ለ - የአላህ ስሞች አሻራዎች በዩኒቨርስ ውስጥ ፦

ለ - የአላህ ስሞች አሻራዎች በዩኒቨርስ ውስጥ ፦
የአላህንﷻ መልካም ስሞችና የላቁ ባሕርያቱን ማወቅ ከዕውቀት ሁሉ የተከበረ የላቀ ዕውቀት ነው። እያንዳንዱ የአላህﷻ ስም የራሱ የሆነ መለያ ባሕርይ አለው። ስሞቹ የውዳሴና የምሉእነት መገለጫዎች ሲሆኑ፣እያንዳንዱ ባሕርይ ግዴታና ተግባር አለው። እያንዳንዱ ተግባርም የመገኛው መሰረት የሆነ መተግበሪያና ውጤት አለው። እርሱነቱ (ዛቱን) ከስሞቹ ለይቶ ትርጉም የለሽ ማድረግ፣ስሞቹንም ከመገለጫዎቻቸውና ከይዘታቸው ነጥሎ ትርጉም አልባ ማድረግ፣ባሕርያቱን ከሚያስከትሏቸው ተግባራትና ውጤቶች መነጠል፣ተግባሮቹን ከውጤቶቹና ከአሻራዎቹ ነጥሎ ትርጉም የለሽ ማድረግ ፈጽሞ የማይቻል ነው። እነዚህ ሁሉ የስሞቹና የባሕርያቱ ነጸብራቅ አሻራዎች ናቸው።

ሥራዎቹ ጥበባዊና ጠቃሚዎች ናቸው። ስሞቹ መልካሞች ናቸው። ከተግባርና ውጤት ነጥሎ ትርጉም አልባ አድርጎ መገመት እርሱንﷻ በተመለከተ ፈጽሞ ሊሆን የማይችል ጉዳይ ነው። ለዚህ ነው አላህﷻ ትእዛዝና እገዳውን፣ምንዳና ቅጣቱን ውድቅና ትርጉም የለሽ የሚያደርገውን ሰው የተቃወመው። ይህን ማድረግ ለርሱ ተገቢ ያልሆነውን ነገር ከርሱ ጋር ማያያዝ፣በርሱ ላይ ክፉ ግምት (ዟን) መያዝ፣ለኃያልነቱና ለጥበቡ ተገቢ በሆነ ክብር እርሱን አለማክበር ነው። አላህﷻ ነቢይነትን፣የመልክተኞችን መላክና የመለኮታዊ መጻሕፍትን መውረድ የሚያስተባብሉትን አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦

(وَمَا قَدَرُواْ ٱللَّهَ حَقَّ قَدۡرِهِۦٓ إِذۡ قَالُواْ مَآ أَنزَلَ ٱللَّهُ عَلَىٰ بَشَرٖ مِّن شَيۡءٖ)

‹‹አላህ በሰው ላይ ምንም አላወረደም ባሉ ጊዜ፣አላህን ተገቢ ክብሩን አላከበሩትም።››

[አልአንዓም፡91]

ዳግም ከሞት መነሳትንና የሥራዎች ዋጋ መከፈሉን የሚያስተባብሉትን ከሓዲዎች አስመልክቶ አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(وَمَا قَدَرُواْ ٱللَّهَ حَقَّ قَدۡرِهِۦ وَٱلۡأَرۡضُ جَمِيعٗا قَبۡضَتُهُۥ يَوۡمَ ٱلۡقِيَٰمَةِ وَٱلسَّمَٰوَٰتُ مَطۡوِيَّٰتُۢ بِيَمِينِهِ)

‹‹አላህንም በትንሣኤ ቀን ምድር በመላ (አንድ) ጭብጡ ስትኾን፤ሰማያትም በቀኙ (በኃይሉ) የሚጠቀለሉ ሲኾኑ፣(ከርሱ ጋር ሌላን በማጋራታቸው) ተገቢ ክብሩን አላከበሩትም።››

[አልዙመር፡67]

የተለያዩ ምድቦችን ትጉሃን ደጋግ ባሮቹን ከአመጸኞቹ ኃጢአን ጋር፣ምእመናንን ከከሓዲዎች ጋር እኩል ማድረግን የሚቻል ያደረጉትን ወገኖች አስመልክቶ አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

أَمۡ حَسِبَ ٱلَّذِينَ ٱجۡتَرَحُواْ ٱلسَّئَِّاتِ أَن نَّجۡعَلَهُمۡ كَٱلَّذِينَ ءَامَنُواْ وَعَمِلُواْ ٱلصَّٰلِحَٰتِ سَوَآءٗ مَّحۡيَاهُمۡ وَمَمَاتُهُمۡۚ سَآءَ مَا يَحۡكُمُونَ ٢١)

‹‹እነዚያ ኀጢአቶችን የሠሩ፣ሕይወታቸውም ሞታቸውም ትክክል ሲኾን፣እንደነዚያ እንደ አመኑትና መልካሞችን እንደሠሩት ልናደርጋቸው ይጠረጥራሉን? (አይጠርጥሩ)፤የሚፈርዱት ምንኛ ከፋ!››

[አልጃሢያ፡21]

ይህ ለርሱ ተገቢው ያልሆነ፣ስሞቹና ባሕርያቱ የሚጻረሩት የተዛባ ፍትሕ መሆኑን ሲነግራቸው አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(أَفَحَسِبۡتُمۡ أَنَّمَا خَلَقۡنَٰكُمۡ عَبَثٗا وَأَنَّكُمۡ إِلَيۡنَا لَا تُرۡجَعُونَ ١١٥ فَتَعَٰلَى ٱللَّهُ ٱلۡمَلِكُ ٱلۡحَقُّۖ لَآ إِلَٰهَ إِلَّا هُوَ رَبُّ ٱلۡعَرۡشِ ٱلۡكَرِيمِ ١١٦)

‹‹የፈጠርናችሁ ለከንቱ መኾኑን እናንተም ወደኛ የማትመለሱ መኾናችሁን ጠረጠራችሁን? (ለከንቱ የፈጠርናችሁ መሰላችሁን?)። የእውነቱም ንጉሥ አላህ፣ከፍተኛነት ተገባው፤ከርሱ ሌላ አምላክ የለም፤የሚያምረው ዐርሽ ጌታ ነው።››

[አልሙእሚኑን፡115-116]

ስሞቹንና ባሕርያቱን ከሚጸረረው ከእንዲህ ዓይነቱ ግምትና ብያኔ አላህﷻ የጠራ ጌታ ነው።

አላህﷻ ስሞቹና ባሕርያቱ ከሚጠይቁትና ከሚያስከትሉት ውጤት በተቃራኒ መሆንን ከራሱ የሚያስተባብልባቸው የዚህ ተመሳሳይ የሆኑ ገለጻዎች ቁርኣን ውስጥ ብዙ ናቸው። ይህን ማድረግ የስሞቹንና የባሕርያቱን ምሉእነትና ግዴታዊ ውጤቶች ውድቅና ትርጉም አልባ ማድረግ ነውና።

‹‹ተመስጋኙ አሸናፊው›› የሚለው ስሙ፣የሰውን ልጅ ከንቱ ግብ የለሽና እንዲሁ የተተወ፣ይህን አድርግ ይህን አታድርግ ተብሎ የማይታዘዝ፣በሥራው የማይሸለምና የማይቀጣ አድርጎ መተውን ይጻረራል። ‹‹ጥበበኛው›› የሚለውና ‹‹ንጉሡ›› የሚለው ስሙም ይህንኑ ይቃወማል።

‹‹ሕያው›› የሚለው ስሙ ሥራ የሌሽነትን ከርሱ የሚያስተባብል ሲሆን፣የሕይወት ምንነትና እውነታ ሥራ ነው። ማንኛውም ሕያው ሠሪ ሲሆን፣የአላህﷻ ከማንምና ከምንም የተብቃቃ ፈጣሪ መሆን ከሕያውነቱ የሚመነጭ የግዴታ ተግባርና ውጤት ነው። ‹‹ሰሚው ተመልካቹ›› የሚለው ስሙ የሚሰማና የሚያይ መኖርን ግድ ይላል። ‹‹ፈጣሪው›› የሚለው ስሙ የፍጡርን መኖር ያስከትላል። ‹‹ሲሳይን ሰጪው›› የሚለው ስሙም እንደዚሁ። ‹‹ንጉሡ›› የሚለው ስሙም ግዛትና ሥልጣንን፣ፈጻሚነትንና አቀነባባሪነትን፣መስጠትና መከልከልን፣ፍትሕና ደግነትን፣ምንዳና ቅጣትን ያስከትላል። ‹‹በጎ ሠሪው፣በጎ አድራጊው፣ሰጪው፣ያለ ገደብ ሰጪው›› የሚሉ ስሞቹና የመሳሰሉትም እንዲሁ መገለጫዎችና አሻራዎች ያሏቸው ናቸው።

‹‹ምሕረተ ብዙ፣ጸጸትን ተቀባይ፣ይቅር ባዩ›› የሚሉ ስሞቹና የመሳሰሉትም እንዲሁ የራሳቸው ተያያዥዎች አሏቸው። በመሆኑም ምሕረት የሚሰጠው ኃጢአት፣ተቀባይነት የሚኖረው ተውበት፣ይቅር የሚባሉ ጥፋቶች የግድ ይኖራሉ ማለት ነው። ‹‹ጥበበኛው›› የሚለው ስሙም ጥበቦቹ የሚገለጽበት ተያያዥ ውጤት መኖርን የሚጠይቅ ሲሆን፣የነዚህ ስሞች ተያያዥነት ‹‹ፈጣሪው፣ሲሳይን ሰጪው፣ሰጪው፣ከልካዩ››የሚሉ ስሞች ከፍጡር፣ሲሳይ የተሰጠው፣ተሰጪና ተከልካይ ጋር ያላቸው ትስስር ዓይነት ነው፤ሁሉም መልካም ስሞች ናቸው።

ኃያሉ ጌታ እርሱነቱን፣ባሕርያቱንና ስሞቹን ይወዳል። እርሱ ይቅር ባይ ነውና ይቅርባይነትን ይወዳል። ምሕረትንና ተጸጽቶ መመለስን (ተውበትን) ይወዳል። ባሪያው በኃጢአቱ ተጸጽቶ ወደርሱ ሲማለስ በእጅጉ ይደሰታል፣ይቅር ብሎም ይምረዋል።

እርሱﷻ ‹‹ተመስጋኙ አሸናፊው›› ነውና ምስጋናውና አሸናፊነቱ መገለጫ አሻራ አላቸው። ከአሻራዎቻቸው መካከል ተገቢውን ቅጣት ከመስጠት ፍጹማዊ ችሎታው ጋር ፣የጥፋቱን መጠንና ተመጣጣኝ ቅጣቱን ከማወቁ ጋር፣ስሕተትን ይቅር ማለት፣ጥፋትን ማለፍ፣ኃጢአቶችን ማበስ፣ጥሰቶችን መማር ይገኙባቸዋል። እያወቀ ይታገሳል፤እየቻለ በይቅርታ ያልፋል፤በኃያልነቱ በአሸናፊነቱና በጥበቡ ምሕረት ይሰጣል። አላህﷻ በአልመሲሕ ዒሳ  አንደበት እንዲህ ብሏል፦

(إِن تُعَذِّبۡهُمۡ فَإِنَّهُمۡ عِبَادُكَۖ وَإِن تَغۡفِرۡ لَهُمۡ فَإِنَّكَ أَنتَ ٱلۡعَزِيزُ ٱلۡحَكِيمُ ١١٨ )

‹‹ብትቀጣቸው እነሱ ባሮችህ ናቸው፤ለነርሱ ብትምርም አንተ አሸናፊው ጥበበኛው ነህ (ይላል)።››

[አልማኢዳህ፡118]

የአንቀጹ ይዘት ምሕረት የምታደርገውና ይቅር የምትለው ችሎታህና ጥበብህ ምሉእ በመሆኑ ነው። ደካማ በመሆኑ ይቅር አንደሚለው፣ተገቢውን መብት ባለማወቁ ምሕረት እንደሚያደርግ ሰው አይደለህም። አንተ መብትህን የምታውቅ፣ተገቢውን ዋጋ ለመስጠት ፍጹማዊ ችሎታ ያለህ ጥበበኛ ነህ፣የሚል ነው።

በዓለምና በፍጥረታት ውስጥ የሚንጸባረቁትን የስሞቹንና የባሕርያቱን አሻራዎች በትኩረት ያስተዋለ ሰው፣የነዚህ ኃጢአቶች ምንጭ ባሮቹ መሆናቸውን ይረዳል። አስቀድመው በአላህﷻ መሻትና በዕውቀቱ የተወሰኑ መሆናቸው የስሞቹ፣የባሕርያቱና የሥራዎቹ ምሉእነት አካል ነው። ግባቸውም እንዲሁ የውዳሴውና የኃያልነቱ፣የጌትነቱና የአምላክነቱ ውጤቶች ናቸው።

በአቀደውና በወሰነው ነገር ሁሉ ውስጥ ጥልቅ ጥበባትና ጉልህ ምልክቶች ይገኛሉ። በስሞቹና በባሕርያቱ ራሱን ለባሮቹ ማስተዋወቁ፣እንዲወዱት፣እንዲያወድሱት፣እንዲያመሰግኑት፣በመልካሞቹ ስሞቹ እንዲያመልኩት ነው። እያንዳንዱ ስም ከማወቁና ይዘቱን ከመገንዘቡ አንጻር የራሱ የተለየ አምልኮት ያለው ሲሆን፣በዕባዳው ይበልጥ የተሟላ የሆነው ሰው የሰው ልጆች ሊያውቁ በሚችሏቸው ሁሉም የአላህﷻ ስሞችና ባሕርያቱ እርሱን ያመለከ ሰው ነው። ይህም በአንድ ስሙ እርሱን ማምለክ በሌላው ስሙ እርሱን ከማምለክ አይጋርደውም ማለት ነው። ‹‹ምንም የማይሳነው ሁሉን ቻይ›› በሚለው ስሙ እርሱን ማምለክ ‹‹በጣም ታጋሹ›› ወይም ‹‹በጣም አዛኙ›› በሚለው ስሙ እርሱን ማምለክ እንደሚጋርደው፣‹‹ሰጭው›› ለሚለው ስሙ መገዛት ‹‹ከልካዩ›› ለሚለው ስሙ መገዛትን፣‹‹በጣም አዛኙ››፣ወይም ‹‹ይቅር ባዩ›› ወይም ‹‹በጣም መሓሪው›› በሚለው ስሙ እርሱን ማምለክ ‹‹ተበቃዩ›› ለሚለው ስሙ መገዛትን እንደሚጋርደው ሰው ዓይነት ማለት ነው።

አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(وَلِلَّهِ ٱلۡأَسۡمَآءُ ٱلۡحُسۡنَىٰ فَٱدۡعُوهُ بِهَا)

‹‹ለአላህም መልካም ስሞች አሉት፤(ስትጸልዩ) በርሷም ጥሩት፤››

[አልአዕራፍ፡180]

በስሞቹ እርሱን መጥራት የልመና ጥሪን (ዱዓእ)፣የውዳሴ ጥሪንና የዕባዳ ጥሪን የሚያካትት ነው። አላህﷻ ባሮቹ በስሞቹና በባሕርያቱ እንዲጠሩት፣እንዲያወድሱትና በተቻላቸው መጠን ተገዥነታቸውን እንዲያሳዩ ጥሪ አድርጎላቸዋል።

አላህﷻ የስሞቹንና የባሕርያቱን መገለጫ ውጤት ይወዳል። እርሱ በጣም ዐዋቂ ነውና ዋቂን ሁሉ ይወዳል። በጣም ቸር ለጋስ ነውና ለጋሾችን ሁሉ ይወዳል። አቻ የሌለው አንድ ብቸኛ (ውትር) ነውና የውትር ሶላትን ይወዳል። ውበትን ሰጭ ነውና ውበትን ይወዳል። መሓሪ ነውና ምሕረትን ይወዳል። ደግ ነውና ደጋጎችን ይወዳል። አመስጋኝ ነውና አመስጋኞችን ይወዳል። ታጋሽ ነውና ታጋሾችን ይወዳል። ቻይ ነውና ሆደ ሰፊዎችን ይወዳል። አላህﷻ ተውበትን፣ምሕረትንና ይቅር ባይነት ስለሚወድ ነው ይቅር የሚለውን፣ምሕረት የሚያደርግለትንና ተውበቱን የሚቀበለውን ፍጡር የፈጠረው።

ከፍጥረታቱ ጋር በምንም አይመሳሰልም፤ፍጥረታቱም ከርሱ ጋር በምንም አይመሳሰሉም። በስሞቹና በባሕርያቱ እንዳለና እንደነበረ ነው።

ኢማም አቡ ሐኒፋ



Tags: