አንደኛ - በግለሰብ ላይ በተለይ የሚስተዋሉ ፦

አንደኛ - በግለሰብ ላይ በተለይ የሚስተዋሉ ፦

ጦሃራ (ንጽሕና) ፦

ለአንድ ሙእምን ጥራትና ንጽሕናን ከሚያስገኙት ሁሉ ትልቁና ዋነኛው ተውሒድ ነው። ለዚህ ነው አላህ የወደደው። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(إِنَّ ٱللَّهَ يُحِبُّ ٱلتَّوَّٰبِينَ وَيُحِبُّ ٱلۡمُتَطَهِّرِينَ٢٢٢)

‹‹አላህ (ከኃጢአት) ተመላሾችን ይወዳል፤ተጥራሪዎችንም ይወዳል፣››

[አልበቀራህ፡222]

ነቢዩﷺ እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹መጥራትና ንጽሕና የኢማን ግማሽ ክፍል ነው።››

(በሙስሊም የተዘገበ)

ጦሃራ የኢማን ግማሽ ክፍል የሆነው ከዋነኛ ዓይነቶቹ አንዱ በመሆኑ ነው። አላህﷻ ንጽሕናንን በሁሉም ዓይነቶቹ ይወዳል። ዓይነቶቹም ፦

1-

ሕሊናዊ ንጽሕና ፦

ይህ ልቦናንና ነፍስያን ከኃጢአቶች፣ ከአላህ ትእዛዛት ጥሰቶችና በአላህ ከማጋራት ቅሪቶች ማጥራትና ማጽዳት ነው። ይህም በእውነተኛ ተውበት፣ልብን ከሽርክና ከጥርጣሬ፣ከምቀኝነት፣ከክፋት፣ከእምነት ማጉደልና ከኩራት ቆሻሻዎች በማጽዳት የሚፈጸም ነው። የማጽዳቱ ተግባር ለአላህ ልቦናን ፍጹም በማድረግ፣በጎ በጎውን በመውደድ፣በትዕግስት፣በመተናነስ፣በትህትና፣በእውነተኛነትና የአላህﷻ ፊት በማሰብ ብቻ እንጂ እውን መሆን አይችልም።

2-

ቁሳዊ ንጽሕና ፦

ይህ ደግሞ ርክሰትንና ሐደሥን ማስወገድ ነው።

- ርክሰትን ማስወገድ ፦

ልብስን ገላና ቦታንና በዚህ ስር የሚጠቃለሉትን በንጹህ ውሃ ከቆሻሻና ከነጃሳዎች ማጥዳት ነው።

- ሐደሥን ማስወገድ ፦

ሐደሥ (በገላ ላይ ተከስቶ ጦሃራ ቅድመ ሁኔታ የተደረገባቸውን እንደ ሶላትና ጠዋፍ የመሳሰሉ ዕባዳዎችን ማከናውን የሚያግድ ክስተት) ማስወገድ ማለት ለሶላት፣ቁርኣን ለመቅራት፣ለጠዋፍ፣ለአላህ ውዳሴና ለመሳሰሉት ገላን መታጠብ፣ውዱእማና ተየሙም ማድረግ ነው፡፡

ነቢዩﷺ እንዲህ ብለዋል፦ ‹‹መጥራትና ንጽሕና የኢማን ግማሽ ክፍል ነው›› (በሙስሊም የተዘገበ)

ሶላት ፦

ባሪያውን ከጌታው ጋር የሚያስተሳስር፣አገልጋዩ ለጌታው ያለውን ታዛዥነት፣ፍቅር፣ተገዥነትና መተናነስ የሚገልጽበት ግንኙነት የሆነው ሶላት፣የአላህን ተውሒድ ያንጸባርቃል። ለዚህም ነው ከሁለቱ ሸሃዳ ቀጥሎ ታላቁ የእስላም ማእዘን፣የሃይማኖት ዐምድና የእርግጠኝነት ብርሃን የሆነው። በሶላት መንፈስ ይረካል፤ልቦና ይጠራል፤ልብ ይረጋጋል። ሶላት ከመጥፎ ሥራዎች የሚከለክል ሲሆን፣ለኃጠአቶችም መታበስ ምክንያት ነው። ሶላት ተለይተው በተቀመጠ አፈጻጸም በተወሰነ ወቅት የሚከናወን ሲሆን፣በተክቢር (አል'ሏሁ አክበር) ተጀምሮ በተስሊም (አስ'ሰላሙ ዐለይኩም) የሚያበቃ ዕባዳ ነው፡፡

ሶላትን የተወና ግዴታነቱን የካደ ሰው አላህንና መልክተኛውን የካደ፣ቁርኣንን ያስተባበለ ሰው ነው። ይህ ደግሞ ከኢማን መሠረት ጋር የሚጻረር ነው። ግዴታነቱን የሚያውቅና በስንፍና የሚተወው ሰው ግን ራሱን ለከባድ ማስጠንቀቂያና ለብርቱ አደጋ አጋልጧል። ነቢዩﷺ እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹በአንድ ሰውና በማጋራትና በክህደት (በሽርክና በኩፍር) መካከል ያለው መለያ ሶላትን መተው ነው፡፡››

(በሙስሊም የተዘገበ)

ሌሎች ደግሞ እንዲህ ብለዋል፦ ሶላትን መተው ኩፍር ነው፤ሆኖም ከሃይማኖት የሚያስወጣ ከባዱ ኩፍር አይደለም። ለሁሉም ግን ወይ ከሃይማኖቱ ጎራ የሚያስወጣ ኩፍር ነው፣ወይም ከከባዳ ኃጢአቶችና ከአደገኛ ጥፋቶች አንዱ ነው።

ሶላት በአማኙ ላይ ታላላቅ አሻራዎችን የሚያሳርፍ ሲሆን፣አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው ፦

ነቢዩﷺ እንዲህ ብለዋል ፦ ‹‹ሶላት ብርሃን ነው፡፡›› (በበይሀቂ የተዘገበ)

1-

ከመጥፎና ከሚጠላ ነገር ይከለክላል። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(ٱتۡلُ مَآ أُوحِيَ إِلَيۡكَ مِنَ ٱلۡكِتَٰبِ وَأَقِمِ ٱلصَّلَوٰةَۖ إِنَّ ٱلصَّلَوٰةَ تَنۡهَىٰ عَنِ ٱلۡفَحۡشَآءِ وَٱلۡمُنكَرِۗ وَلَذِكۡرُ ٱللَّهِ أَكۡبَرُۗ وَٱللَّهُ يَعۡلَمُ مَا تَصۡنَعُونَ٤٥)

‹‹ከመጽሐፉ ወደ አንተ የተወረደውን አንብብ፤ሶላትንም ደንቡን ጠብቀህ ስገድ፤ሶላት ከመጥፎና ከሚጠላ ነገር ሁሉ ትከለክላለችና፤አላህንም ማውሳት ከሁሉ ነገር በላጭ ነው፤አላህም የምትሠሩትን ሁሉ ያውቃል።››

[አልዐንከቡት፡45]

2-

ከሁለቱ ሸሃዳዎች በኋላ ከሥራዎች ሁሉ በላጩ ነው። ይህም እብን መስዑድ  ባስተላለፉት ቀጣዩ ሐዲሥ መሰረት ነው ፦

የአላህን መልክተኛ ﷺ ከሥራ በላጩ የቱ ነው? ብዬ ጠየቅኋቸውና ፦ ‹‹ሶላትን በወቅቱ መስገድ ነው›› አሉ። ከዚያስ? አልኳቸው።‹‹ለወላጆች ደግ መሆን ነው›› አሉ። ከዚያስ? አልኳቸው። ‹‹በአላህ መንገድ መታገል (ጅሃድ) ነው›› አሉ።

(በሙስሊም የተዘገበ)

አንድን የአላህ አገልጋይ ወደ ጌታው ከሚያቀርቡት ነገሮች መካከል ሶላት በላጩ ነው።

3-

ሶላት ኃጢአትን ያጥባል። ይህም ጃብር ብን ዐብዱላህ  ባስተላለፉት ሐዲሥ መሰረት ሲሆን፣የአላህ መልክተኛ ﷺ እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹የአምስቱ ወቅት ሶላቶች ምሳሌ፣ሰውየው በየቀኑ አምስት ጊዜ ገላውን እንደሚታጠብበት፣በአንዳችሁ ደጃፍ ላይ እንደሚፈስ ትልቅ ወንዝ ነው።››

(በሙስሊም የተዘገበ)

4-

ሶላት ለሰጋጁ በዱንያም ሆነ በኣኽራ ብርሃን ነው። ነቢዩﷺ ሶላትን አስመልክተው እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹አዘውትሮ ተጠባብቆ የሰገደ ሰው፣በትንሣኤ ቀን ብርሃን አስረጅና መድህን ይሆነዋል። አዘውትሮ ተጠባብቆ ያልሰገደው ሰው ግን፣ብርሃን አስረጅም ሆነ መድህን አይኖረውም። በትንሣኤ ቀን ከቃሩን፣ከፈርዖን፣ከሃማንና ከኡበይ ብን ኸለፍ ጋር ይሆናል።››

(በአሕመድ የተዘገበ)

በተጨማሪም ነቢዩﷺ እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹ሶላት ብርሃን ነው፡፡››

(በበይሀቂ የተዘገበ)

5-

አላህﷻ በሶላት ደረጃዎችን ከፍ ያደርግበታል። ኃጢአቶችን ያራግፋል። ይህም ከሠውባን በተላለፈው ሐዲሥ መሰረት ሲሆን፣ነቢዩﷺ እንዲህ ብለዋቸዋል ፦

‹‹ሱጁድ አብዛ አዘውትር፤አላህ አንድ ደረጃ ከፍ የሚያደርግህ፣በርሱ አንድ ኃጢአት ከአንተ የሚያራግፍ ቢሆን እንጂ አንድ ሱጁድ አታደርግምና።››

(በሙስሊም የተዘገበ)

6-

ሶላት ከነቢዩ ﷺ ጋር ወደ ጀነት ከሚያስገቡ አበይት ምክንያቶች አንዱ ነው። ከረቢዓ ብን ከዕብ አልአስለሚ  የሚከተለው ሐዲሥ ተላልፏል ፦

ከአላህ መልክተኛ ﷺ ዘንድ አድር ነበር፤ ውዱእ ማድረጊያ ውሃና የሚፈልጉትን አቀረብኩላቸውና ፦ ‹‹የምትፈልገውን ጠይቅ›› አሉኝ። ጀነት ውስጥ ከርስዎ ጋር መሆንን እጠይቃለሁ፣አልኳቸው። ከርሱ ሌላስ? አሉኝ። እርሱውኑ ነው፣አልኳቸው። ‹‹እንግዲያውስ ሱጁድን በማብዛት በራስህ ላይ አግዘኝ፡›› አሉ።

(በሙስሊም የተዘገበ)

ሶላት በኃያሉ አላህ ﷻ እና በደካማው ባሪያ መካከል የሚገኝ፣ደካማውን በኃያሉ ጌታ ኃይል የሚያጠነክር፣የርሱን ውዳሴ የሚያበዛ፣ልብን ከርሱ ጋር የሚያስተሳስር፣የመገናኛ መስመር ነው። የሶላት ዋነኛ ዓለማዎችም እነዚሁ ናቸው። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(وَأَقِمِ ٱلصَّلَوٰةَ لِذِكۡرِيٓ ١٤)

‹‹ሶላትንም (በርሷ) እኔን ለማውሳት ስገድ።››

[ጣሃ፡14]

ዘካ ፦

ዘካ ነፍስን ገንዘብንና ሕብረተሰቡን የሚያጠራና የሚያጎለብት ማጽጃ ነው።

ቃሉ መጥራትና መፋፋትን የሚያመለክት ሲሆን፣የአላህን ተውሒድ የሚያረጋግጥ አገልጋይ ነፍስ ስትጠራና ልቦናው ሲጸዳ ሀብትና ንብረቱን የዘካ ግዴታን ለሚገባቸው በመክፈል እንዲያጸዳና እንዲያጠራ ያደርገዋል። ዘካ ድሆችና አጦች በሀብታሞች ሀብት ውስጥ ያላቸው የግዴታ ድርሻ ሲሆን፣የአላህን ውዴታ የሚያስገኝና ነፍስን የሚያጠራ ለችግረኞች የሚከፈል በጎ አድራጎት ነው።

ዘካ እስላም ውስጥ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠውና ትልቅ ቦታ የሚይዝ እስላማዊ ግዴታ ነው። ከድንጋጌው በስተጀርባ ያለው ጥበብም አስፈላጊነቱን በጉልህ የሚያመለክት ነው። ጥበቡንና ፍልስፍናውን አስተውሎ ያስተነተነ ሰው የዚህን ታላቅ ማእዘን አስፈላጊነትና ፋይዳውን በቀላሉ ይገነዘባል። ከፋይዳዎቹ መካከል የሚከተሉትን እናገኛለን ፦

1 - የሰውን ነፍስ ከንፉግነት፣ከራስ ወዳድነት፣ከስግብግብነትና ከአገብስባሽሽነት ቆሻሻ ማጥራት።

2 - ድሆችን አጦችንና ችግረኞችን ማገዝ፣ችግራቸውን ማስወገድና መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ማሟላት።

3 - የሕብረተሰቡና የሕዝቡ መልካም ኑሮና የተረጋጋ ሕይወት የሚመሰረትባቸውን የጋራ ጥቅሞች እውን ማድረግ።

4 - ገንዘብ በጥቂት ባለ ሀብቶችና ነጋዴዎች ወይም በተወሰኑ መደቦች እጅ ብቻ ተይዞ እንዳይደልብና ፍትሐዊ የሀብት ስርጭትና ክፍፍል እንዲኖር ማድረግ።

5 - እስላማዊውን ሕብረተሰብ እንደ አንድ ቤተሰብ በማድረግ፣ሀብታሙ ለደሃው፣አቅም ያለው አቅም ለሌለው ወገኑ እንዲያስብና የጋራ ተራድኦ እንዲኖር ሁኔታዎችን ያመቻቻል።

6 - ዘካ አላህ ለሀብታሞች በዘረጋው ጸጋ ምክንያት ድሆች በነሱ ላይ ላይ የሚቋጥሩትን የንዴትና፣የቁጭትና የቅናት ስሜት ከልባቸው ያጸዳል።

7 - ዘካ እንደ ስርቆት ንጥቅያና ዝርፊያ ያሉ ገንዘብ ነክ ወንጀሎችን ይከላከላል።

8 - ሀብትና ነብረትን ያፋፋል፣ይጨምራል።

ዘካ ግዴታ መሆኑን የሚደነግጉ ግልጽ የሆኑ አያሌ ማስረጃዎች በክታብና በሱንና ውስጥ ቀርበዋል። እስላም ከተመሰረተባቸው ጽኑ መሰረቶች አንዱ መሆኑን ነቢዩ ﷺ አብራርተዋል። ለዚህም ነው የዚህ ሃይማኖት ሦስተኛው ማእዘን የሆነው። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(وَأَقِيمُواْ ٱلصَّلَوٰةَ وَءَاتُواْ ٱلزَّكَوٰةَ وَٱرۡكَعُواْ مَعَ ٱلرَّٰكِعِينَ٤٣)

‹‹ሶላትንም ደንቡን ጠብቃችሁ ስገዱ፤ዘካንም (ግዴታ ምጽዋትን) ስጡ፤(ለጌታችሁ) ከአጎንባሾች ጋርም አጎንብሱ።››

[አልበቀራህ፡43]

በተጨማሪም አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(وَأَقِيمُواْ ٱلصَّلَوٰةَ وَءَاتُواْ ٱلزَّكَوٰةَۚ وَمَا تُقَدِّمُواْ لِأَنفُسِكُم مِّنۡ خَيۡرٖ تَجِدُوهُ عِندَ ٱللَّهِۗ إِنَّ ٱللَّهَ بِمَا تَعۡمَلُونَ بَصِيرٞ١١٠)

‹‹ሶላትንም ደንቡን ጠብቃችሁ ስገዱ፤ዘካንም ስጡ፤ለነፍሶቻችሁም፣ከበጎ ሥራ የምታስቀድሙትን አላህ ዘንድ ታገኙታላችሁ፤አላህ የምትሠሩትን ሁሉ ተመልካች ነውና።››

[አልበቀራህ፡110]

በታዋቂው የጀብሪል ሐዲሥም በግልጽ ተቀምጧል ፦

‹‹እስላም ከአላህ በስተቀር ሌላ አምላክ አለመኖሩንና ሙሐመድ የርሱ መልእክተኛ መሆናቸውን መመስከር፣ሶላትን ደንቡን ጠብቆ መስገድ፣ዘካን መስጠት፣ረመዳንን መጾምና አቅም ካለህ የሐጅ ሥርዓተ ጸሎት መፈጸም ነው፡፡››

(በሙስሊም የተዘገበ)

ነቢዩﷺ እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹እስላም በአምስት (ማእዘኖች) ላይ ነው የተመሰረተው፡፡ (እነሱም) ፡- ከአላህ በስተቀር ሌላ አምላክ አለመኖሩንና ሙሐመድ የርሱ አገልጋይና መልእክተኛው መሆናቸውን መመስከር፣ሶላትን ደንቡን ጠብቆ አዘውትሮ መስገድ፣ዘካን መስጠት፣የሐጅ ሥርዓተ ጸሎት መፈጸምና ረመዷንን መጾም ናቸው፡፡››

(በቡኻሪ የተዘገበ)

እነዚህና የመሳሰሉት ጥቅሶች ዘካ የእስላም አንዱ ማእዘንና ሃይማኖቱ ከታነጸባቸው ታላላቅ መሠረቶችም አንዱ መሆኑን በግልጽ ያስረዳሉ።

ጾም ፦

አላህ ﷻ የጾምን ግዴታ ደንግጎ፣የእስላም አንዱ ማእዘን አድርጎታል። ጾም አላህን ለመገዛት ዓለማ ከጎሕ መቅደድ እስከ ጸሐይ መጥለቅ ድረስ ጾምን ከሚያፈርሱ ነገሮች ታቅቦ መዋል ነው። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(وَكُلُواْ وَٱشۡرَبُواْ حَتَّىٰ يَتَبَيَّنَ لَكُمُ ٱلۡخَيۡطُ ٱلۡأَبۡيَضُ مِنَ ٱلۡخَيۡطِ ٱلۡأَسۡوَدِ مِنَ ٱلۡفَجۡرِۖ ثُمَّ أَتِمُّواْ ٱلصِّيَامَ إِلَى ٱلَّيۡلِ)

‹‹ከጎህ የኾነው ነጩ ክርም ከጥቁሩ ክር (ከሌሊት ጨለማ) ለናንተ እስከሚገለጽላችሁ ድረስ ብሉ፤ጠጡም፤ከዚያም ጾምን እስከ ሌሊቱ ድረስ ሙሉ፤››

[አልበቀራህ፡187]

በአላህ አገልጋይ ልብ ውስጥ ኢማንና የአላህ ተውሒድ ስር ሰደው ሲጸኑ፣አላህ ግዴታ ያደረገበትን ሁሉ ለመተግበር አነሳሽ ምክንያት ይሆኑታል። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آَمَنُوا كُتِبَ عَلَيْكُمُ الصِّيَامُ كَمَا كُتِبَ عَلَى الَّذِينَ مِنْ قَبْلِكُمْ لَعَلَّكُمْ تَتَّقُونَ)

‹‹እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ጾም በነዚያ ከናንተ በፊት በነበሩት (ሕዝቦች) ላይ እንደ ተጻፈ፣በናንተም ላይ ተጻፈ (ተደነባ)፣ልትጠነቀቁ ይከጀላልና፡፡››

[አልበቀራህ፡183]

አማኝ ሰው በጾም ይደሰታል፤ለመጾምም ይጓጓል። ይህን አስመልክቶ አላህ ﷻ ሐዲሥ አልቁድሲ ውስጥ እንዲህ ብሏል ፦

‹‹የኣደም ልጅ ሥራ ሁሉ ለራሱ ነው፤ከጾም በስተቀር፣እርሱ ለእኔ ነውና እኔ ነኝ ምንዳውን የምሰጠው . . ››

(በቡኻሪ የተዘገበ)

ጾም በአማኙ አገልጋይ ላይ የሚኖረው አሻራ ብዙ ሲሆን፣ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው ፦

ጾም የኢማን ግንባታና የእነጻው ትምህርት ቤት ነው።

1 - ጾም በባሪያውና በፈጣሪ መካከል የሚገኝና በሙእምኑ ሕሊና ውስጥ በሚገኝ የአላህን ተቆጣጣሪነት የመገንዘብ እውነተኛ ስሜት የሚገለጽ ምስጢር ነው። ጾም በጾመኛውና በአላህ መካከል ብቻ የተወሰነ ዕባዳ በሆኑ ለታይታና ለጉራ የተጋለጠ አይደለም። የአላህን ተጠባባቂነትና ተቆጣጣሪነት የመገንዘብ ስሜትን በአማኙ ውስጥ የሚያንጽ ሲሆን፣ይህም ብዙዎች የሚጓጉለት ታላቅ ግብና ክቡር የሆነ ዓለማ ነው።

2 - ሕዝቡን (ኡማውን) ሥርዓትና አንድነትን፣ፍቅር፣ፍትሕና እኩልነትን ልማዱ እንዲያደርግ ያሰለጥናል። በምእመናን ልቦና ውስጥ የመተሳሰብ የመተዛዘንና የደግነት ባሕርያት የሚያንጽ ሲሆን፣ሕብረተሰቡንም ከእኩይና ጎጂ ነገሮች ይጠብቃል።

3 - ሙስሊሙን የወንድሞቹ ችግር እንዲሰማውና ለድሆችና ለችግረኞች እንዲለግስ ያነሳሳዋል። በዚህም በሙስሊሞች መካከል ፍቅርና ወንድማማችነት ይረጋገጣል።

4 - የገዛ ራስን መቆጣጠር፣ኃላፊነትን መሸከምና አስቸጋሪ ሁኔታዎችን መወጣት የሚያስችል ተግባራዊ ስልጠና ነው።

5 - ለጾመኛው ኃጢአት ላይ እንዳይወድቅ መከላከያ ይሆነዋል። አያሌ ሰናይ ነገሮችን እንዲያገኝ ያደርገዋል። ነቢዩﷺ እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹ጾም (ከእሳት የሚከላከል) ጋሻ ነው። መጥፎና አልባሌ አይናገር፤ጅል አይናገር አይሥራ፤ሌላ ሰው ቢጣላው ወይም ቢዘልፈው፣ሁለት ጊዜ እኔ ጾመኛ ነኝ ይበልም፡፡ ነፍሴ በእጁ በሆነችው (አላህ) እምላለሁ፣የጾመኛው የአፍ ጠረን ለውጥ አላህ ዘንድ ከሚስክ ሽቶ የበለጠ መዓዝ አለው፡፡ ምግቡንና መጠጡን፣ሥጋዊ ፍላጎቱንም ለእኔ ብሎ ነው የሚተወው፡፡ ጾም ለእኔ ነውና እኔ ነኝ ምንዳውን የምሰጠው፤አንድ ሐሰና (መልካም ሥራ ምንዳው) አስር እጥፍ ነው፡፡››

(በቡኻሪ የተዘገበ)

ሐጅ ፦

የአላህ ተውሒድ በሐጅ ሥርዓተ ጸሎት ውስጥ ይንጸባረቃል። ሐጅ አንድ የአላህ አገልጋይ ተውሒድን ከሚጨምርባቸውና በኢማን ሙላት ከሚዋብባቸው ዕባዳዎች አንዱ ነው። ሐጅ ላይ ሐጅ አድራጊው ገና ሥርዓተ ዕባዳውን ‹‹ለብበይከ አልሏሁምመ ለብበይከ፣ላ ሸሪከ ለከ ለብበይከ›› ብሎ ሲጀምር ተውሒድን ያውጃል። በሁሉም የሐጅ ክንውኖች ላይም ተውሒድን ያንጸባርቃል። ተውሒድን አውጆና ለተውሒድ ፍጹም ሆኖ ልክ እናቱ እንደወለደችው ቀን ከኃጢአት ንጹሕ ሆኖ ሐጁን ያጠናቅቃል። ሐጅ የተለየ የዕባዳ ክንውን ሲሆን፣ከአላህﷻ በተላለፈውና ረሱልﷺ በፈጸሙት መሰረት ለመፈጸም በተወሰነ ወቅት ወደ መካ የተከበረው መስጊድ መሄድ ነው፡፡ ሐጅ አላህﷻ በባሮቹ ላይ የደነገገው፣በክታብና በሱንና አንቀጾች፣በሙስሊሞች የጋራ አቋም የተረጋገጠ እስላማዊ ግዴታ (ፈርድ) ነው።

ሐጅ በአማኙ ሰው ሕይወት ላይ ከሚኖራቸው አሻራዎች መካከል የሚከተሉት ይገኛሉ ፦

ነቢዩﷺ እንዲህ ብለዋል ፦ ‹‹በከዕባ ዙሪያ መዞር፣በሶፋና መርዋ መካከል መመላለስ፣ጠጠሮችን መወርወር የተደረገው፣የአላህንﷻ ወስዳሴ (ዝክር)ሕያው ለማድረግ ብቻ ነው።›› (በአሕመድ የተዘገበ)

1 - ኃጢአቶችና ጥፋቶች እንዲታበሱ ምክንያት ነው። ነቢዩﷺ እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹እስላም ከርሱ በፊት የነበረውን የሚያፈርስ መሆኑን፣ህጅራም (ስደት) ከርሱ በፊት የነበረውን የሚያፈርስ መሆኑንና ሐጅም ከርሱ በፊት የነበረው የሚያፈርስ መሆኑን አታውቀውም . . ››

(በሙስሊም የተዘገበ)

2 - ሐጅ አድራጊው የአላህንﷻ ትእዛዝ ለመተግበር ብሎ ነው ከቤተሰቡና ከልጆቹ ተለይቶ፣የተሰፉ ልብሶችን አውልቆ በመጓዝ የጌታውን ተውሒድ የሚያውጀው። ይህም የተገዥነትና የታዛዥነት ሁሉ ቁንጮ ነው ።

3 - ሐጅ የአላህን ውዴታ ለማግኘትና ጀነት ለመግባት ምክንያት ነው። ነቢዩﷺ እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹ተቀባይነት ያለው ሐጅ ከጀነት በስተቀር ሌላ ምንዳ የለውም፡፡››

(በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ)

4 - ሐጅ በሰዎች መካከል ለሚኖር የእኩልነትና የፍትሕ መርሕ ተግባራዊ መገለጫ ነው። ይህም ሰዎች በየትኛው የዓለማዊ ሕይወት ጉዳዮች በመካከላቸው አንዳች ልዩነት በማይታይበት ሁኔታ በምድረ ዐረፋ በአንድነት መገኘታቸው ነው። በዚህ ትእይንት ላይ ብቸኛው መበላለጫ ለአላህ ያለቸው ፍራቻ (ተቅዋ) እና የተውሒዳቸው ጥራት ብቻ ነው።

5 - ሐጅ የመተዋወቅና የመረዳዳት መርህ እውን የሚሆንበት ሲሆን፣ከተለያዩ ዓለማት የመጡ የተለያዩ ባህሎችና ቋንቋዎች ባሏቸው ሙስሊሞች መካከል ትውውቅ፣ምክክርና፣የሀሳብ ልውውጥ የሚፈጸምበት አጋጣሚ ነው። ይህ ለኡማው እድገትና ምጥቀት፣ለመሪነት ቦታውም የሚኖረው አስተዋጽኦ እጅግ የላቀ ነው።

6 - ሐጅ ለተውሒድና ለፍጹምነት (እኽላስ) ይጠራል። ይህም በሐጅ አድራጊው ሙሉ ቀሪ ሕይወት ላይ የሚንጸባርቅ ሲሆን፣ሕይወቱን በአላህ ተውሒድና ወደ አላህ ጥሪ በማድረግ ይሞላል።

ሁለተኛ - ከሰዎች ጋር በሚኖረው አጠቃላይ ግንኙነት ላይ የሚኖረው አሻራ ፦

የተውሒድና የኢማን አሻራ በሙእምን ልብና በግላዊ ስነምግባሩ ውስጥ እንደተንጸባረቀው ሁሉ፣ከሰዎች ጋር በሚኖረው ማህበራዊ ግኝኙነት ውስጥም ይንጸባረቃል። ነቢዩﷺ እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹የተላክሁት መልካም ስነምግባራትን ምሉእ ለማድረግ ነው።››

(በበይሀቂ የተዘገበ)

ከዚህም አልፈው ነቢዩﷺ ኢማንና መልካም ስነምግባርን እርስ በርስ የተሳሰሩ አድርጓቸዋል። ነቢዩﷺ እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹ከምእመናን ሁሉ ኢማናቸው ይበልጥ ምሉእ የሆነው ስነምግባራቸው ይበልጥ ያማረውና ለቤተሰባቸው ይበልጥ ገር የሆኑት ናቸው።››

(በትርምዚ የተዘገበ)

የአላህﷻ ተቆጣጣሪነት ሁሌም ከአእምሮው ጓዳ የማይጠፋው የተውሒድ ሰው፣በተለያዩ የሕይወቱ ገጽታዎችና የኑሮ መስኮች ላይ ለሰው ልጆች ያለው እዝነትና ርህራሄ የበዛ ይሆናል።



Tags: