ጌታው (አርረብ) መኖሩን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች፦

ጌታው (አርረብ) መኖሩን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች፦
ዩኒቨርሱና ፍጥረታቱ ሁሉ የአላህን መኖር ያረጋግጣሉ። እውነት መሆኑን ያጸድቃሉ። ያምናሉ፤ሕልውናውን ይናገራሉ። አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(قَالَتۡ رُسُلُهُمۡ أَفِي ٱللَّهِ شَكّٞ فَاطِرِ ٱلسَّمَٰوَٰتِ وَٱلۡأَرۡضِۖ يَدۡعُوكُمۡ لِيَغۡفِرَ لَكُم مِّن ذُنُوبِكُمۡ وَيُؤَخِّرَكُمۡ إِلَىٰٓ أَجَلٖ مُّسَمّٗىۚ قَالُوٓاْ إِنۡ أَنتُمۡ إِلَّا بَشَرٞ مِّثۡلُنَا تُرِيدُونَ أَن تَصُدُّونَا عَمَّا كَانَ يَعۡبُدُ ءَابَآؤُنَا فَأۡتُونَا بِسُلۡطَٰنٖ مُّبِينٖ ١٠)

‹‹መልክተኞቻቸው፦ ከኀጢአቶቻችሁ እንዲምራችሁ፣ወደ ተወሰነ ጊዜም (ያለ ቅጣት) እንዲያቆያችሁ የሚጠራችሁ ሲኾን፣ሰማያትንና ምድርን ፈጣሪ በኾነው አላህ (በመኖሩ) ጥርጣሬ አለን? አሏቸው፤(ሕዝቦቹም)፦ እናንተ ብጤያችን ሰው እንጂ አይደላችሁም፤አባቶቻችን ይግገዙት ከነበሩት ልትከለክሉን ትሻላችሁ፤ግልጽንም አስረጅ (ካመጣችሁት ሌላ) አምጡልን አሉ።››

[ኢብራሂም፡10]

እርሱ ራሱ በሁሉም ነገሮች ላይ አስረጅ ለሆነው ፈጣሪ ጌታ ﷻ መኖር እንዴት ነው ማስረጃ የሚጠየቀው?

ይሁን ብለን ማስረጃዎቹን ካየን ለአብነት የሚከተሉትን እናገኛለን፦

ሙእምን (አማኝ) ሰው፣አላህ ﷻ ምንም የማይሳነው ቻይ ጌታ መሆኑን አስረግጦ የሚያውቅ፣ብቻኛው እውነተኛ አምላክ መሆኑንም በእርግጠኝነት የሚያውቅ ሰው ነው።

የምታወድሰውና የምታመሰግነው በችሮታውና በዘረጋልህ ጸጋዎቹ ምክንያት ሲሆን፣በሁሉም ሁኔታዎች አንተ አላህን ﷻ ከጃይ ነህ።

የፍጥረት (አልፍጥራህ) ማስረጃ፦

ፍጡራን ሁሉ በፈጣሪ የማመን ተፈጥሮን ይዘው ተፈጥረዋል። ከዚህ መሰረታዊ ተፈጥሮ የሚያፈነግጥ፣አላህ ﷻ ልቦናውን ያሳወረውና መንፈሱን ያጨለመበት ሰው ብቻ ነው። ተፈጥሮ የአላህን መኖር ከሚያመለክቱ ታላላቅ ማስረጃዎች አንዱ መሆኑን ከሚያስረዱት አንዱ የሚከተለው የነቢዩ ﷺ ቃል ነው፦

‹‹ሁሉም ሕጻን በተፈጥሮ (በአላህ ለማመን ዝግጅት ያለው) ሆኖ ይወለዳል። ይሁዲ፣ክርስቲያን ወይም ዞሮስትሪያን የሚያደርጉት ወላጆቹ ናቸው። ልክ እንስሳ መሰሉን እንስሳ እንደሚወልድ ማለት ነው። የተጎመደ አካለ ጎደሎ ታዩበታላችሁን? (አታዩም)።››

(በቡኻሪ የተዘገበ)

እናም እያንዳንዱ ፍጡር በፍጥረቱ የአላህን ተውሒድ የሚያረጋግጥ ሆኖ ይወለዳል። አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(فَأَقِمۡ وَجۡهَكَ لِلدِّينِ حَنِيفٗاۚ فِطۡرَتَ ٱللَّهِ ٱلَّتِي فَطَرَ ٱلنَّاسَ عَلَيۡهَاۚ لَا تَبۡدِيلَ لِخَلۡقِ ٱللَّهِۚ ذَٰلِكَ ٱلدِّينُ ٱلۡقَيِّمُ وَلَٰكِنَّ أَكۡثَرَ ٱلنَّاسِ لَا يَعۡلَمُونَ ٣٠)

‹‹ወደ እውነት ተዘንባይ ኾነህ ፊትህን ለሃይማኖት ቀጥ አድርግ፤የአላህን ፍጥረት ያችን አላህ ሰዎችን በርስዋ ላይ የፈጠረባትን (ሃይማኖት ያዙዋት)፤የአላህን ፍጥረት መለወጥ የለም፤ይህ ቀጥተኛ ሃይማኖት ነው፤ግን አብዛኛዎቹ ሰዎች አያውቁም።››

[አልሩም፡30]

ለአላህﷻ መኖር ይህ የተፈጥሮ ማስረጃ ነው።

ሰይጣናት ላልተጠናወቱት ሰው፣የአላህን መኖር የሚያመለክተው የተፈጥሮ ማስረጃ ከሁሉም ይበልጥ ጠንካራው ማስረጃ ነው። ለዚህ ነው አላህﷻ እንዲህ ያለው፦

(فِطۡرَتَ ٱللَّهِ ٱلَّتِي فَطَرَ ٱلنَّاسَ عَلَيۡهَا)

‹‹የአላህን ፍጥረት ያችን አላህ ሰዎችን በርስዋ ላይ የፈጠረባትን (ሃይማኖት ያዙዋት)፤››

[አልሩም፡30]

በተጨማሪም አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(فَأَقِمۡ وَجۡهَكَ لِلدِّينِ حَنِيفٗا)

‹‹ወደ እውነት ተዘንባይ ኾነህ ፊትህን ለሃይማኖት ቀጥ አድርግ፤››

[አልሩም፡30]

ጤናማ ተፈጥሮ የአላህን መኖር ይመሰክራል። ሰይጣናት የተጠናወቱት ሰው ግን ይህ ማስረጃ ይሰወርበትና ማስረጃ ፍለጋ ይዳክራል። ከባድ ችግርና ፈተና ላይ ሲወድቅ ግን በእጆቹ፣በዓይኖቹና በልቦናውም ወደ ጌታው በመወትወት እንዲደርስለት በቀጥታ በጤናማ ተፈጥሮው እርሱን ይማጸናል።

አላህ . . . በሰው ልጅ ተፈጥሮ ውስጥ የተቀረጸ ስም በመሆኑ ከዚህ የበለጠ ማስረጃ አያስፈልገውም።

የአእምሮ ማስረጃ፦

የአእምሮ ማስረጃዎች ፈጣሪ አምላክ ለመኖሩ እጅግ ብርቱ ከሆኑ ማስረጃዎችና ማረጋገጫዎች ውስጥ ሲሆኑ፣ከሓዲ አስተባባይ ከሆነ ሰው በስተቀር ማንም ሊያስተባብላቸው አይችልም። ከነዚህ የሚከተሉትን እናገኛለን፦

1-

ማንኛውም ፍጡር ፈጣሪ አለው። እነዚህ የቀደሙትም ሆኑ የሚቀጥሉት ፍጥረታት የፈጠራቸውና ያስገኛቸው ፈጣሪ የግድ ሊኖራቸው ይገባል። ለምን ቢባል ራሳቸውን በራሳቸው ሊፈጥሩም ሆነ በአጋጣሚ የተገኙ ሊሆኑ ስለማይችሉ ሲሆን፣አንድ ነገር ከመገኘቱ በፊት አልቦ ነበርና እንዴት አድርጎ ነው ራሱን የሚፈጥረው?! ማንኛውም ክስተት እንዲከሰት ያደረገው ሠሪ የግድ ሊኖረው ይገባል። የፍጥረታት በዚህ እጹብ ድንቅ ቅንብር፣ሳቢያና ውጤትን በሚገርም ሁኔታ በሚያስተሳስር፣ሁነቶችን እርስ በርሳቸው እንዲናበቡ አድርጎ በሚያደራጅ ሥርዓት ውስጥ መኖር በራሱ ዩኒቨርስ በአጋጣሚ ተገኘ የሚለውን ነገር ሙሉ በሙሉ ውድቅ ያደርጋል። በመሆኑም እያንዳንዱ ፍጡር ፈጣሪ ሊኖረው የግድ ነው፤እርሱም የዓለማት ጌታ አላህ ነው። አላህﷻ ይህን የአእምሮ ማስረጃ እንዲህ ሲል ገልጾታል፦

(أَمۡ خُلِقُواْ مِنۡ غَيۡرِ شَيۡءٍ أَمۡ هُمُ ٱلۡخَٰلِقُونَ ٣٥)

‹‹ወይስ ያለ አንዳች (ፈጣሪ) ተፈጠሩን? ወይስ እነርሱ ፈጣሪዎች ናቸው?››

[አልጡር፡35]

ያለ ፈጣሪ አልተፈጠሩም፤ራሳቸውን በራሳቸው አልፈጠሩምም። እናም የፈጠራቸው አላህﷻ መሆኑ የግድ ይሆናል ማለት ነው። ለዚህ ነው፣ጁበይር ብን ሙጥዐም (ረ.ዐ) ነቢዩ ﷺ የአጥጡር ምዕራፍን እየደገሙ በሚከተሉት አንቀጾች ላይ ሲደርሱ፦

(أَمۡ خُلِقُواْ مِنۡ غَيۡرِ شَيۡءٍ أَمۡ هُمُ ٱلۡخَٰلِقُونَ ٣٥ أَمۡ خَلَقُواْ ٱلسَّمَٰوَٰتِ وَٱلۡأَرۡضَۚ بَل لَّا يُوقِنُونَ ٣٦ أَمۡ عِندَهُمۡ خَزَآئِنُ رَبِّكَ أَمۡ هُمُ ٱلۡمُصَۜيۡطِرُونَ ٣٧)

‹‹ወይስ ያለ አንዳች (ፈጣሪ) ተፈጠሩን? ወይስ እነርሱ ፈጣሪዎች ናቸውን? ወይስ ሰማያትንና ምድርን ፈጠሩን? አይደለም አያረጋግጡም። ወይስ የጌታህ ግምጃ ቤቶች እነሱ ዘንድ ናቸውን? ወይስ እነሱ አሸናፊዎች ናቸውን?››

[አልጡር፡35-37]

በወቅቱ ሙሽሪክ የነበሩት ጁበይር፦

‹‹ልቤ አምልጣ ለመብረር ምንም ያህል አልቀራትም ነበር።›› ያሉት።

(በቡኻሪ የተዘገበ)

2-

በዩኒቨርሱና በፍጥረታቱ ውስጥ የሚገኙ የአላህ ታምራትና ምልክቶች። አላህﷻ

እንዲህ ብሏል፦

(قُلِ ٱنظُرُواْ مَاذَا فِي ٱلسَّمَٰوَٰتِ وَٱلۡأَرۡضِ)

‹‹፦ በሰማያትና በምድር ያለውን (ታምር) ተመልከቱ፣በላቸው፤››

[ዩኑስ፡101]

በሰማያትና በምድር ያሉትን አስተውሎ መመልከት አላህﷻ ፈጣሪ እርሱ መሆኑን ያስረዳል፤የርሱን ብቸኛ ጌትነትም ያረጋግጣል። አንድ የዐረብ ገጠሬ ጌታህን በምን አወቅኸው? ተብሎ ሲጠየቅ፣የኮቴ ዱካ ከብቱ የሄደበትን መንገድ ያመለክታል፤በጠጡም የእንስሳውን ምንነት ይጠቁማል። ባለ ቡርጆች የሆነው ሰማይ፣ባለ መንገዶች የሆነው ምድርም፣ባለ ማእበል የሆኑት ባሕሮችም ሰሚ ተመልካች የሆነ ፈጣሪ መኖሩን አያመለክቱምን?! ነበር ያለው።

ምድራዊ ቁሳዊ ዕውቀቱ የቱንም ያህል ቢመጥቅ፣ከሕዋሳት ግንዛቤ ወዲያ የሆነውን (ጓይብን) በጋረዱት መጋረጃዎች ፊት የሰው ልጅ አቅም የለሽ ደካማ ሆኖ ይቆማል። ይህን ድክመት ሊክስ የሚችለው ወሳኙ ነገር ግን በአላህ ማመን ብቻ ነው።

3-

ዓለም የተቀነባበረና ጥብቅ የሆነ ሥርዓት ያለው መሆኑ። ይህ ያስገኘውና ያቀነባበረው አንድ አምላክ፣አንድ ገዥ ባለቤት፣አንድ ጌታ መሆኑን ያረጋግጣል። ከርሱ በስተቀር ፍጥረታት ሌላ ፈጣሪ የላቸውም። ከርሱ በስተቀር ሌላ ጌታ የላቸውም። ዩኒቨርስ እኩል ሥልጣን ያላቸውና አቻ የሆኑ ሁለት ጌቶች ሊኖረው እንደማይችል ሁሉ፣አምልኮት የሚገባቸው ሁለት እውነተኛ አምላኮችም ሊኖረው ፈጽሞ አይችልም። በሁለት አቻ የሆኑ ተመሳሳይ ፈጣሪዎች የተፈጠረ ዓለም ሊኖር አለመቻሉን የመገንዘብ ስሜት በሰው ልጅ ተፈጥሮ ውስጥ የሰረጸ ጥንተ ፍጥረቱ ነው። ቀጥተኛ የሆነ ጤናማ አእምሮም በቀጥታ የሚያስተባብለው እንደሆነ ሁሉ፣ሁለት አምልኮት የሚገባቸው አምላኮች መኖርም እንዲሁ ውድቅ ይሆናል።

የሸሪዓ ማስረጃ፦

ሁሉም መለኮታዊ ሕግጋት (ሸሪዓዎች)፣ምሉእ ዕውቀት፣ጥበብና ርኅራሄ ያለው አዛኝ ፈጣሪ ጌታ መኖሩን ያመለክታሉ። እነዚህ ሕግጋት ያስገኛቸው ሕግ አውጭ የግድ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን እርሱም አላህﷻ ነው። አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(يَٰٓأَيُّهَا ٱلنَّاسُ ٱعۡبُدُواْ رَبَّكُمُ ٱلَّذِي خَلَقَكُمۡ وَٱلَّذِينَ مِن قَبۡلِكُمۡ لَعَلَّكُمۡ تَتَّقُونَ ٢١ ٱلَّذِي جَعَلَ لَكُمُ ٱلۡأَرۡضَ فِرَٰشٗا وَٱلسَّمَآءَ بِنَآءٗ وَأَنزَلَ مِنَ ٱلسَّمَآءِ مَآءٗ فَأَخۡرَجَ بِهِۦ مِنَ ٱلثَّمَرَٰتِ رِزۡقٗا لَّكُمۡۖ فَلَا تَجۡعَلُواْ لِلَّهِ أَندَادٗا وَأَنتُمۡ تَعۡلَمُونَ ٢٢)

‹‹እላንተ ሰዎች ሆይ! የፈጠራችሁን፣እነዚያንም ከናንተ በፊት የነበሩትን (የፈጠረውን) ጌታችሁን ተገዙ፤(ቅጣትን) ልትጠነቀቁ ይከጀላልና። (እርሱ) ያ ለናንተ ምድርን ምንጣፍ፣ሰማይንም ጣራ ያደረገ ነው፤ከሰማይም (ከደመና) ውሃን ያወረደ፣በርሱም ከፍሬዎች ለናንተ ሲሳይን ያወጣ ነው፤እናንተም (ፈጣሪነቱን) የምታውቁ ስትኾኑ፣ለአላህ ባላንጣዎችን አታድርጉ።››

[አልበቀራህ፡21-22]

ሁሉም መለኮታዊ መጽሐፍት ይህንኑ ይናገራሉ።

ተጨባጩ ሕዋሳዊ ማስረጃ፦

ለፈጣሪ አምላክ ሕልውና ከማስረጃዎች ሁሉ ይበልጥ ግልጹና በጣም ገዝፎ የሚታየው፣የዓይንና የሕሊና ብርሃን ባለው ሰው ሁሉ የሚጨበጠውና የሚዳሰሰው ግልጹ ሕዋሳዊ ማስረጃ ነው። ከነዚህ መካከል የሚከተሉትን እናገኛለን፦

1-

የጸሎቶች ምላሽ ማግኘት፦ የሰው ልጅ አላህንﷻ ይለምነዋል፣ይማጸነዋል፣አቤት ጌታዬ እያለ ምኞቱን እንዲሞላለት ስኬቱን ይጠይቃል፤ይጸልያል። የለመነው ምላሽ አግኝቶ ፍላጎቱ ይሞላለታል። ይህ ለፈጣሪ ጌታ መኖር ተጨባጭ ማስረጃ ነው። ራሱ የለመነውና የጠየቀው አላህን ብቻ ሲሆን፣መልስ የሰጠውና ያሳከለትም እርሱ ብቻ ነው። ይህ መሆኑን ለማኙ ሰው ራሱ በተጨባጭ አይቷል ማለት ነው። እንደዚሁም ባለፉት ቀደምት አበው ዘመንም ሆነ በኛ ዘመን ለዚህ አብነት የሚሆኑ አላህﷻ ዱዓቸውን የሰማላቸውና የለመኑትን ስላገኙ ሰዎች አያሌ ምሳሌዎችን እንሰማለን። ይህ ለፈጣሪ አምላክ መኖር ተጨባጭ የሆነ ቁሳዊ ማስረጃ ሲሆን፣ይህን በተመለከተ ቁርኣን ውስጥ በርካታ አንቀጾች ቀርበዋል። ከነዚህም የሚከተሉትን እናገኛለን፦

(وَأَيُّوبَ إِذۡ نَادَىٰ رَبَّهُۥٓ أَنِّي مَسَّنِيَ ٱلضُّرُّ وَأَنتَ أَرۡحَمُ ٱلرَّٰحِمِينَ ٨٣ فَٱسۡتَجَبۡنَا لَهُ)

‹‹አዩብንም (እዮብን) ጌታውን ፦ እኔ መከራ አገኘኝ አንተም ከአዛኞች ሁሉ ይበልጥ አዛኝ ነህ፣ሲል በተጣራ ጊዜ (አስታውስ)። ለርሱም ጥሪውን ተቀበልነው፤››

[አልአንቢያ፡83-84]

በተጨማሪም ሌሎች ብዙ ቁርኣናዊ አንቀጾች ይገኛሉ።

ኤቲዝም የአእምሮ ሕመም ነው። የአመለካከት መቃወስና የእሳቤ መዛባት ነው።

2-

ፍጥረታት የሕልውናቸው ምስጢርና መሰረት ወዳለበት መመራታቸው። የሰው ልጅ ገና ከእናቱ ማሕጸን ሲወጣ የእናቱን ጡት እንዲጠባ የመራው ማነው?! ሁድሁድ የሚባለውን ወፍ፣ከርሱ ሌላ የማያየውንና ከርሰ ምድር ውስጥ ውሃ የሚገኝባቸውን ቦታዎች ለይቶ እንዲያውቅ የመራው ማነው?! እንዲህ በማለት ጠናገረው አላህﷻ ነው፦

(رَبُّنَا ٱلَّذِيٓ أَعۡطَىٰ كُلَّ شَيۡءٍ خَلۡقَهُۥ ثُمَّ هَدَىٰ ٥٠)

‹‹ጌታችን፣ያ ለፍጥረቱ ነገርን ሁሉ (የሚያስፈልገውን) የሰጠ፣ከዚያም የመራው ነው አለው።››

[ጣሃ፡50]

3-

ነቢያትና መልእክተኞች ይዟቸው የመጡት ታምራትና ምልክቶች፦ እነዚህ ለነቢዮችና አላህ ለመረጣቸው መልክተኞቹ እውነተኛነት ማረጋገጫ ይሆኑ ዘንድ የተሰጧቸው ምልክቶች ናቸው። እያንዳንዱ ነቢይ ይዞ የመጣው መልእክት፣በእርግጥ ከርሱ በስተቀር አምላክም ሆነ ጌታ የሌለ ከሆነው አንድ ፈጣሪ አምላክ ዘንድ መሆኑን የሚያረጋግጥ ተአምር ይዞ ነው ወደ ሕዝቦቹ የተላከው።

ኤቲዝም የአእምሮ ሕመም ነው። የአስተሳሰብ መዛባት ነው። የሕሊና መታወርና የሕይወት ብክነት ነው



Tags: