በአላህ ጌትነት የማመን ተውሒድ (ተውሒድ አርሩቡብይያ) በአማኙ ላይ የሚያሳርፈው አሻራ፦

በአላህ ጌትነት የማመን ተውሒድ (ተውሒድ አርሩቡብይያ) በአማኙ ላይ የሚያሳርፈው አሻራ፦
1- ከግራ መጋባትና ከጥርጣሬ መዳን፦ የሁሉም ነገሮች ጌታ የሆነ፣የፈጠረውና ያስተካከለው ያከበረውና ከሌሎች ፍጥረታት ብልጫ የሰጠው፣በምድር ላይ ተጠሪው ያደረገው፣በሰማያትና በምድር ያለውን ሁሉ ከርሱ ሲሆን ለግልጋሎቱ የገራለት፣ግልጽና ስውር ጸጋዎቹን የዘረጋለት፣ፈጣሪ ጌታ እንዳለው የሚያውቅ ሰው፤በርሱ ተጽናንቶ ወደርሱ የተጠጋ፣ሕይወት አጠር ያለች፣ ጥሩና መጥፎ፣ፍትሕና ግፍ፣ደስታና ሲቃይ የተቀያየጠባት መሆኑን የሚያውቅ ሰው በግራ መጋባትና በጥርጣሬ እንዴት ይጠቃል?!

የአላህን ጌትነት የሚያሰተባብሉ፣ከርሱ ጋር መገናኘት መኖሩን የሚጠራጠሩ ደግሞ ሕይወታቸው ጣዕምም ሆነ ትርጉም የለውም። ሕይወታቸው በጭንቀት፣በጥርጣሬ፣በግራ መጋባትና መልስ በሌላቸው ተከታታይ ጥያቄዎች የተሞላ ሲሆን፣የሚጠጉበት ማእዘን የሌላቸው ያሻቸውን ያህል ብልጠትና የሰላ አእምሮ ቢኖራቸውም አእምሯቸው በጥርጣሬና በጭንቀት የሚዋልል ነው። በዚህ መልኩም የዱንያ ዓለም ቅጣትና ስቃይ ጧትና ማታ ልቦቻቸውን እየለበለበ ይኖራሉ።

2-

የመንፈስ እርካታ፦ የመንፈስ እርካታና የሕሊና ሰላም ምንጫቸው አንድና አንድ ብቻ ሲሆን፣እሱም በአላህና በመጨረሻው ቀን ማመን ብቻ ነው . . ጥልቀት ያለው፣ጥርጣሬ የማያጎድፈውና አስመሳይነት የማይበክለው እውነተኛ ኢማን ብቻ ነው። ይህ ተጨባጩ ሁኔታ የሚመሰክረው፣ታሪክ የሚደግፈው፣ለራሱና በዙሪያው ላሉት ታማኝና ፍትሐዊ የሆነ አስተዋይ የሆነ ማንኛውም ሰው በተግባር የሚመለከተው ጥሬ እውነት ነው። ከሰዎች ሁሉ ይበልጥ በጭንቀት በውጥረትና በብኩንነት ስሜት የሚጠቁት፣የኢማንን ጸጋና የእርግጠኝነትን እርካታ የተነፈጉ መሆናቸውን ተምረናል። ሕይወት ትርጉም እንዳለው ስለማይገነዘቡ፣ዓላማ አለው ብለውም ስለማያስቡ፣ምስጢሩን ስለማይረዱ፣ሕይወታቸው በመደሰቻዎችና በአዝናኝ ነገሮች የተጥለቀለቀ ቢሆንም ጣዕም አልባ ነው። ከዚህ ጋር የመንፈስ እርካታና የሕሊና ደስታን እንዴት መጎናጸፍ ይችላሉ?! እርካታና እውነተኛ ደስታ የኢማን ፍሬ ሲሆን፣ተውሒድ ደግሞ በጌታዋ ፈቃድ ሁሌም የምታፈራ መልካም ዛፍ ናት። ሰዎች መረጋጋትን አጥተው ሲናወጡ ይጸኑ ዘንድ፣ሰዎች ሲከፉ ይደሰቱ ዘንድ፣ሰዎች በጥርጣሬ ሲመቱ እርግጠኞች ይሆኑ ዘንድ፣ሰዎች ሲብሰለሰሉ ይታገሡ ዘንድ፣ሰዎች ሲንቀዠቀዡ ይረጋጉ ዘንድ፣አላህﷻ በምእመናን ልብ ላይ የሚያወርደው መለኮታዊ በረከት ነው። ይህ እርጋታ ነው ጭንቀትም ሆነ ሐዘን ዝር ሳይልበት፣ፍርሃትም ሆነ ስጋት ሳይደርስበት፣ጥርጣሬም ሆነ ግራ መጋባት ሳይኖርበት፣በህጅራ ቀን የአላህ መልክተኛን ልብ ሞልቶ ያጥለቀለቀው። አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(إِلَّا تَنصُرُوهُ فَقَدۡ نَصَرَهُ ٱللَّهُ إِذۡ أَخۡرَجَهُ ٱلَّذِينَ كَفَرُواْ ثَانِيَ ٱثۡنَيۡنِ إِذۡ هُمَا فِي ٱلۡغَارِ إِذۡ يَقُولُ لِصَٰحِبِهِۦ لَا تَحۡزَنۡ إِنَّ ٱللَّهَ مَعَنَا)

‹‹(ነቢዩን) ባትረዱት፣እነዚያ የካዱት ሕዝቦች የሁለት (ሰዎች) ሁለተኛ ኾኖ (ከመካ) ባወጡት ጊዜ፣አላህ በእርግጥ ረድቶታል፤ሁለቱም በዋሻው ሳሉ፣ለጓደኛው አትዘን፣አላህ ከእኛ ጋር ነውና ባለ ጊዜ፣››

[አልተውባህ፡40]

የባልደረባቸው የአቡ በክር (ረ.ዐ) ልብ፣ለራሳቸውና ለገዛ ሕይወታቸው ሳይሆን ለአላህ መልክተኛ ﷺ እና ለመልእክተ ተውሒድ ዕጣ ፈንታ በሐዘንና በመሳሳት ስሜት ተሞልቶ ነበር። ጠላቶች ዋሻው አፍ ላይ ደርሰው እንደቆሙ ሲመለከቱ እንዲህ እስከ ማለት ደርሰውም ነበር፦

‹‹የአላህ መልክተኛ ሆይ! አንዳቸው ወደ እግሮቹ ቢመለከት ከእግሩ ሥር ያየናል፤›› ሲሉ ነቢዩ ﷺ ልባቸውን በማረጋጋት ‹‹ አቡ በክር ሆይ! አላህ ሦስተኛቸው የሆነ ሁለት ሰዎችን እንዴታ?!›› አሏቸው።

(በሙስሊም የተዘገበ)

ይህ እርጋታ ፈሪ የሚረጋጋበት፣የተጨነቀ የሚጽናናበት፣ያዘነ የሚታገስበት፣የታከተው የሚያርፍበት፣ደካማው ብርታት የሚያገኝበት፣ግራ የተጋባው የሚመራበት፣ከአላህ የሆነ መንፈስና ብርሃን ነው። ይህ እርጋታ አላህﷻ ለምእመናን ባሮቹ በሠሩት በጎ ተግባር፣ካዘጋጀላቸው ድሎት ውስጥ በዚህ በረከት በሰላሙና በጸጥታው ይረኩ ዘንድ፣ጥቂቱን ሊያቀምሳቸው፣አነስተኛውን ሞዴል ሊያሳያቸው፣በነርሱ ላይ መዓዛና ሽውታው ከርሷ የሚለቀቅበት፣ብርሃኑ በነርሱ ላይ ከርሷ የሚያፈነጥቅበት፣ሽቶው ከዚያ የሚያውድበት መስኮት ነው።

ኢማን ነፍስ አድን ጀልባ ነው

ራሱን በአላህﷻ ያብቃቃን ሰው፣ሰዎች አስፈላጊያቸው አድርገው ይወስዱታል።

ከአላህﷻ ጋር ያለህ ግንኙነት በተዳከመ ቁጥር፣ለጉትጎታና ለውስወሳ የተጋለጥክ ትሆናለህ።

3-

በአላህﷻ ላይ መተማመን፦ መጥቀምም ሆነ መጉዳት ሁሉም ነገር በርሱ እጅ ነው። ሲሳይ ሰጭና አቀነባባሪ ጌታ እርሱ ብቻ ነው። የሰማያትና የምድር መክፈቻዎች ሁሉ የርሱ ብቻ ናቸው። በመሆኑም አንድ ሙእምን ጥሩም ሆነ መጥፎ፣ጠቃሚም ሆነ ጎጂ ነገር አላህ ከጻፈለት ተቃራኒው እንዲሆን ፍጥረታት ሁሉ አንድ ላይ ቢሰባሰቡ እንኳ እርሱ ከወሰነለት ውጭ የማያገኘው መሆኑን ካወቀ፤ጠቃሚና ጎጂ፣ሰጭና ነሺ አንድ አላህ ብቻ መሆኑን ይረዳል። ይህም በአላህﷻ ላይ ያለውን መተማመን እንዲጨምር፣ተውሒዱንም እንዲያልቅ ያደርገዋል። ለዚህ ነው አላህﷻ የማይጠቅመውን፣የማይጎዳውንና ከምንም የማያብቃቃውን ነገር የሚያመልከውን ሰው የወቀሰው። አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(لَّهُۥ مَقَالِيدُ ٱلسَّمَٰوَٰتِ وَٱلۡأَرۡضِۗ وَٱلَّذِينَ كَفَرُواْ بِئايَٰتِ ٱللَّهِ أُوْلَٰٓئِكَ هُمُ ٱلۡخَٰسِرُونَ ٦٣)

‹‹የሰማያትና የምድር (ድልብ)፣መክፈቻዎች የርሱ ብቻ ናቸው፤እነዚያም በአላህ አንቀጾች የካዱት፣እነዚያ እነሱ ከሳሪዎቹ ናቸው።››

[አልዙመር፡63]

4-

አላህንﷻ ማክበርና ማላቅ፦ የዚህ አሻራ በአላህﷻ በሚያምን፣በአምልኮት በጸሎት በፍላጎትና በዓለማ እርሱን ብቻ በሚያልም ሙእምን ሕይወት ውስጥ በጣም ጎልቶ የሚታይ ነው። አላህﷻ በሰማያትና በምድር ግዛቶቹ ውስጥ ያሉትን አማኝኙ ሰው ሲያሰተነትን፣እንዲህ ከማለት ሌላ የሚለው ነገር አይኖረውም፦

(وَسِعَ رَبِّي كُلَّ شَيۡءٍ عِلۡمًا)

‹‹ጌታዬም ነገሩን ሁሉ ዕውቀቱ ሰፋ፤››

[አልአንዓም፡80]

በተጨማሪምﷻ እንዲህ ይላል፦

(رَبَّنَا مَا خَلَقۡتَ هَٰذَا بَٰطِلٗا سُبۡحَٰنَكَ)

‹‹ጌታችን ሆይ! ይኸን በከንቱ አልፈጠርከውም፤ጥራት ይገባህ፤››

[ኣል ዒምራን፡191]

ይህ ሁሉ የሚያመለክተው ልብ በፈጣሪ አምላክ ላይ የሚንጠለጠል መሆኑን፣ውዴታውን ለማትረፍ ጥረት ማድረግን፣ሸሪዓውንና ሕግጋቱን ለማክበር መትጋትን፣በምድርም ሆነ በሰማያት ለራሱም ሆነ ለሌላው ቅንጣት ያህል መጥቀምም ሆነ መጉዳት የማይችልን ከአላህ ጋር አለማሻረክን ያመለክታል። አላህን ﷻ ማላቅና ማክበር በሙእምኑ ላይ የጌትነቱ ተውሒድ ከሚተዋቸው አሻራዎች አንዱ ነው።

ፊትን ወደ አላህ ﷻ መመለስ እንጂ ሌላ የማይሰበስበው መበታተን፣ከርሱ ጋር ብቻ መገለል እንጂ ሌላ የማያስወግደው ብቸኝነት፣እርሱን በማወቅና ለርሱ ፍጹም በመሆን መደሰት ብቻ እንጂ ሌላ ነገር የማያጠፋው ሐዘን ልብ ውስጥ ይገኛል።Tags: