የ‹‹ላ እላሀ እልላሏህ›› ትሩፋት ፦

የ‹‹ላ እላሀ እልላሏህ›› ትሩፋት ፦
የአላህ መልክተኛ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦

‹‹እስላም በአምስት (ማእዘኖች) ላይ ነው የተመሰረተው፡፡ (እነሱም) ፡- ከአላህ በስተቀር ሌላ አምላክ አለመኖሩንና ሙሐመድ የርሱ አገልጋይና መልእክተኛው መሆናቸውን መመስከር፣ሶላትን ደንቡን ጠብቆ አዘውትሮ መስገድ፣ዘካን መስጠት፣የሐጅ ሥርዓተ ጸሎት መፈጸምና ረመዷንን መጾም ናቸው፡፡››

(በቡኻሪ የተዘገበ)

በተጨማሪም ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦

‹‹እኔ ካልኩትና ከኔ በፊት የነበሩ ነቢያትም ካሉት (ዱዓእ) ሁሉ በላጩ ‹ላ እላሀ እል'ላል'ሏሁ ወሕደሁ ላሸሪከ ለሁ፣ለሁልሙልኩ ወለሁልሐምዱ፣ወሁወ ዐላ ኩል'ሊ ሸይእን ቀዲር› ማለት ነው፡፡››

ትርጉሙ ፦ ከአላህ በስተቀር ሌላ አምላክ የለም፡፡ እርሱ አንድ ነው፤ተጋሪ (ሸሪክ) የለውም፡፡ ንግሥና የርሱ ብቻ ነው፡፡ ምሥጋና ሁሉ የርሱ ነው፡፡ እርሱ በሁሉም ነገር ላይ ቻይ ነው፣ማለት ነው።

(በትርምዚ የተዘገበ)

ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦

‹‹የአላህ ነቢይ ኑሕ ሊሞቱ ሲሉ ለወንድ ልጃቸው እንዲህ አሉ፦ በ‹ላ እላሀ እልላሏህ› (ከአላህ በስተቀር ሌላ አምላክ አለመኖሩን እንድትመሰክር) አዝዤሃለሁ፤ሰባቱ ሰማያትና ሰባቱ ምድሮች በአንድ ወገን ቢደረጉና ‹‹ላ እላሀ እልላሏህ›› በአንዱ የሚዛን ሳህን ቢቀመጥ፣‹‹ላ እላሀ እልላሏህ›› በእርግጥ ሚዛኑን ይደፋ ነበር።››

(በቡኻሪ ተዘገበ)

አላህ ﷻ ጀነትን ያጌጣት፣ጀሀነምን የለኮሳት፣የበጎ ሥራዎችንና የክፉ ሥራዎችን ገበያ የዘረጋው ለ‹‹ላ እላሀ እልላሏህ›› ብሎ ነው።

ለ‹‹ላ እላሀ እልላሏህ›› መሟላት ያለባቸው መስፈርቶች ፦

1-

ትርጉሙንና ይዘቱን ማወቅ ፦

ይህ፣ቃሉን የሚናገረው ሰው ትርጉሙንና አምላክነትን ከአላህ በቀር ከሌላው ሁሉ የማስተባበልንና እወነተኛ አምላክነትን ለአላህ ﷻ ብቻ አጽንቶ የማጽደቅ ይዘቱን ማወቅ ማለት ነው። አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(فَٱعۡلَمۡ أَنَّهُۥ لَآ إِلَٰهَ إِلَّا ٱللَّهُ)

‹‹እነሆ ከአላህ ሌላ አምላክ አለመኖሩንም ዕወቅ፤››

[ሙሐመድ፡19]

2-

እርግጠኝነት ፦

እርግጠኝነት (የቂን) በትርጉሙም ሆነ በይዘቱ ላይ የቃሉ ተናጋሪ አንድም ጥርጣሬ በልቡ ውስጥ አለማሳደር ማለት ነው። አላህﷻ እንዲህ ብሏልና ፦

(إِنَّمَا ٱلۡمُؤۡمِنُونَ ٱلَّذِينَ ءَامَنُواْ بِٱللَّهِ وَرَسُولِهِۦ ثُمَّ لَمۡ يَرۡتَابُواْ وَجَٰهَدُواْ بِأَمۡوَٰلِهِمۡ وَأَنفُسِهِمۡ فِي سَبِيلِ ٱللَّهِۚ أُوْلَٰٓئِكَ هُمُ ٱلصَّٰدِقُونَ ١٥)

‹‹(እውነተኛዎቹ) ምእምናን፣እነዚያ በአላህና በመልክተኛው ያመኑት፣ከዚያም ያልተጠራጠሩት፣በገንዘቦቻቸውና በነፍሶቻቸውም በአላህ መንገድ የታገሉት ብቻ ናቸው፤እነዚያ እነሱ እውነተኞቹ ናቸው።››

[አልሑጁራት፡15]

ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦

‹‹ከአላህ በቀር ሌላ እውነተኛ አምላክ አለመኖሩንና እኔ የአላህ መልክተኛ መሆኔን በመመስከር፣(በሁለቱ ቃለ ምስክርነት) ምንም ጥርጣሬ ሳያድርበት አላህን የሚገናኝ የአላህ አገልጋይ ጀነት የሚገባ ቢሆን እንጂ አንድም የለም።››

(በሙስሊም የተዘገበ)

3-

ቃለ ተውሒድ ግዴታ የሚያደርገውን ሁሉ በልብ አጽድቆ በመቀበል በአንደበትም ማረጋገጥ ፦

መቀበል ሲባል እዚህ ላይ እምቢታንና ኩራትን የሚጻረር ሙሉ ተቀባይነት ማለት ነው። አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(إِنَّا كَذَٰلِكَ نَفۡعَلُ بِٱلۡمُجۡرِمِينَ ٣٤ إِنَّهُمۡ كَانُوٓاْ إِذَا قِيلَ لَهُمۡ لَآ إِلَٰهَ إِلَّا ٱللَّهُ يَسۡتَكۡبِرُونَ ٣٥)

‹‹እኛ በአመጠኞች ሁሉ፣እንደዚሁ እንሠራለን። እነርሱ፣ከአላህ ሌላ አምላክ የለም በተባሉ ጊዜ ይኮሩ ነበር።‌››

[አልሶፋት፡34-35]

4-

ቃሉ ለሚያመለክተው ነገር ታዛዥና ተገዥ መሆን ፦

ይህ ደግሞ መስካሪው አላህ ﷻ ያዘዘውን ነገር የሚፈጽም፣ከከለከለው ነገር የሚታቀብ መሆን ማለት ነው። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(وَمَن يُسۡلِمۡ وَجۡهَهُۥٓ إِلَى ٱللَّهِ وَهُوَ مُحۡسِنٞ فَقَدِ ٱسۡتَمۡسَكَ بِٱلۡعُرۡوَةِ ٱلۡوُثۡقَىٰۗ وَإِلَى ٱللَّهِ عَٰقِبَةُ ٱلۡأُمُورِ ٢٢)

‹‹እርሱ መልካም ሠሪ ኾኖ ፊቱን ወደ አላህ የሚሰጥም ሰው፣ጠንካራን ገመድ በእርግጥ ጨበጠ፤የነገሩም ሁሉ ፍጻሜ ወደ አላህ ነው።››

[ሉቅማን፡22]

ባርነት በመሰረቱ የልቦና ተገዥነትና የአእምሮ ባርነት ሲሆን፣ልብ ለተገዛለት ባሪያው ነው።

5-

እውነተኝነት ፦

እውነተኝነት ማለት መስካሪው ከልቡ እርግጠኛ ሆኖ በአንደበቱ በመናገር ማረጋገጥ ማለት ነው። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(وَمِنَ ٱلنَّاسِ مَن يَقُولُ ءَامَنَّا بِٱللَّهِ وَبِٱلۡيَوۡمِ ٱلۡأٓخِرِ وَمَا هُم بِمُؤۡمِنِينَ ٨ يُخَٰدِعُونَ ٱللَّهَ وَٱلَّذِينَ ءَامَنُواْ وَمَا يَخۡدَعُونَ إِلَّآ أَنفُسَهُمۡ وَمَا يَشۡعُرُونَ ٩)

‹‹ከሰዎችም በአላህና በመጨረሻው ቀን አምነናል የሚሉ አልሉ፤እነርሱም አማኞች አይደሉም። አላህንና እነዚያን ያመኑትን (ሰዎች) ያታልላሉ፤የማያውቁ ሲኾኑ ነፍሶቻቸውን እንጂ ሌላን አያታልሉም።››

[አልበቀራህ፡8-9]

6-

ቅንነትና ፍጹምነት ፦

ይህ ደግሞ ቃለ ተውሒዱን የአላህን ውዴታ በመሻትና እርሱን በማሰብ ፍላጎት ብቻ በፍጹምነት መመስከር ማለት ነው። አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(وَمَآ أُمِرُوٓاْ إِلَّا لِيَعۡبُدُواْ ٱللَّهَ مُخۡلِصِينَ لَهُ ٱلدِّينَ حُنَفَآءَ وَيُقِيمُواْ ٱلصَّلَوٰةَ وَيُؤۡتُواْ ٱلزَّكَوٰةَۚ وَذَٰلِكَ دِينُ ٱلۡقَيِّمَةِ ٥)

‹‹አላህን ሃይማኖትን ለርሱ ብቻ አጥሪዎች፣ ቀጥተኞች ኾነው ሊግገዙት፣ሶላትንም አስተካክለው ሊሰግዱ፣ዘካንም ሊሰጡ እንጅ ያልታዘዙ ሲኾኑ (ተለያዩ)። ይህም የቀጥተኛይቱ (ሃይማኖት) ድንጋጌ ነው።››

[አልበይናህ፡5]

7-

ይህን ቃለ ምስክርነት መውደድ፣ደንቦቹንና መስፈርቶቹን አሟልተው የሚተገብሩትን፣በርሱ የሚገዙትን መስካሪዎቹን ምእመናን ሁሉ መውደድ፤የሚጻረሩትን መጥላት ማለት ነው። አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(وَمِنَ ٱلنَّاسِ مَن يَتَّخِذُ مِن دُونِ ٱللَّهِ أَندَادٗا يُحِبُّونَهُمۡ كَحُبِّ ٱللَّهِۖ وَٱلَّذِينَ ءَامَنُوٓاْ أَشَدُّ حُبّٗا لِّلَّهِ)

‹ከሰዎችም ከአላህ ሌላ ባላንጣዎችን (ጣዖታትን)፣አላህን እንደሚወዱ የሚወዷቸው ኾነው የሚይዙ አልሉ፤እነዚያ ያመኑትም፣አላህን በመውደድ (ከነርሱ) ይበልጥ የበረቱ ናቸው፤››

[አልበቀራህ፡165]

ልብ ለአላህ ያለው ፍቅር በጨመረ ቁጥር፣ለአላህ ያለው ተገዥነትና ከርሱ በቀር ካለው ሁሉ ያለው ነጻነት እየጨመረ ይሄዳል ።

የ ‹‹ላ እላሀ እልላሏህ›› ትርጉም እንግዲህ ይህ ነው፤መስፈርቶቹም እነዚህ ናቸው። አላህ ﷻ ዘንድ መድህን ለማግኘት ምክንያት የሚሆነውም ይኸው ነው። ሐሰን አልበስሪ፣አንዳንድ ሰዎች ‹‹ላ እላሀ እልላሏህ›› ያለ ሰው ጀነት ይገባል፣ይላሉ ሲባሉ ፦ ‹‹ላ እላሀ እልላሏህ›› ብሎ ግዴታውንና መስፈርቱን ያሟላ ሰው ጀነት ይገባሉ፣ብለዋል።

እናም ‹‹ላ እላሀ እልላሏህ›› በቃሉ መሰረት የሚሠራና መስፈርቶቹን የሚያሟላ ካልሆነ በስተቀር መስካሪውን አይጠቅመውም። ቃሉ ግዴታ የሚያደርገውን መተግበር ከመተው ጋር ቃሉን ብቻ በአንደበቱ የሚደግም ሰው ግን ቃሉን ከተግባር ጋር እስካላጣመረ ድረስ ተጠቃሚ አይሆንም።

‹‹ላ እላሀ እልላሏህ››ን የሚያፈርሱ ነገሮች ፦

1-

ማጋራት (ሽርክ) ፦

እዚህ ላይ ሽርክ ሲባል ማለት የተፈለገው፣ ከሃይማኖቱ ጎራ የሚያስጣውን፣በዚያ ላይ የሞተ ሰው የአላህ ምሕረት የማያገኝበትን ዐቢይ ማጋራትን (ሽርክ) ነው። ይህም የአላህ ﷻ ብቻ መብቶች በሆኑት የአምላክነትና የጌትነት መብቶቹ ሌሎችን ማጋራት፣በስሞቹና በባሕርያቱ ለአላህ ﷻ ባላንጣ ማድረግ ነው። አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(إِنَّ ٱللَّهَ لَا يَغۡفِرُ أَن يُشۡرَكَ بِهِۦ وَيَغۡفِرُ مَا دُونَ ذَٰلِكَ لِمَن يَشَآءُۚ وَمَن يُشۡرِكۡ بِٱللَّهِ فَقَدۡ ضَلَّ ضَلَٰلَۢا بَعِيدًا ١١٦)

‹‹አላህ በርሱ የማጋራትን (ወንጀል) አይምርም፤ከዚህም ወዲያ ያለውን፣ለሚሻው ሰው ይምራል። በአላህም የሚያጋራ ሰው (ከእውነት) የራቀን መሳሳት በእርግጥ ተሳሳተ።››

[አልኒሳእ፡116]

ማንን ሰው አላህን ﷻ መጥራትና እርሱን መለመን የሚገባው በስሞቹ ነው። የተፈቀደውና የታዘዘው መጥራት (ዱዓእ) ቀጥሎ ባለው ቃሉ ውስጥ የተመለከተው ነው። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

( وَلِلَّهِ ٱلۡأَسۡمَآءُ ٱلۡحُسۡنَىٰ فَٱدۡعُوهُ بِهَاۖ وَذَرُواْ ٱلَّذِينَ يُلۡحِدُونَ فِيٓ أَسۡمَٰٓئِهِۦۚ سَيُجۡزَوۡنَ مَا كَانُواْ يَعۡمَلُونَ ١٨٠ )

‹‹ለአላህም መልካም ስሞች አሉት፤(ስትጸልዩ) በርሷም ጥሩት፤እነዚያንም ስሞቹን የሚያጣምሙትን ተውዋቸው፤ይሠሩት የነበሩትን ነገር በእርግጥ ይመነዳሉ።››

[አልአዕራፍ፡180]

ኢማም አቡ ሐኒፋ

አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(وَلَقَدۡ أُوحِيَ إِلَيۡكَ وَإِلَى ٱلَّذِينَ مِن قَبۡلِكَ لَئِنۡ أَشۡرَكۡتَ لَيَحۡبَطَنَّ عَمَلُكَ وَلَتَكُونَنَّ مِنَ ٱلۡخَٰسِرِينَ ٦٥ بَلِ ٱللَّهَ فَٱعۡبُدۡ وَكُن مِّنَ ٱلشَّٰكِرِينَ ٦٦)

‹‹ብታጋራ፣ሥራህ በእርግጥ ይታበሳል፤በእርግጥም ከከሐዲዎቹ ትኾናለህ ማለት ወደ አንተም ወደነዚያም ካንተ በፊት ወደነበሩት በእርግጥ ተወርዷል። ይልቅ አላህን ብቻ ተገዛም፤ከአመስጋኞቹም ኹን።››

[አልዙመር፡65-66]

2-

በራሱና በአላህ መካከል የሚጠራቸው፣ ምልጃቸውን የሚለምናቸው፣በነርሱ ላይ የሚተማመንና የሚመካ፣አምልኮ የሚያደርግላቸው የሆኑ አገናኞችን ያደረገ ሰው፣በዚህ ድርጊቱ ‹‹ላ እላሀ እልላሏህ››ን አፍርሷል፤ተጻርሯል።

3-

አላህ ከርሱ በስተቀር ሌላ የማይቀበል ከሆነው ከእስላም ውጭ መሆናቸውን የተጠራጠረ በመሆኑ፣አጋሪዎችን (ሙሽሪኮችን) ከሓዲ ያላደረገ፣ወይም ከሓዲ መሆናቸውን የተጠራጠረ፣ወይም መንገዳቸውን ትክክለኛ አድርጎ የወሰደ ሰው ራሱ ከሐዲ (ካፍር) ሆኗል። ከአላህ በቀር ሌላን ያመለከ ወይም ለአላህ ብቻ የሚገባውን አምልኮት ለሌላ ያስተላለፈ ወይም የአይሁዶችን፣የክርስቲያኖችንና የጣዖት አምላኪዎችን ክሕደት (ኩፍር) የተጠራጠረ፣ወይም አድራጊው ከሓዲ መሆኑ በሸሪዓዊ ማስረጃ ከተረጋገጡትና ሙሽሪኮች ከሚከተሏቸውና ከሚፈጽሟቸው ነገሮች ውስጥ አንዱንም ነገር ትክክለኛ አድርጎ የወሰደ ሰው ከሓዲ (ካፍር) ሆኗል።

4-

የነቢዩ ﷺ ያልሆነው መመሪያ ከርሳቸው መመሪያ ይበልጥ የተሟላ ነው፣ፍርድና ብያኔውም ከርሳቸው ይበልጥ የተሟላ ነው ብሎ የሚያምን ሰው ከሓዲ (ካፍር) ሆኗል። ሰው ሠራሽ ሕጎችንና የጎሳ ወግና ልማዶችን ከእስላማዊ ሸሪዓ የሚያስበልጥ፣ወይም በነርሱ መዳኘትን የሚፈቀድ አድርጎ የሚያምን፣ወይም እነሱም አንደ እስላማዊ ሸሪዓ መሆናቸውን የሚያምን ሰው . . ይህ ሁሉ በኃያሉ አላህ መካድ ነው። አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(وَمَن لَّمۡ يَحۡكُم بِمَآ أَنزَلَ ٱللَّهُ فَأُوْلَٰٓئِكَ هُمُ ٱلۡكَٰفِرُونَ ٤٤)

‹‹አላህም ባወረደው ነገር ያልፈረደ ሰው፣እነዚያ ከሓዲዎቹ እነርሱ ናቸው።››

[አልማኢዳህ፡44]

በተጨማሪም አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(فَلَا وَرَبِّكَ لَا يُؤۡمِنُونَ حَتَّىٰ يُحَكِّمُوكَ فِيمَا شَجَرَ بَيۡنَهُمۡ ثُمَّ لَا يَجِدُواْ فِيٓ أَنفُسِهِمۡ حَرَجٗا مِّمَّا قَضَيۡتَ وَيُسَلِّمُواْ تَسۡلِيمٗا ٦٥)

‹‹በጌታህም እምላለሁ (አላህ በራሱ መማሉ ነው) በመካከላቸው በተከራከሩበት ፍርድ እስከሚያስፈርዱህ፣ከዚያም ከፈረድከው ነገር በነፍሶቻቸው ውስጥ ጭንቀትን እስከማያገኙና ፍጹም መታዘዝንም እስከሚታዘዙ ድረስ አያምኑም (ምእምን አይሆኑም)።››

[አልኒሳእ፡65]

5-

ረሱል ﷺ ይዘው የመጡትን በተግባር እየፈጸመው ቢሆን እንኳ የሚጠላው ሰው ከሓዲ (ካፍር) ነው። ሶላትን የጠላ ሰው የሚሰግድ ቢሆን እንኳ፣የአላህን ትእዛዝ ያልወደደ በመሆኑ ከሓዲ (ካፍር) ነው። ከ‹‹ላ እላሀ እልላሏህ›› መስፈርቶች መካከል ከአላህ ﷻ የተላለፈውን ሁሉ መውደድ አንዱ ነው። ረሱል ﷺ ይዘው የመጡትን የጠላ ሰው ‹‹ሙሐመድ የአላህ መልክተኛ መሆናቸውን እመሰክራለሁ›› የሚለውን የቃለ ተውሒድ ክፍል አላረጋገጠም። ቃሉ ግዴታ የሚያደርገው ነቢዩﷺ ይዘው የመጡትን ሁሉ መቀበልና ከልብ መውደድ ነውና።

6-

ሃይማኖቱንና ይዘውት የመጡትን ነቢይ ﷺ ማክበር ግዴታው እየሆነ ያላከበረ በመሆኑ፣ አማኞች የነበሩ ሰዎች በአላህ መልክተኛና በባልደረቦቻቸው ላይ ‹‹እንደኛዎቹ የቁርኣን ዐዋቂዎች ሆዳሞች፣ሲናገሩ ዋሾዎችና ውጊያ ላይ ጠላትን ሲገናኙ ፈሪዎች የሆኑ ሰዎችን አይተን አናውቅም›› በማለት በተሳለቁ ጊዜ፣አላህ ﷻ ክሕደት (ኩፍር) የበየነባቸው በመሆኑ፣ከአላህ ሃይማኖት ውስጥ በአንድም ነገር ወይም በምንዳውና በቅጣቱ ያፌዘና የተሳለቀ ሰው፣ከሓዲ (ካፍር) ነው። በዚህ ስላቃቸው ሳቢያ አላህﷻ የሚከተለውን አስተላልፏል ፦

(وَلَئِن سَأَلۡتَهُمۡ لَيَقُولُنَّ إِنَّمَا كُنَّا نَخُوضُ وَنَلۡعَبُۚ قُلۡ أَبِٱللَّهِ وَءَايَٰتِهِۦ وَرَسُولِهِۦ كُنتُمۡ تَسۡتَهۡزِءُونَ ٦٥ لَا تَعۡتَذِرُواْ قَدۡ كَفَرۡتُم بَعۡدَ إِيمَٰنِكُمۡ)

‹‹በእርግጥ ብትጠይቃቸው እኛ የምንዘባርቅና የምንጫወት ብቻ ነበርን ይላሉ፤በአላህና በአንቀጾቹ፣በመልክተኛውም ታላግጡ ነበራችሁን በላቸው? አታመካኙ፣ከእምነታችሁ በኋላ በእርግጥ ከዳችሁ፤››

[አልተውባህ፡65-66]

ከዚያ በፊት ምእመናን የነበሩ ቢሆንም አላህ ﷻ የክሕደት (የኩፍር) ውሳኔ አስተላልፎባቸዋል። ቀጥሎ የቀረበው የአላህﷻ ቃልም ይህንኑ ያመለክታል ፦

(قَدۡ كَفَرۡتُم بَعۡدَ إِيمَٰنِكُمۡ)

‹‹ከእምነታችሁ በኋላ በእርግጥ ከዳችሁ፤››

[አልተውባህ፡66]

የተናገሩትን ከመናገራቸው በፊት ምእመናን መሆናቸውን አጽንቶላቸው፣የጉዞ ድካም ለመርሳት በማሰብ ለቀልድ፣ለፌዝና ለጨዋታ ያሉትን ያሉ ቢሆንም በድርጊታቸው ክሕደት (ኩፍር) በይኖባቸዋል።

7-

ድግምት ፦

ድግምት (ስሕር) በአእምሮና በአካል ላይ ተጽእኖ የሚያሳድሩ የጥንቆላና የምትሃት ነገሮች ሲሆን፣ግድያንና ባልና ሚስት መለያየትን የሚያስከትል እኩይ ሥራ ነው። ድግምትና ጥንቆላ ክሕደት (ኩፍር) ናቸው። አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(وَلَقَدۡ عَلِمُواْ لَمَنِ ٱشۡتَرَىٰهُ مَا لَهُۥ فِي ٱلۡأٓخِرَةِ مِنۡ خَلَٰقٖ)

‹‹የገዛውም ሰው፣ለርሱ በመጨረሻይቱ አገር ምንም ዕድል የሌለው መኾኑን በእርግጥ ዐወቁ፤››

[አልበቀራህ፡102]

ይህ የመዳን ዕድል የለውም ማለት ሲሆን፣ከዚህ በማስቀደም እንዲህ ብሏል፦

(وَمَا يُعَلِّمَانِ مِنۡ أَحَدٍ حَتَّىٰ يَقُولَآ إِنَّمَا نَحۡنُ فِتۡنَةٞ فَلَا تَكۡفُرۡ)

‹‹፦ እኛ መፈተኛ ነንና አትካድ፣እስከሚሉ ድረስ አንድንም አያስተምሩም፤››

[አልበቀራህ፡102]

ረሱልﷺ እንዲህ ብለዋል፦

‹‹ሰባቱን አውዳሚ ነገሮች ተጠንቀቁ›› አሉ፤ የአላህ መልክተኛ ሆይ! ምንድን ናቸው? ሲባሉ፣በአላህ ማጋራት (ሽርክ)፣አላህ እርም ያደረገውን ነፍስ ያለ ሕግ አግባብ መግደል፣አራጣ መብላት፣የየቲም ገንዘብ መብላት፣ከጦር ሜዳ መሸሽና በጋብቻ የተጠበቁ ይዋሃን ምእመናትን በዝሙት ስም ማጥፋት ናቸው›› አሉ።

(በቡኻሪ የተዘገበ)

በተጨማሪም ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦

‹‹ገመድ ቋጥሮ ትፍ ትፍ ያለበት ሰው ድግምት ደግሟል፤ድግምት የፈጸመ ሰው ደግሞ በአላህ አጋርቷል፤(ጥቅም ያስገኛል ወይም ጉዳት ያስወግዳል በሚል እምነት) ክታብ ነገር ያንጠለጠለ ሰው፣ለዚያ ነገር ይተዋል።››

(በነሳኢ የተዘገበ)

ኮከብ ቆጠራና በቡርጆች (ፈለኮች) በምድር የሚከሰቱ ሁነቶችን መተንተንም ከድግምት (ስሕር) ይቆጠራል። አቡ ዳውድ እብን ዐባስን በመጥቀስ በዘገቡት ሐዲሥ የአላህ መልክተኛ ﷺ እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹ከከዋክብት አንድ ዕውቀት የቀሰመ ሰው አንድ ክፍል ድግምትን ቀስሟል፤የጨመረም ይጨምል።››

(በበይሀቂ የተዘገበ)

አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(وَلَا يُفۡلِحُ ٱلسَّاحِرُ حَيۡثُ أَتَىٰ ٦٩ )

‹‹ድግምተኛም በመጣበት ስፍራ ሁሉ አይቀናውም (አልን)።››

[ጣሃ፡69]

የሚፋቀሩ ሰዎችን መለያየትና መስተፋቅርም አንዱ የድግምት አካል ነው።

ጠቃሚ ዕውቀት አንድን የአላህ አገልጋይ ወደ አላህ ተውሒድ የሚወስድ፣ ከርሱ ጋር በተጣጣመ ሰብአዊነትን የሚያገለግልና ለሰው ልጆች በጎነት የሚጠቅም ዕውቀት ነው። ጎጂ ዕውቀት ደግሞ ሰውን በአላህ ወደ ማጋራትና ወደ ሽርክ የሚወስድ፣ለሰው ልጆች ጎጂና እኩይ የሆነ ዕውቀት ነው።

8-

ሙስሊሞችን በመጻረር ከሙሽሪኮች ጎን መቆምና እነሱን መደገፍ። ይህም በቀጣዩ የአላህﷻ ቃል የተጠቀሰው ረዳትነት (ተወልሊ) ነው ፦

(وَمَن يَتَوَلَّهُم مِّنكُمۡ فَإِنَّهُۥ مِنۡهُمۡ)

‹‹ከናንተም ውስጥ ረዳቶች የሚያደርጋቸው ሰው እርሱ ከነርሱ ነው፤››

[አልማኢዳህ፡51]

ረዳት አድርጎ መያዝ (አትተወልሊ) ከመውደድና ወደዚያ ከማዘንበል (አልሙዋላት) የተለየ ነው። ይኸኛው ውዴታን፣ልባዊ ቀረቤታንና ጉድኝትን የሚያመለክት በመሆኑ ከከባዳ ኃጢአቶች አንዱና ከክሕደት ያነሰ ነው። ተወልሊ ግን ሙስሊሞችን የሚያጠቃና የሚዋጋቸውን ወገን ማገዝ፣ከነሱ ጋር በሙስሊሞች ላይ ማሴር ሲሆን ይህ የመናፍቃን ባሕሪ ነው። ለዓለማዊ ጥቅም ብሎ ሙሽሪኮችን ረዳት አድርጎ የያዘ ሙስሊም አደገኛ ሁኔታ ላይ ወድቋል።

9-

ሙሐመድ ﷺ የተላኩበት እስላማዊ ሸሪዓ በሁሉም ሸሪዓዎች (ሕግጋት) ላይ የበላይ ተቆጣጣሪና የቀደሙትን ሁሉ የሻረ ሕግ በመሆኑ፣አላህምﷻ ከእስላም በስተቀር ሌላውን የማይቀበል በመሆኑ፣ከሙሐመድﷺ ሸሪዓ ማፈንገጥ ይቻላል ብሎ የሚያምን ሰው ከሐዲ (ካፍር) ይሆናል። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(إِنَّ ٱلدِّينَ عِندَ ٱللَّهِ ٱلۡإِسۡلَٰمُ)

‹‹አላህ ዘንድ (የተወደደ) ሃይማኖት እስላም ብቻ ነው።››

[ኣል ዒምራን፡19]

በተጨማሪምﷻ እንዲህ ብሏል፦

(وَمَن يَبۡتَغِ غَيۡرَ ٱلۡإِسۡلَٰمِ دِينٗا فَلَن يُقۡبَلَ مِنۡهُ وَهُوَ فِي ٱلۡأٓخِرَةِ مِنَ ٱلۡخَٰسِرِينَ ٨٥)

‹‹ከእስላም ሌላ ሃይማኖትን የሚፈልግ ሰው፣ፈጽሞ ከርሱ ተቀባይ የለውም፤እርሱም በመጨረሻይቱ ዓለም ከከሳሪዎቹ ነው።››

[ኣል ዒምራን፡85]

አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(قُلۡ إِن كُنتُمۡ تُحِبُّونَ ٱللَّهَ فَٱتَّبِعُونِي يُحۡبِبۡكُمُ ٱللَّهُ وَيَغۡفِرۡ لَكُمۡ ذُنُوبَكُمۡۚ وَٱللَّهُ غَفُورٞ رَّحِيمٞ ٣١ قُلۡ أَطِيعُواْ ٱللَّهَ وَٱلرَّسُولَۖ فَإِن تَوَلَّوۡاْ فَإِنَّ ٱللَّهَ لَا يُحِبُّ ٱلۡكَٰفِرِينَ ٣٢)

‹‹በላቸው፦ አላህን የምትወዱ እንደኾናችሁ፣ ተከተሉኝ፤አላህ ይወዳችኋልና፤ኃጢአቶቻችሁንም ለናንተ ይምራልና፤አላህም መሓሪ አዛኝ ነው።››

[ኣል ዒምራን፡31-32]

ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦

‹‹ነፍሴ በእጁ በሆነችው [አላህ] እምላለሁ፣ከዚህ ሕዝብ (ኡምማ) ውስጥ ስለኔ የሰማና በተላክሁበት ነገር ሳያምን የሞተ ማንኛውም ይሁዲ ይሁን ክርስቲያን፣(ዕጣ ፈንታው) ከእሳት ጓዶች አንዱ መሆን ብቻ ነው።››

(በሙስሊም የተዘገበ)

ለዚህ ሌላው ምሳሌ አንዳንድ ማይማን ሰዎች፣ጻድቃን ‹‹አውሊያእ›› የሚሏቸው ሰዎች ነቢዩ ሙሐመድን ﷺ ለመከተል አይገደዱም፣የሚል እምነት የሚያራምዱ ሲሆን፣ይህም ክሕደት (ኩፍር) እና ከእስላም ማፈንገጥ ነው።

ልብ ከሁሉም ዞር ብሎና ወደ እወነት አዘንባይ ሆኖ ወደ አላህ ብቻ ሙሉ በሙሉ ካልዞረ፣ሙሽሪክ ይሆናል።

10-

ከአላህ ሃይማኖት በጥቅሉ ያፈነገጠና ያልተገበረው ሰው ከሐዲ (ካፍር) ይሆናል። ሙሉ በሙሉ ከመተግበር አፈንግጦ በያዘው የክሕደት መንገድ የተብቃቃ ሰው፣ወደ እስላም ወይም ወደ ትምሕርቶቹ ጥሪ ሲደረግለት እምቢ ብሎ ያፈነገጠ ወይም ካወቀ በኋላ ከመተግበርና ከመቀበል ያፈነገጠ ሰውም ከሐዲ (ካፍር) ይሆናል።

‹‹ላ እላሀ እልላሏህ››ን የሚጻረሩትንና የሚያፈርሱትን ነገሮች በተመለከተ ሆን ተብለውና እየታወቁ እስከተፈጸሙ ድረስ ለቀልድና ለፌዝም ይሁን በፍርሃት የተፈጸሙትን አይለይም። ይህ ተገዶና ምርጫ አጥቶ ከልቡ ሳይሆን በአንደበቱ ብቻ የክሕደት ቃል የተናገረውን ሰው አያካትትም። አላህﷻ እንዲህ ብሏልና ፦

(إِلَّا مَنۡ أُكۡرِهَ وَقَلۡبُهُۥ مُطۡمَئِنُّۢ بِٱلۡإِيمَٰنِ وَلَٰكِن مَّن شَرَحَ بِٱلۡكُفۡرِ صَدۡرٗا)

‹‹ልቡ በእምነት የረጋ ኾኖ (የክሕደት ቃል ለመናገር) የተገደደ ሰው ብቻ ሲቀር፤ግን ልባቸውን በክሕደት የከፈቱ ሰዎች፣››

[አልነሕል፡106]

ክሕደት እንዲፈጽም የተገደደና ከዚያ በኋላ ወዶ የፈጸመው ሰው፣ልቡን ለክሕደት የከፈተ በመሆኑ ከሐዲ (ካፍር) ሆኗል። ከሞት አደጋ ለማዳን ብሎ ውስጡ በኢማኑ እንደጸና የኩፍር ቃል የተናገረ ሰው ግን ይድናል ምንም የለበትም። አላህﷻ እንዲህ ብሏልና ፦

(إِلَّآ أَن تَتَّقُواْ مِنۡهُمۡ تُقَىٰةٗ)

‹‹ከነርሱ መጠበቅን ብትጠበቁ እንጂ፤››

[ኣል ዒምራን፡28]

ዕውቀት (ዕልም) መልካም የሆኑ ስነምግባራትን ሁሉ፣በጎ ሥራዎችን ሁሉ፣ምስጉን ባሕርያትን ሁሉ የሚያፈራ ዛፍ ነው። ማይምነት (ጀህል) ደግሞ እኩይ ስነምግባራትንና ክፉ ባሕርያትን ሁሉ የሚያፈራ ዛፍ ነው።Tags: