የአላህንﷻ ስሞችና ባሕርያቱን የማወቅ አስፈላጊነት ፦

የአላህንﷻ  ስሞችና ባሕርያቱን የማወቅ አስፈላጊነት ፦
የአላህንﷻ ስሞችና ባሕርያቱን የማወቅ አስፈላጊነት፣ክቡርነቱና የላቀ ሰፍራው ከሚከተሉት ነጥቦች ግልጽ ይሆናሉ፦

አንደኛ -

ከዕውቀት ሁሉ የተከበረውና የላቀው ዕውቀት፣ከአላህﷻ መልካም ስሞችና ከላቁ ባሕርያቱ ጋር የተያያዘ ዕውቀት ነው። አንድ የአላህ አገልጋይ

ለአላህﷻ የሚኖረው ተገዥነት (ዕባዳው)፣በርሱ የሚኖረው መጽናናት፣ለርሱ የሚኖረውና በልቡ ውስጥ የሚፈጠረው ፍቅርና የርሱ ግርማ ሞገስ፣ለርሱ ﷻ ስሞችና ለባሕርያቱ በሚኖረው ዕውቀት መጠን ነው። ይህም በወዲያኛው የኣኽራ ሕይወት የአላህንﷻ ውዴታና ጀነትን ለማግኘት፣የኃልነትና የግርማ ሞገስ ባለቤት ወደሆነው የአላህﷻ ፊት መመልከትን ለመታደል ምክንያት ይሆናል። ይህ ታላቅ ግብ እውን ሊሆን የሚችለው አላህﷻ በቸርነቱ ሲያሳካው (በርሱ ተውፊቅ) ነው።

ሁለተኛ -

የአላህንﷻ ስሞችና ባሕርያቱን ማወቅ የዕውቀቶች ሁሉ መሰረትና የኢማን የማእዘን ድንጋይ ነው። ከግዴታዎች ሁሉም ቀዳሚው ግዴታ ነው። ሰዎች ጌታቸውን ካወቁት ለርሱ ተገቢው የሆነውን አምልኮ ያመልኩታል። አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(فَٱعۡلَمۡ أَنَّهُۥ لَآ إِلَٰهَ إِلَّا ٱللَّهُ)

‹‹እነሆ ከአላህ ሌላ አምላክ አለመኖሩንም ዕወቅ፤››

[ሙሐመድ፡19]

ሦስተኛ -

አላህንﷻ በስሞቹና በባሕርያቱ ማወቅ ኢማንና እርግጠኝነትን ያሳድጋል፤ተውሒድን እውን ያደርጋል፤የዕባዳን ጥፍጥና እና ጣዕም ይጨምራል። ይህም የኢማን መንፈስ መሰረቱና ዋነኛ ግቡ ነው። ወደዚህ ለመድረስ አጭሩ መንገድ ደግሞ ቁርኣን ውስጥ የሰፈሩትን የአላህንﷻ ስሞችና ባሕርያቱን ማስተዋልና ማስተንን ነው። አላህﷻ አንድ ባሪያውን እርሱን ማወቅና እርሱን ማፍቀር እንዲችል በማድረግ ካከበረው፣የላቁ ባሕርያቱን እንዲቀበል ልቡን ያሰፋለታል፤ከወሕይ ምንጭ እንዲጎነጭም ያደርገዋል። የስሞቹና የባሕርያቱ ግንዛቤ ልቡ ውስጥ ሲሰማው ወዶና ፈልጎ ይቀበለዋል፤ተገዥና ተመሪ ይሆንና ልቡ ይበራል። ልቦናው ይጠራል።

የአንድ ዕውቀት ከበሬታ የሚመነጨው ዕውቀቱ ከሚያስጨብጠው መረጃ ክቡርነት ሲሆን፣የአላህን ስሞችና ባሕርያቱን ከማወቅ የበለጠ ክቡር የሆነ ዕውቀት የለም

በፍቅርና በደስታ ይሞላል። በፍስሐ ይፈነድቃል፤መንፈሳዊ ሀብቱ ይጎለብታል። ዕውቀቱ በርሱ ይበለጽጋል፤ይጠናከራል። ልቦናው ይረጋጋል። የዕውቀት መናኸሪያ ይሆናል። የአንድ ዕውቀት ክቡርነት ከሚሰጠው መረጃ ክቡርነት የሚመነጭ ነውና ዓይነ ሕሊናው በዐጸዱና በጨፌው አትክልት እይታ ይረካል። እንዲህ ያሉ ባሕርያት ያሉትን ጌታ ከማወቅ የበለጠ ክቡርና ታላቅ ዕውቀት የሌለ ሲሆን፣ክቡርነቱ የመልካም ስሞችና የላቁ ባሕርያት ባለቤት የሆነው አላህﷻ አስፈላጊያችን የሆነውን ያህል የበዛ ነው። ለአንዲት ነፍስ ከምንም አስገኝቶ የፈጠራትን ፈጣሪ ከማወቅ፣እርሱን ከማፍቀር፣እርሱን ከማወደስ፣በርሱ ከመጽናናት፣ወደርሱ መቃረቢያን ከመፈለግና ወደርሱ ከመጠጋት የሚበልጥባት ምንም ነገር የለም። ወደዚህ ለመድረስ ደግሞ የአላህንﷻ ስሞችና ባሕርያቱን ከማወቅ ውጭ ሌላ መንገድ የለም። አንድ የአላህ አገልጋይ ይህን ዕውቀት ይበልጥ በገበየ ቁጥር አላህንﷻ ይበልጥ የሚያውቅ ይሆናል። እርሱን ይበልጥ የሚፈልግና ወደርሱ ይበልጥ የሚቀርብ ይሆናል። ዕውቀቱን ባጣ መጠንም ለአላህﷻ ያለው ዕውቀት ያነሰ፣ከርሱ ያለው ርቀትም የሰፋ ይሆናል። አላህﷻ አንድን ባሪያ የሚያስቀምጠው ባሪያው ለጌታው በሚሰጠው ደረጃና በውስጡ በሚሰጠው ግምት ልክ ነው።

የአላህን ስሞችና ባሕርያቱን ማወቅ የልብ ጥራትና የኢማን ምሉእነት ነው።

አራተኛ -

አላህንﷻ በእውነት ያወቀ ሰው፣አላህ በሚሠራውና በሚደነግገው ሕግ ላይ የቀሰመውን የአላህን ስሞችና የባሕርያቱን ዕውቀት አስረጅ አድርጎ ይጠቀማል። የአላህﷻ ሥራዎች ሁሉ በፍትሕ በትሩፋትና በጥበብ መካከል የሚሽከረከሩ በመሆናቸው፣አላህﷻ ከስሞቹና ከባሕርያቱ ጋር የሚጣጣመውን እንጂ አይሠራም። የሚደነግጋቸው ሕጎችም እንደዚሁ ከውዳሴው ከጥበቡ ከችሮታውና ከፍትሑ ጋር የተጣጣሙ ናቸው። የተናገራቸውና ከርሱ የተላለፈው ሁሉ እውነትና ሐቅ ናቸው። ትእዛዛቱና እገዳዎቹ ሁሉ ፍትሕ ጥበብና ርኅራሄ ናቸው። ይህ የዕውቀት ዘርፍ በጣም ጉልህ ከመሆኑ የተነሳ መንገርና መጠቆም የማያሻው ታላቅ ዕውቀት ነው።

አምስተኛ -

እያንዳንዱ ባሕርይ (ስፋህ) ከርሱ የሚመነጭና ከውጤቶቹ የሆነ የተለየ ዕባዳ (አምልኮ) ያለው በመሆኑ፣በአላህﷻ ባሕርያትና ከነርሱ በሚመነጩ ግልጽና ስውር ዕባዳዎች መካከል ጥብቅ ቁርኝትና መጣጣም መኖሩ። ይህ ሁሉንም የልቦና እና የአካል የዕባዳ ዓይነቶችን የሚያጠቃልል ሲሆን፣አላህﷻ የሚጠቅምና የሚጎዳ፣የሚሰጥና የሚነሳ፣ፈጣሪ፣ሲሳይ ሰጪ፣የሚያኖርና የሚገድል ብቸኛው ባለመብት ጌታ መሆኑን የሚገነዘብ የአላህ ባሪያ፣በውስጡ በአላህ ላይ የመመካትን (የተወኩልን) ጸጋ ሲጎናጸፍ በተባጩ ደግሞ ለዚህ ተወኩል አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችንና ውጤቶቹን ይታደላል። አላህﷻ ሰሚና ተመልካች መሆኑን ማወቁ፣አንድም ነገር ከርሱ የማይሰወር መሆኑን፣የዓይኖችን ክህደትና ልብ የደበቀውን ሁሉ የሚያውቅ ጌታ መሆኑን ማወቁ፣አገልጋዩ አንደበቱንና አካላቱን አላህﷻ ከማይወዳቸው ነገሮች ሁሉ እንዲጠብቅ ያደርገዋል። አንደበቱና አካላቱ አላህ በሚወደውና በሚፈልገው ነገር ላይ ብቻ ለመሰማራት እንዲተጉ በማድረግ በውስጡ ‹‹አላህ ምን ይለኛል›› የሚያሰኝ ስሜት ይፈጥርበታል። ይህ ይሉኝታና ፈጣሪን የማፈር ስሜትም አላህ ከከለከላቸው ነገሮችና ከእኩይ ተግባራት እንዲታቀብ ያደርገዋል። አላህﷻ ከፍጥረታት ሁሉ የተብቃቃ፣ቸር፣ለጋስ፣ርኅሩህ፣አዛኝና ደግ ጌታ መሆኑን ማወቁ ደግሞ የተስፋና በርሱ ላይ የመተማመን አድማሱን እንዲያሰፋ ያስችለዋል። ኃያልነቱን፣ግርማ ሞገሱንና አሸናፊነቱን ማወቁም እንደዚሁ ለርሱ መተናነስን፣መንበርከክንና ውዴታውን ያስገኝለታል። እነዚህ ሕሊናዊ ስውር ሁኔታዎች ውጤታቸው የሆኑ ተግባራዊ ተጨባጭ የዕባዳ ዓይነቶችን ያፈራሉ። . . እናም ዕባዳዎች ሁሉ በዚህ መልኩ የአላህﷻ ስሞችና የባሕርያቱ ውጤቶች መሆናቸው ይረጋገጣል።

ስድስተኛ -

በአላህﷻ ስሞችና በባሕርያቱ እርሱን ማምለክ በልቦና ሰላምና መረጋጋት ላይ፣በጠባይና ስነምግባር ደህንነት ላይም በጎ ተጽእኖ ያሳድራል። ስሞቹንና ባሕርያቱን ትርጉም የለሽና ውድቅ ማድረግ ለልቦና ደዌዎች በር መክፈት ነው።

ሰባተኛ -

የአላህﷻ ስሞችና የባሕርያቱ ዕውቀት፣አንድ የአላህ አገልጋይ ችግርና መከራ ሲያጋጥመው መጽናኛ ይሆንለታል። ፈጣሪ ጌታው በጣም ዐዋቂ፣ጥበበኛና ማንንም የማይበድል ፍትሐዊ መሆኑን ያወቀ ሰው፣አላህ የወሰነውንና የደረሰበትን ነገር ወዶ በትዕግስት ይቀበላል። የሚደርስበት ፈተና፣የሚያጋጥመው መከራና አበሳ፣እርሱ የማያውቃቸውና ዕውቀቱ የማይደርስባቸው ጥቅሞችና ፋይዳዎች ይዘው እንደሚመጡ ይገነዘባል። በአላህﷻ ዕውቀትና በጥበቡ የተወሰኑና የተቀነባበሩ በመሆናቸው በጌታው ይጽናናል፤በርሱም ይተማመናል፤ጉዳዩን ሁሉ ለርሱ አሳልፎ ይሰጣል።

ስምንተኛ -

የአላህንﷻ ስሞችና ባሕርያቱን ማወቅ ወደ አላህ ውዴታ፣እርሱን ወደ ማላቅና ማክበር፣በርሱ ላይ ተስፋን ወደ መጣል፣እርሱን ብቻ ወደ መፍራት፣በርሱ ላይ ብቻ ወደ መተማመንና ሁሌም ተመልካችና ተቆጣጣሪ መሆኑን ወደ ማስታወስ የሚወስድ መንገድ ነው። እነዚህ ሁሉ የአላህንﷻ ስሞችና ባሕርያቱን የማወቅ ፍሬዎች ናቸው።

ዘጠነኛ -

የአላህንﷻ ስሞችና ባሕርያቱን ማስተንተንና አስተውሎ መመርመር ቁርኣንን ለመገንዘብና ለማስተንተንን የሚያግዝ ብርቱ መሳሪያ ነው። አላህﷻ ቁርኣንን እንድናስተነትን ሲያዘን እንዲህ ብሏል፦

(كِتَٰبٌ أَنزَلۡنَٰهُ إِلَيۡكَ مُبَٰرَكٞ لِّيَدَّبَّرُوٓاْ ءَايَٰتِهِۦ وَلِيَتَذَكَّرَ أُوْلُواْ ٱلۡأَلۡبَٰبِ٢٩)

‹‹(ይህ) ወዳንተ ያወረድነው፣ብሩክ መጽሐፍ ነው፤አንቀጾቹን እንዲያስተነትኑትና የአእምሮዎች ባለቤቶችም እንዲገሠጹ (አወረድነው)።››

[ሷድ፡29]

ቅዱስ ቁርኣን የአላህﷻ ስሞችና ባሕርያቱ በተደጋጋሚና በብዛት የሚወሱበት ከመሆኑ አንጻር፣ ስሞቹንና ባሕርያቱን ማስተዋልና አስተንትኖ መረዳት ማለት ቁርኣንን አስተንትኖ መረዳት ማለት ነው። ቁርኣንን አስተውሎ የተገነዘበ ሰው ከሰማያቱ በላይ ዐርሹ ላይ ያለውን ኃያሉን አላህﷻ ፣የባሮቹን ጉዳዮች ሲያቀነባብር፣ትአዛዝና እገዳ ሲያስተላልፍ፣ነቢያትንና መልእክተኞችን ሲልክ፣መለኮታዊ መጽሐፍትን ሲያወርድ፣ወዶ ሲቀበልና ሲቆጣ፣ሲሸልምና ሲቀጣ፣ሲሰጥና ሲነሳ፣ከፍ ሲያደርግና ሲያዋርድ፣ሲያነሳና ሲጥል፣ከሰባቱ ሰማያት በላይ ሆኖ ሲሰማና ሲመለከት፣ግልጽና ስውሩን የሚያውቅ፣ያሻውን ሲሰራና የመሰለውን ሲፈርድ፣ከጉድለት ሁሉ የጠራ ሆኖ፣ያለ እርሱ ፈቃድ አንዲት ቅንጣት አቶምም ሆነች ከዚያ ያነሰ አንዳች ነገር የማይንቀሳቀስ፣ከርሱ ዕውቀት ውጭ ቅጠል እንኳ ከዛፉ የማይወድቅ የፍጹማዊ ዕውቀት ባለቤት የሆነ ጥበበኛ አምላክ መኖሩን በአእምሮው ያስተውላል።

አላህንﷻ ያገኘው ሰው ምን አጥቶ?! አላህንﷻ ያጣ ሰውስ ምን አገኝቶ?!

ዐሥረኛ -

የአላህﷻ ስሞችና የባሕርያቱ ዕውቀት፣ከአላህ ጋር በሚኖረን ግንኙነት ውስጥ አደብና ስነምግባርን፣እንደዚሁም የርሱን ይሉኝታ ልብ ውስጥ ይዘራል። ይህም ለሃይማኖቱ ተገዥ መሆንና በስውርም ሆነ በግልጽ ለሃይማኖታዊ ስነምግባሮቹ ተመሪ መሆን ማለት ሲሆን፣ ከአላህ ጋር በሚኖረን ግንኙነት ውስጥ በአደብ መመራት የሚቻለው በሦስት ነገሮች አማካይነት ብቻ ነው። እነሱም፦ በስሞቹና በባሕርያቱ አላህንﷻ ማወቅ፣እርሱ የሚወደውንና የሚጠላውን በመለየት በሃይማኖቱና በሸሪዓው እርሱን ማወቅ፣እውነትን ከዕውቀት ከተግባርና ከአኳኋን አንጻር አውቆ ለመቀበል ዝግጁ የሆነች ገርና ስንዱ ነፍሲያ ናቸው።

ዐሥራ አንደኛ -

የአላህﷻ ስሞችና የባሕርያቱ ዕውቀት፣ባሪያው የራሱን እንከኖችና ጉድለቶች መለስ ብሎ እንዲያስተውል ስለሚያደርገው ራሱን ለማረምና ለማሻሻል እንዲተጋ ያነሳሳዋል።

የከሕደት ማእዘናት አራት ሲሆኑ፣እነሱም ኩራት፣ምቀኝነት፣ቁጣና ሥጋዊ ዝንባሌ ናቸው። የነዚህ የአራቱ ምንጭ ደግሞ ባሪያው ጌታውን የማያውቅ መሆንና የገዛ ራሱንም የማያውቅ መሆን ነው። ጌታውን በምሉእ ባህርያቱና በግርማ ሞገስ መገለጫዎቹ ቢያውቀው፣የገዛ ነፍሲያውን እንከኖችና ጉድለቶቿን የሚረዳ ቢሆን ኖሮ አይኩራራም፤ለነፍሲያው ብሎ አይቆጣም፤አላህ በለገሰው ጸጋ ምክንያት በማንም ሰው ላይ የቅናት ስሜት አያድርበትም።

ዐሥራ ሁለተኛ -

የአላህﷻ ስሞችና ባሕርያቱን አለማወቅና በቂ ግንዛቤ አለመጨበጥ፣በስሞቹና በባሕርያቱ እርሱን አለመገዛት ለጥመትና ለማይምነት የሚያጋልጥ አደጋ ነው። አላህንና መልእክተኞቹን ያላወቀ ሰው ምንም ነገር አላወቀም። ይህ እውነታ ያመለጠው ሰው ምንም እውነታ አልጨበጠም። አላህንﷻ ማወቅ፣እርሱ የሚወደውን መሥራትና ወደዚያ የሚያደርሰውን መንገድ ማወቅ ያመለጠው ሰው ምንም ዕውቀት አልገበየም፤አንዳች ሥራም አላስመዘገበም። የሰው ልጅ ሕያውነቱ በልቦናውና በመንፈሱ ሕያውነት የሚለካ ነው። የመንፈስና የልቦና ሕያውነት ፈጣሪ አምላኩን ከማወቅ፣እርሱን ከመውደድ፣እርሱን ብቻ ከመገዛት፣ወደርሱ ብቻ ከመማለስ፣በርሱ ውዳሴ ከመረጋጋትና ከመጽናናት፣ወደርሱ በመቅረብ ከመርካት ውጭ የሚታሰብ አይደለም። ይህን እውነተኛ ሕይወትና ሕያውነት የተነፈገ ሰው፣በዚህ ዓለም ላይ ያለው ሁሉ በዚህ ምትክ ቢሰጠው እንኳ መልካም ነገሮችን ሁሉ የተነፈገ ሰው ነው።

ዐሥራ ሦስተኛ -

የአላህﷻ ስሞችና የባሕርያቱ ዕውቀት፣ለጠራ ተውሒድና ለኢማን ምሉእነት የሚያበቃ ሲሆን፣ለአላህ ፍጹም መሆን፣እርሱን መውደድ፣እርሱን መፍራት፣በርሱ ላይ ተስፋን መጣልንና በርሱ ላይ ብቻ መተማመንን ለመሳሰሉ የልቦና ሥራዎችም መገለጫ ይሆናል። ልቦናን ለማጥራት፣ከጎትጓችና አደናቃፊ ነገሮች ነጻ ለማድረግ ካለው ከፍተኛ ጥቅም አኳያ፣ርእሰ ጉዳዩን አስተውሎ መመልከትና ተገቢ የሆነ ትኩረት መስጠት ቀላል ነው። የሸሪዓውን ምንጮችና መሰረቶች ያስተነተነ ሰው፣የልቦና ሁኔታዎችና ተግባራት ከአካላዊ ሥራዎችና ክንዋኔዎች ጋር የተሳሰሩ መሆናቸውን፣ያለ እነሱ የማይጠቅሙ፣የልቦና ሁኔታዎችና ተግባራት በአንድ የአላህ አገልጋይ ላይ ከአካላዊ ተግባራት ይበልጥ ግዴታ የተደረጉ መሆናቸውን ይገነዘባል። ሙእምን ሰው ከአስመሳይ መናፍቅ የሚለየውስ በያንዳንዳቸው ልብ ውስጥ ባሉትና ሁለቱን በሚለዩት የልቦና ሁኔታዎችና ተግባራት እንጂ መች በሌላ ሆነና? አንድ ሰው እስላምን መቀበልና መስለም የሚችለውስ ከአካላዊ ግዴታዎችና ሥራዎች በፊት በውስጣዊው የልቦና ተግባር አይደለምን? እናም የልብ ዕባዳና ተገዥነት ከአካላዊ ዕባዳና ተገዥነት የላቀና ይበልጥ የሚቆይ ሲሆን፣ወደ አካላዊ ዕባዳ የሚወስድ መንገድ ነው። በመሆኑም በማንኛውም ጊዜ ግዴታነቱ የጸና ነው።

አላህንﷻ ማወቅ ለልቦና እና ለአካላት በጎ መሆን አስፈላጊ ነው።Tags: