በአላህ ላይ ተስፋ ማድረግ (ረጃእ) ፦

በአላህ ላይ ተስፋ ማድረግ (ረጃእ) ፦
ነቢዩﷺ እንዲህ ብለዋል፦ ‹‹ነገሮችን አቅልሉ እንጂ አታካብዱ፣ብስራት ንገሩ እንጂ አታስበርግጉ።›› (በቡኻሪ የተዘገበ)

ተስፋ የማድረግ (የረጃእ) ጽንሰ ሀሳብ ፦

ተስፋ ማድረግ ማለት፦

የአላህን የችሮታውንና የርኅራሄውን መኖር መገንዘብ፣ስሜት ማሳደር፣ችሮታና ጸጋዎቹን በመከጀል መደሰት፣በዚህም መተማመን ማለት ነው። ረጃእ ልቦችን ወደ አላህና ወደ ጀነቱ የሚነዳ ሞተር ነው። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

( وَمَن يَعۡمَلۡ سُوٓءًا أَوۡ يَظۡلِمۡ نَفۡسَهُۥ ثُمَّ يَسۡتَغۡفِرِ ٱللَّهَ يَجِدِ ٱللَّهَ غَفُورٗا رَّحِيمٗا ١١٠)

‹‹መጥፎም የሚሠራ ሰው፣ወይም ነፍሱን የሚበድል፣ከዚያም (ተጸጽቶ) አላህን ምሕረትን የሚለምን፣አላህን መሓሪ አዛኝ ኾኖ ያገኘዋል።››

[አልኒሳእ፡110]

የረጃእ ዓይነቶች ፦

ተስፋ ማድረግ (ረጃእ) ሦስት ዓይነት ነው። ሁለቱ ዓይነት የተመሰገኑ ሲሆኑ አንደኛው ዓይነት ግን የተወገዘ መዘናጋትና ራስን መሸንገል ነው።

1-

የአላህን ትእዛዝ በአላህ ብርሃን ተመርቶ በመፈጸም ምንዳውን ተስፋ የሚያደርግ ሰው ረጃእ።

2-

ኃጢአት ሰርቶ በመጸጸት የተመለሰና የአላህን ምሕረት፣ይቅርታውንና የኃጢአቱን መታበስና ከውርደት መዳንን ተስፋ የሚያደርግ ሰው ረጃእ።

3-

የአላህን ትእዛዝ በመጣስ፣በኃጢአት ሥራ፣በእኩይ ተግባራት ላይ መሰማራቱን እየቀጠለ፣የአላህን እዝነትና ምሕረቱን ያለ በጎ ሥራ ተስፋ የሚያደርግ ሰው!! ይህ ራስን መሸንገል፣ከንቱ ተስፋና ባዶ ምኞት ሲሆን፣ፈጽሞ የሚወደስ ተስፋ ሊሆን አይችልም። የምእመናን ተስፋ (ረጃእ) ከተግባር ጋር የተቆራኘ ተስፋ ነው። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(إِنَّ ٱلَّذِينَ ءَامَنُواْ وَٱلَّذِينَ هَاجَرُواْ وَجَٰهَدُواْ فِي سَبِيلِ ٱللَّهِ أُوْلَٰٓئِكَ يَرۡجُونَ رَحۡمَتَ ٱللَّهِۚ وَٱللَّهُ غَفُورٞ رَّحِيمٞ ٢١٨)

‹‹እነዚያ ያመኑትና እነዚያም (ከአገራቸው) የተሰደዱት፣በአላህም መንገድ ላይ የተጋደሉት፣እነዚያ የአላህን እዝነት ይከጅላሉ፤አላህም እጅግ መሓሪ አዛኝ ነው።››

[አልበቀራህ፡218]

እርከኖቹና ደረጃዎቹ ፦

ተስፋ ማድረግ (ረጃእ) ደረጃና እርከኖች ያሉት ሲሆን፣እነሱም የሚከተሉት ናቸው ፦

1-

ለዕባዳና ለጥረት የሚገፋፋ፣ከባድና አስቸጋሪ ቢሆን እንኳ ዕባዳውን ሲያከናውን ባለቤቱ ዘንድ ደሰታና እርካታን በመፍጠር ከኃጢኣቶችና ከእኩይ ነገሮች እንዲርቅ የሚያደርግ ተስፋ።

2-

የነፍስያቸውን ልማዶችና ከፈጣሪያቸው ፍላጎት የሚያዘናጋቸውን ፍላጎቶች ሁሉ በመተውና ልቦቻቸውን ለርሱ አንድ ወጥ በማድረግ ረገድ ትጉሃን አገልጋዮች የሚያሳድሩት ተስፋ (ረጃእ)።

3-

የልቦና ባለቤቶች ተስፋ (ረጃእ) ፦ ይህ ከፈጣሪ አምላክ ጋር መገናኘትን በመናፈቅ፣ልቦናን ለርሱ ብቻ ፍጹም በማድረግ በርሱ ፍቅር የመመሰጥ ተስፋ (ረጃእ) ነው። ይህ ከተስፋ ማደረግ ዓይነቶች ሁሉ በላጩና ከፍተኛው ነው። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(فَمَنْ كَانَ يَرْجُوا لِقَاءَ رَبِّهِ فَلْيَعْمَلْ عَمَلًا صَالِحًا وَلَا يُشْرِكْ بِعِبَادَةِ رَبِّهِ أَحَدًا)

‹‹የጌታውንም መገናኘት የሚፈልግ ሰው፣መልካም ሥራን ይሥራ፤በጌታውም መገዛት አንድንም አያጋራ፣በላቸው።››

[አልከህፍ፡110]

በተጨማሪም አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(مَنْ كَانَ يَرْجُو لِقَاءَ اللَّهِ فَإِنَّ أَجَلَ اللَّهِ لَآَتٍ وَهُوَ السَّمِيعُ الْعَلِيمُ)

‹‹የጌታውንም መገናኘት ተስፋ የሚያደርግ ሰው፣(ይዘጋጅ) የአላህ ቀጠሮ በእርግጥ መጪ ነውና፤እርሱም ሰሚው፣ዐዋቂው ነው።››

[አልዐንከቡት፡5]

አንድን ነገር ለማግኘት ተስፋ የሚያደርግ ሰው አጥብቆ ይፈልገዋል።

ረጃእ አላህንﷻ ፣ስሞቹንና ባሕርያቱን ከማወቅ ጋር ያለው ትስስር ፦

ተስፋ አድራጊ ሙእምን የአላህን ትእዛዛት በፈጸም ላይ የሚተጋ፣የኢማን ግዴታዎችን የሚያከናውን፣አላህﷻ እንዳያጠመው፣ሥራውን ከርሱ እንዲቀበልና ውድቅ እንዳያደርግበት ተስፋ የሚያደርግ፣ምንዳና አጅሩን እጥፍ ድርብ እንዲያደርግለት ተስፋና ምኞቱን በርሱ ላይ የሚጥል ሰው ነው። አላህን፣ስሞቹንና ባሕርያቱን ለማወቅ በጌታው እዝነት ላይ ተስፋ የሚጥል፣ ማድረግ የሚችላቸውን ነገሮች ሁሉ ያደረገ፣የሚገበያየው በጣም አዛኝ፣በጣም አፍቃሪ፣በጣም አመስጋኝ፣ቸር፣ለጋሽ፣መሓሪ፣ርኅሩህ ከሆነ ጌታ ጋር ነው። በዚህች ዓለም ላይ ስጉ ሲሆን ነገ ወደ ጌታው ፊት ሲቀርብ መድህን ለማግኘት ተስፋ ያደርጋል።

የተስፋ ማድረግ (የረጃእ) ፍሬዎች ፦

1-

በበጎ ሥራዎችና በአላህ ትእዛዛት ትግባራ (ጧዓት) ላይ የባለቤቱን ጥረትና ትጋት ያጎለብታል።

2-

ሁኔታዎች የፈለገውን ያህል ቢለዋወጡና አስቸጋሪ ቢሆኑም፣ባለቤቱ የአላህ ትእዛዛት ትግባራን (ጧዓትን) ልማዱ አድርጎ እንዲያዘወትር ያላምደዋል።

3-

ባለቤቱ ፊቱን ዘውትር ወደ አላህ በመመለስ እርሱን በመማጸን፣በመለማመን፣በጸሎቱና በጥሪው ላይ መትጋትን ልማዱ አድርጎ እንዲይዝ ያደርጋል።

4-

ባሪያው ለአላህﷻ ያለውን ተገዥነት፣ድህነቱን፣ፈላጊነቱን፣ከርሱ ችሮታና ከቸርነቱ ለአንዲት ሰከንድ እንኳ መብቃቃት የማይችል መሆኑን ያመለክታል።

5-

ለአላህﷻ መኖር፣ለቸርነቱና ለትሩፋቱ ዕውቀትና እርግጠኝነትን ያስጨብጣል። እርሱﷻ ከሚለመኑት ሁሉ ይበልጥ ቸር፣ከሰጭዎች ሁሉ ይበልጥ አስፍቶ የሚሰጥ፣መልሰው መላልሰው የሚለምኑትንና በርሱ ላይ ተስፋ የጣሉትን ባሮቹን የሚወድ ጌታ ነው።

6-

ተስፋ ማድረግ (ረጃእ) ባሪያውን በአላህ ፍቅር ደጃፍ ላይ እንዲወድቅ በማድረግ ወደ ተሟላ አፍቃሪነት ደረጃ ያደርሰዋል። ተስፋ በጠነከረና ተስፋ ያደረገውን ነገር ባገኘ ቁጥር፣ለጌታው ያለው ፍቅርና አመስጋኝነቱ እየበረታ ይሄዳል። ይህ ከተገዥነት (ዑቡዲይያህ) ግዴታዎችና ከማእዘናቱ አንዱ ነው።

ተስፋ አድራጊው ዘውትር የጌታውን ችሮታ በመከጀል በተስፋና በስጋት ውስጥ ሆኖ ከጌታው በጎውን ይመኛል፣ደግ ደጉን ይጠቃል።

ሙእምን ሰው በጌታው ላይ በጎ ግምት ያሳድርና በጎ በጎውን ይሠራል። አመጸኛ ሰው ግን በጌታው ላይ ክፉ ግምት ያሳድራና ክፉ ክፉውን ይሠራል።

በአላህ ላይ በጎ ግምት ከማሳደር (ሑስን አዝዟን) አንዱ አላህﷻ ወደርሱ የተጠጋውንና በርሱ የተከለለውን ሰው የማይጥለው መሆኑን ማወቅ ነው።

7-

ተስፋ መቋጠር የአላህንﷻ ጸጋዎች በተግባር ወደ ማመስገን ደረጃ እንዲራመድ ስለሚገፋፋው፣ወደ አመስጋኝነት ደረጃ እንዲደርስ ባሪያውን ያበረታታል። ይህ የተገዥነት (የዑቡዲይያህ) ንጥርና አስኳል ነው።

8-

ረጃእ የአላህንﷻ ስሞችና ባሕርያት (አልአስማእ ወስስፋት) ያስተዋውቃል። እርሱ በጣም አዛኙ፣ቸሩ፣ለጋሱ፣ጸሎት ተቀባዩ፣ውቡና ሀብታሙ ጌታﷻ ነው። ምንኛ ኃያል ጌታ!

9-

ረጃእ ባሪያው ተስፋ ያደረገውን ነገር እንዲያገኝ ምክንያት ይሆናል። የተመኙትን ማግኘት ተጨማሪ ለመጠየቅና ለማግኘት ፊቱን ወደ አላህ እንዲመለስ ያደፋፍረዋል። በዚህ መልኩ ኢማኑና ወደ አላህ ያለው ቀረቤታ እየጨመረ መሄዱን ይቀጥላል።

10-

ምእመናን በትንሣኤ ቀን የተመኙትን የአላህ ውዴታ (ሪዷ) ጀነቱንና ወደርሱ ፊት መመልከትን ታድለው የሚደሰቱት፣በዱንያ ዓለም ሕይወታቸው በአላህﷻ ላይ በጣሉት ተስፋ (ረጃእ) እና ለርሱ ባላቸው ፍራቻ ልክ ነው።

ረጃእን የሚመለከቱ ብያኔዎችና ማሳሰቢያዎች ፦

1-

በሙእምኑ ዘንድ ፍራቻ (ኸውፍ) ከተስፋ ማድረግ (ከረጃእ) ጋር የተጎዳኘ ነው። ለዚህ ነው የፍራቻ መኖር መልካም በሆነበት ሁሉ ተስፋ ማድረግ (ረጃእ) መኖሩ መልካም የሆነው ፦

(مَّا لَكُمۡ لَا تَرۡجُونَ لِلَّهِ وَقَارٗا ١٣ )

‹‹ለአላህ ልቅናን የማትሹት ለናንተ ምን አላችሁ።››

[ኑሕ፡13]

በተጨማሪም አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(قُل لِّلَّذِينَ ءَامَنُواْ يَغۡفِرُواْ لِلَّذِينَ لَا يَرۡجُونَ أَيَّامَ ٱللَّهِ)

‹‹ለነዚያ ለአመኑት ሰዎች (ምሕረት አድርጉ)፣በላቸው፤ለነዚያ የአላህን ቀኖች ለማይፈሩት ይምራሉና፣››

[አልጃሢያ፡14]

ከነሱ በፊት በነበሩት ሕዝቦች ላይ የደረሰውን ዓይነት ጥፋትና ውድመት አላህ ያደርስብናል ብለው አይፈሩም ማለት ነው።

2-

ተስፋ ማድረግ (ረጃእ) በሚከተሉት ሁኔታዎች የምንፈልገው መድኃኒት ነው ፦

- ነፍስያ ቀቢጠ ተስፋ መሆን አይሎባት ዕባዳ በምትተውበት ጊዜ።

- ፍርሃቱ ከተፈላጊው ሸሪዓዊ ገደብ አልፎ፣አንድ ሰው ራሱንና ቤተሰቡን ለአደጋ እስከማጋለጥ ድረስ በፍርሃት ቁጥጥር ስር ሲሆን። በዚህ ጊዜ ሁኔታውን መለወጥና ሚዛን የሚያስጠብቅ ነገር እንዲሰነቅ ማድረግ ግድ ይላል። ያም በሙእምኑ ዘንድ የተለመደው ተፈጥሯዊ ሁኔታ የሆነውን ተስፋ (ረጃእ) መሰነቅ ነው።

3-

ተስፋ ማድረግ (ረጃእ) የቀቢጠ ተስፋ ተቃራኒ ነው። ተስፋ መቁረጥ የአላህ እዝነት ማምለጡን ማስታወስ፣ርኅራሄውን ከመሻት መቋረጥ ሲሆን፣ይህን ማድረግ የኩፍርና የጥመት መንስኤ ነው። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(وَلَا تَاْيۡئسُواْ مِن رَّوۡحِ ٱللَّهِۖ إِنَّهُۥ لَا يَاْيۡئسُ مِن رَّوۡحِ ٱللَّهِ إِلَّا ٱلۡقَوۡمُ ٱلۡكَٰفِرُونَ ٨٧)

‹‹ከአላህም እዝነት ተስፋ አትቁረጡ፤እነሆ ከአላህ እዝነት ከሐዲዎች ሕዝቦች እንጂ ተስፋ አይቆርጥም (አለ)።››

[ዩሱፍ፡87]

ሚዛን ቀርቦ የአንድ ሙእምን ተስፋና ፍርሃቱ ቢመዘን ሁለቱ እኩልና ተመጣጣኝ ይሆኑ ነበር።

የእኔ ምርመራ በወላጅ አባቴ እጅ እንዲሆን አልሻም፤ጌታዬ ከአባቴ ይሻለኛልና።

ኢማም ሱፍያን አሥሠውሪ

ዕባዳ በፍርሃትና በተስፋ (ረጃእ) ማድረግ እንጂ ሊከናወን አይችልም። አማኙ በፍርሃት ከተከለከሉ ነገሮች ይታቀባል፤በተስፋ ደግሞ የትእዛዛትን ትግበራዎች (ጧዓት) ያበዛል።

ኢማም እብን ከሢር



Tags: