ ብለዋል፦ ሞትን ማስታወስ አብዢ፣ ልብሽ ያለሰልሳልና።

5-

እኩይና መጥፎ ነገሮችን ከመስራት ይከለክላል። ጌታችንﷻ እንዲህ ብሏል፦

(وَلَا يَحِلُّ لَهُنَّ أَن يَكۡتُمۡنَ مَا خَلَقَ ٱللَّهُ فِيٓ أَرۡحَامِهِنَّ إِن كُنَّ يُؤۡمِنَّ بِٱللَّهِ وَٱلۡيَوۡمِ ٱلۡأٓخِرِۚ)

‹‹በአላህና በመጨረሻው ቀን የሚያምኑ ቢኾኑ፣አላህ በማሕጸኖቻቸው ውስጥ የፈጠረውን ሊደብቁ ለነርሱ አይፈቀድላቸውም፤››

[አልበቀራህ፡228]

በተጨማሪም አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

( وَإِذَا طَلَّقۡتُمُ ٱلنِّسَآءَ فَبَلَغۡنَ أَجَلَهُنَّ فَلَا تَعۡضُلُوهُنَّ أَن يَنكِحۡنَ أَزۡوَٰجَهُنَّ إِذَا تَرَٰضَوۡاْ بَيۡنَهُم بِٱلۡمَعۡرُوفِۗ ذَٰلِكَ يُوعَظُ بِهِۦ مَن كَانَ مِنكُمۡ يُؤۡمِنُ بِٱللَّهِ وَٱلۡيَوۡمِ ٱلۡأٓخِرِۗ )

‹‹ሴቶችን በፈታችሁና ጊዜያቸውን በደረሱ ጊዜ፣በመካከላቸው በሕግ በተዋደዱ ጊዜ፣ባሎቻቸውን ከማግባት አታስተጓጉሏቸው፣ይህ (መከልከል) ከናንተ በአላህና በመጨረሻው ቀን የሚያምን በርሱ ይገሠጽበታል።››

[አልበቀራህ፡232]

አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

( لَا يَسۡتَئذِنُكَ ٱلَّذِينَ يُؤۡمِنُونَ بِٱللَّهِ وَٱلۡيَوۡمِ ٱلۡأٓخِرِ أَن يُجَٰهِدُواْ بِأَمۡوَٰلِهِمۡ وَأَنفُسِهِمۡۗ وَٱللَّهُ عَلِيمُۢ بِٱلۡمُتَّقِينَ ٤٤ إِنَّمَا يَسۡتَٔۡذِنُكَ ٱلَّذِينَ لَا يُؤۡمِنُونَ بِٱللَّهِ وَٱلۡيَوۡمِ ٱلۡأٓخِرِ وَٱرۡتَابَتۡ قُلُوبُهُمۡ فَهُمۡ فِي رَيۡبِهِمۡ يَتَرَدَّدُونَ ٤٥ )

‹‹እነዚያ በአላህና በመጨረሻው ቀን የሚያምኑት፣በገንዘቦቻቸውና በነፍሶቻቸው ከመታገላቸው (ለመቅረት) ፈቃድን አይጠይቁህም፤አላህም የሚፈሩትን ዐዋቂ ነው። ፈቃድን የሚጠይቁህ፣እነዚያ በአላህና በመጨረሻው ቀን የማያምኑት፣ልቦቻቸውም የተጠራጠሩት ብቻ ናቸው፤እነሱም በጥርጣሬያቸው ውስጥ ይዋልላሉ።››

[አልተውባህ፡44-45]

ስለዚህም በዚህ ቀን የማያምን ከሃዲ፣ሐራም የሆኑ ድርጊቶችን ከመፈጸም አይቆጠብም፤ያን ማድረግም አያሳፍረውም።

( أَرَءَيۡتَ ٱلَّذِي يُكَذِّبُ بِٱلدِّينِ ١ فَذَٰلِكَ ٱلَّذِي يَدُعُّ ٱلۡيَتِيمَ ٢ وَلَا يَحُضُّ عَلَىٰ طَعَامِ ٱلۡمِسۡكِينِ ٣ )

‹‹ያንን በምርመራው የሚያስተባብለውን አየህን? (ዐወቅከውን?) ይህም ያ የቲምን በኀይል የሚገፈትረው፤ድኻንም በማብላት ላይ የማያግባባው ሰው ነው።››

[አልማዑን፡1-3]

ሐሰን (ረ.ዐ) እንዲህ ብለዋል፦ ሞትን ያወቀ ሰው፣የዱንያ ችግሮች ሁሉ ቀላል ይሆኑበታል።

6-

አማኙን ሰው በዚህ ዓለም ሕይወቱ ያላገኘውንና ያመለጠውን ነገር፣ተስፋ ቃል በተገባለት የወዲያኛው የኣኽራ ሕይወት ተድላና ሽልማት እንዲጽናና ያደርገዋል። ጀነትን ማግኘት ታላቁ ድልና ስኬት ሲሆን፣ይህች የዱንያ ሕይወትና መደሰቻዎቿ የመታለያ መሣሪያ እንጅ ሌላ አይደሉምና። አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

( كُلُّ نَفۡسٖ ذَآئِقَةُ ٱلۡمَوۡتِۗ وَإِنَّمَا تُوَفَّوۡنَ أُجُورَكُمۡ يَوۡمَ ٱلۡقِيَٰمَةِۖ فَمَن زُحۡزِحَ عَنِ ٱلنَّارِ وَأُدۡخِلَ ٱلۡجَنَّةَ فَقَدۡ فَازَۗ وَمَا ٱلۡحَيَوٰةُ ٱلدُّنۡيَآ إِلَّا مَتَٰعُ ٱلۡغُرُورِ ١٨٥ )

‹‹ነፍስ ሁሉ ሞትን ቀማሽ ናት፤ምንዳዎቻችሁንም የምትሞሉት በትንሣኤው ቀን ብቻ ነው። ከእሳትም የተራቀና ገነትን የተገባ ሰው በእርግጥ ምኞቱን አገኘ። ቅርቢቱም ሕይወት የመታለያ መሣሪያ እንጅ ሌላ አይደለችም።››

[ኣል ዒምራን፡185]

በተጨማሪም አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

( قُلۡ إِنِّيٓ أَخَافُ إِنۡ عَصَيۡتُ رَبِّي عَذَابَ يَوۡمٍ عَظِيمٖ ١٥ مَّن يُصۡرَفۡ عَنۡهُ يَوۡمَئِذٖ فَقَدۡ رَحِمَهُۥۚ وَذَٰلِكَ ٱلۡفَوۡزُ

ٱلۡمُبِينُ ١٦ )

‹‹እኔ ጌታዬን ባምጥ [ትእዛዙን ብጥስ] የታላቁን ቀን ቅጣት እፈራለሁ በላቸው። በዚያ ቀን ከርሱ ላይ (ቅጣት) የሚመለስለት ሰው፣(አላህ) በእርግጥ አዘነለት፤ይህም ግልጽ ማግኘት ነው።››

[አልአንዓም፡15-16]

አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

( وَٱلۡأٓخِرَةُ خَيۡرٞ وَأَبۡقَىٰٓ ١٧ )

‹‹መጨረሻይቱ (ሕይወት) በላጭ፣ሁል ጊዜ ዘውታሪም ስትኾን።››

[አልአዕላ፡17]

አማኙን ሰው በዚህ ዓለም ሕይወቱ ያላገኘውንና ያመለጠውን፣ተስፋ ቃል በተገባለት የወዲያኛው የኣኽራ ሕይወት ተድላና ሽልማት እንዲጽናና ያደርገዋል። ጀነትን ማግኘት ታላቁ ድልና ስኬት ሲሆን፣ይህች የዱንያ ሕይወትና መደሰቻዎቿ የመታለያ መሣሪያ እንጅ ሌላ አይደሉምና። አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

كُلُّ نَفۡسٖ ذَآئِقَةُ ٱلۡمَوۡتِۗ وَإِنَّمَا تُوَفَّوۡنَ أُجُورَكُمۡ يَوۡمَ ٱلۡقِيَٰمَةِۖ فَمَن زُحۡزِحَ عَنِ ٱلنَّارِ وَأُدۡخِلَ ٱلۡجَنَّةَ فَقَدۡ فَازَۗ وَمَا ٱلۡحَيَوٰةُ ٱلدُّنۡيَآ إِلَّا مَتَٰعُ ٱلۡغُرُورِ ١٨٥ )

‹‹ነፍስ ሁሉ ሞትን ቀማሽ ናት፤ምንዳዎቻችሁንም የምትሞሉት በትንሣኤው ቀን ብቻ ነው። ከእሳትም የተራቀና ገነትን የተገባ ሰው በእርግጥ ምኞቱን አገኘ። ቅርቢቱም ሕይወት የመታለያ መሣሪያ እንጅ ሌላ አይደለችም።››

[ኣል ዒምራን፡185]

በተጨማሪም አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

( قُلۡ إِنِّيٓ أَخَافُ إِنۡ عَصَيۡتُ رَبِّي عَذَابَ يَوۡمٍ عَظِيمٖ ١٥ مَّن يُصۡرَفۡ عَنۡهُ يَوۡمَئِذٖ فَقَدۡ رَحِمَهُۥۚ وَذَٰلِكَ ٱلۡفَوۡزُ

ٱلۡمُبِينُ ١٦ )

‹‹እኔ ጌታየን ባምጥ [ትእዛዙን ብጥስ] የታላቁን ቀን ቅጣት እፈራለሁ በላቸው። በዚያ ቀን ከርሱ ላይ (ቅጣት) የሚመለስለትን ሰው፣(አላህ) በእርግጥ አዘነለት፤ይህም ግልጽ ማግኘት ነው።››

[አልአንዓም፡15-16]

አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

( وَٱلۡأٓخِرَةُ خَيۡرٞ وَأَبۡقَىٰٓ ١٧ )

‹‹መጨረሻይቱ (ሕይወት) በላጭ፣ሁል ጊዜ ዘውታሪም ስትኾን።››

[አልአዕላ፡17]

ልቦና ጌታውን በማምለክ፣እርሱን በማፍቀርና ወደርሱ በመመለስ እንጂ፣አይበጅም፤ስኬት አያገኝም፤አይደሰትም፤ምቾትን አያጣጥምም፤አይሰምርም፤አይረጋጋም።

ሸይኽ አልእስላምTags: